ምዕራፍ 37

የእግዚአብሔርም እጅ በላዬ ነበረ እግዚአብሔርም በመንፈሱ አወጣኝ አጥንቶችም በሞሉባት ሸለቆ መካከል አኖረኝ።
2 ፤ በእነርሱም አንጻር በዙሪያቸው አሳለፈኝ፤ እነሆም፥ በሸለቆው ፊት እጅግ ብዙ ነበሩ፥ እነሆም፥ እጅግ ደርቀው ነበር።
3 ፤ እርሱም። የሰው ልጅ ሆይ፥ እነዚህ አጥንቶች በሕይወት ይኖራሉን? አለኝ። እኔም። ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ አንተ ታውቃለህ አልሁ።
4 ፤ እርሱም እንዲህ አለኝ። በእነዚህ አጥንቶች ላይ ትንቢት ተናገር እንዲህም በላቸው። እናንተ የደረቃችሁ አጥንቶች ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ሰሙ።
5 ፤ ጌታ እግዚአብሔር ለእነዚህ አጥንቶች እንዲህ ይላል። እነሆ፥ ትንፋሽን አገባባችኋለሁ በሕይወትም ትኖራላችሁ።
6 ፤ ጅማትም እሰጣችኋለሁ ሥጋንም አወጣባችኋለሁ በእናንተም ላይ ቁርበትን እዘረጋለሁ ትንፋሽንም አገባባችኋለሁ በሕይወትም ትኖራላችሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።
7 ፤ እንዳዘዘኝም ትንቢት ተናገርሁ፤ ስናገርም ድምፅ ሆነ፥ እነሆም፥ መናወጥ ሆነ፥ አጥንቶችም አጥንት ከአጥንት ጋር ተቀራረቡ።
8 ፤ እኔም አየሁ፥ እነሆም፥ ጅማት ነበረባቸው ሥጋም ወጣ ቁርበትም በላያቸው ተዘረጋ፥ ትንፋሽ ግን አልነበረባቸውም።
9 ፤ እርሱም። የሰው ልጅ ሆይ፥ ትንቢት ተናገር፥ ለነፋስ ትንቢት ተናገር፥ ለነፋስም። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ነፋስ ሆይ፥ ከአራቱ ነፋሳት ዘንድ ና፥ እነዚህም የተገደሉት በሕይወት ይኖሩ ዘንድ እፍ በልባቸው በል አለኝ።
10 ፤ እንዳዘዘኝም ትንቢት ተናገርሁ፥ ትንፋሽም ገባባቸው ሕያዋንም ሆኑ፥ እጅግም ታላቅ ሠራዊት ሆነው በእግራቸው ቆሙ።
11 ፤ እርሱም እንዲህ አለኝ። የሰው ልጅ ሆይ፥ እነዚህ አጥንቶች የእስራኤል ቤት ሁሉ ናቸው፤ እነሆ። አጥንቶቻችን ደርቀዋል ተስፋችንም ጠፍቶአል ፈጽመንም ተቈርጠናል ብለዋል።
12 ፤ ስለዚህ ትንቢት ተናገር እንዲህም በላቸው። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ሕዝቤ ሆይ፥ እነሆ፥ መቃብራችሁን እከፍታለሁ ከመቃብራችሁም አወጣችኋለሁ፥ ወደ እስራኤልም ምድር አገባችኋለሁ።
13 ፤ ሕዝቤ ሆይ፥ መቃብራችሁን በከፈትሁ ጊዜ ከመቃብራችሁም ባወጣኋችሁ ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።
14 ፤ መንፈሴንም በውስጣችሁ አሳድራለሁ፥ እናንተም በሕይወት ትኖራላችሁ፥ በገዛ ምድራችሁም አኖራችኋለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ተናገርሁ እንዳደረግሁም ታውቃላችሁ፥ ይላል እግዚአብሔር።
15 ፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
16 ፤ አንተ፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ አንድ በትር ውሰድና። ለይሁዳና ለባልንጀሮቹ ለእስራኤል ልጆች ብለህ በላዩ ጻፍ፤ ሌላም በትር ውሰድና። የኤፍሬም በትር ለዮሴፍና ለባልንጀሮቹ ለእስራኤል ቤት ሁሉ ብለህ በላዩ ጻፍ።
17 ፤ አንድ በትርም እንዲሆኑ አንዱን ከሁለተኛው ጋር ለአንተ አጋጥም፥ በእጅህም ውስጥ አንድ ይሁኑ።
18 ፤ የሕዝብህም ልጆች። ይህ የምታደርገው ነገር ምን ማለት እንደሆነ አትነግረንምን? ብለው በተናገሩህ ጊዜ፥
19 ፤ አንተ። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ በኤፍሬም እጅ ያለውን የዮሴፍን በትር ባልንጀሮቹንም የእስራኤልን ነገዶች እወስዳለሁ፥ ከእርሱም ከይሁዳ በትር ጋር አጋጥማቸዋለሁ አንድ በትርም አደርጋቸዋለሁ፥ በእጄም ውስጥ አንድ ይሆናሉ በላቸው።
20 ፤ የምትጽፍባቸውም በትሮች በዓይናቸው ፊት በእጅህ ውስጥ ይሆናሉ።
21 ፤ አንተም እንዲህ ትላቸዋለህ። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ የእስራኤልን ልጆች ከሄዱባቸው ከአሕዛብ መካከል እወስዳለሁ ከስፍራም ሁሉ እሰበስባቸዋለሁ ወደ ገዛ ምድራቸውም አመጣቸዋለሁ፤
22 ፤ በምድርም ላይ በእስራኤል ተራሮች ላይ አንድ ሕዝብ አደርጋቸዋለሁ፥ አንድ ንጉሥም በሁላቸው ላይ ይነግሣል፤ ከዚያ ወዲያ ሁለት ሕዝብ አይሆኑም፥ ከዚያ ወዲያም ሁለት መንግሥቶች ሆነው አይለዩም።
23 ፤ ከዚያ ወዲያም በጣዖቶቻቸውና በርኵሰታቸው በመተላለፋቸውም ሁሉ አይረክሱም፥ ኃጢአትም ከሠሩባት ዓመፅ ሁሉ አድናቸዋለሁ አነጻቸውማለሁ፤ ሕዝብም ይሆኑኛል እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ።
24 ፤ ባሪያዬም ዳዊት ንጉሥ ይሆናቸዋል፤ ለሁሉም አንድ እረኛ ይሆንላቸዋል፤ በፍርዴም ይሄዳሉ ትእዛዜንም ይጠብቃሉ ያደርጓትማል።
25 ፤ አባቶቻችሁም በኖሩበት ለባሪያዬ ለያዕቆብ በሰጠኋት ምድር ይኖራሉ፤ እነርሱና ልጆቻቸው የልጅ ልጆቻቸውም ለዘላለም ይኖሩባታል፤ ባሪያዬም ዳዊት ለዘላለም አለቃ ይሆናቸዋል።
26 ፤ የሰላምም ቃል ኪዳን ከእነርሱ ጋር አደርጋለሁ፥ የዘላለምም ቃል ኪዳን ይሆንላቸዋል፤ እኔም እባርካቸዋለሁ አበዛቸውማለሁ መቅደሴንም ለዘላለም በመካከላቸው አኖራለሁ።
27 ፤ ማደሪያዬም በላያቸው ላይ ይሆናል፤ እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል።
28 ፤ መቅደሴም ለዘላለም በመካከላቸው በሆነ ጊዜ፥ እኔ እስራኤልን የምቀድሰው እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ አሕዛብ ያውቃሉ።