ትንቢተ ሕዝቅኤል
ምዕራፍ 31
እንዲህም ሆነ፤ በአሥራ አንደኛው ዓመት በሦስተኛው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
2 ፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ የግብጽን ንጉሥ ፈርዖንንና የሕዝቡን ብዛት እንዲህ በላቸው። በታላቅነትህ ማንን መስለሃል?
3 ፤ እነሆ፥ አሦር ጫፉ እንደ ተዋበ፥ ችፍግነቱ ጥላ እንደ ሰጠ፥ ቁመቱም እንደ ረዘመ፥ ራሱም በደመናዎች መካከል እንደ ነበረ እንደ ሊባኖስ ዝግባ ነበረ።
4 ፤ ውኆችም አበቀሉት፥ ቀላይም አሳደገው፥ ወንዞችም በተተከለበት ዙሪያ ይጐርፉ ነበር፥ ፈሳሾቹንም ወደ ምድረ በዳ ዛፍ ሁሉ ሰደደ።
5 ፤ ስለዚህ ቁመቱ ከምድረ በዳ ዛፍ ሁሉ በላይ ከፍ ከፍ አለ፥ ቅርንጫፎቹም በዙ፥ ጫፎቹንም ባበቀለ ጊዜ ከብዙ ውኆች የተነሣ ረዘሙ።
6 ፤ የሰማይ ወፎች ሁሉ ጎጆቻቸውን በቅርንጫፎቹ ላይ አደረጉ፥ የምድርም አራዊት ሁሉ ከጫፎቹ በታች ተዋለዱ፥ ከጥላውም በታች ታላላቆች አሕዛብ ሁሉ ይቀመጡ ነበር።
7 ፤ ሥሩም በብዙ ውኃ አጠገብ ነበረና በታላቅነቱና በጫፎቹ ርዝመት የተዋበ ነበረ።
8 ፤ በእግዚአብሔር ገነት የነበሩ ዝግባዎች አላጨለሙትም፥ ጥዶችም ቅርጫፎቹን አስታ የሚባለውም ዛፍ ጫፎቹን አይመሳሰሉትም ነበር፤ የእግዚአብሔርም ገነት ዛፍ ሁሉ በውበቱ አይመሳሰለውም ነበር።
9 ፤ በጫፎቹም ብዛት ውብ አደረግሁት በእግዚአብሔርም ገነት በዔድን የነበሩ ዛፎች ሁሉ ቀኑበት።
10 ፤ ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ቁመትህ ከፍ ከፍ ብሎአልና፥ ራሱንም በደመናዎች መካከል አድርጎአልና፥
11 ፤ ልቡም በቁመቱ ኰርቶአልና ከአሕዛብ በጨካኙ እጅ አሳልፌ እሰጠዋለሁ፥ እርሱም እንደ ክፋቱ መጠን ያደርግበታል እኔም አሳድደዋለሁ።
12 ፤ የሌላ አገር ሰዎች፥ የአሕዛብ ጨካኞች የሆኑ፥ ቈርጠው ጣሉት፤ በተራሮችና በሸለቆች ሁሉ ውስጥ ጫፎቹ ወደቁ፥ ቅርንጫፎቹም በምድር ፈሳሾች ሁሉ ላይ ተሰባበሩ፥ የምድርም አሕዛብ ሁሉ ከጥላው ተመልሰው ተዉት።
13 ፤
14 ፤ ወደ ጕድጓድ በሚወርዱ በሰው ልጆች መካከል ሁላቸው ለታችኛው ምድር ለሞት አልፈው ተሰጥተዋልና በውኃ አጠገብ ያሉ ዛፎች ሁሉ በቁመታቸው እንዳይረዝሙ፥ ራሳቸውንም በደመናዎች መካከል እንዳያደርጉ፥ ውኃንም የሚጠጡ ኃያላኖቻቸው ሁሉ በቁመታቸው እንዳይቆሙ፥ በወደቀው ግንድ ላይ የሰማይ ወፎች ሁሉ ይቀመጣሉ የምድርም አራዊት ሁሉ በቅርንጫፎቹ ላይ ይሆናሉ።
15 ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ወደ ሲኦል በወረደበት ቀን ልቅሶ አስለቀስሁ፤ ቀላዩንም ስለ እርሱ ሸፈንሁት ፈሳሾቹንም ከለከልሁ ታላላቆችም ውኆች ተከለከሉ፤ ሊባኖስንም ስለ እርሱ አሳዘንሁት፥ የዱርም ዛፎች ሁሉ ስለ እርሱ ዛሉ።
16 ፤ ወደ ጕድጓድ ከሚወርዱ ጋር ወደ ሲኦል በጣልሁት ጊዜ ከመውደቁ ድምፅ የተነሣ አሕዛብን እንቀጠቀጥሁ፤ ውኃም የሚጠጡ ሁሉ፥ ምርጦችና መልካካሞች የሊባኖስ ዛፎች፥ የዔድን ዛፎች ሁሉ በታችኛው ምድር ውስጥ ተጽናንተዋል።
17 ፤ ክንዱም ወደ ነበሩት በአሕዛብም መካከል በጥላው ወደ ተቀመጡት፥ በሰይፍ ወደ ተገደሉት ሰዎች ወደ ሲኦል ከእርሱ ጋር ወረዱ።
18 ፤ በክብርና በታላቅነት በዔድን ዛፎች መካከል ማንን መስለሃል? ነገር ግን ከዔድን ዛፎች ጋር ወደ ታችኛው ምድር ያወርዱሃል፥ በሰይፍም በተገደሉት ባልተገረዙት መካከል ትተኛለህ። ይህም ፈርዖንና የሕዝቡ ብዛት ሁሉ ነው፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።