ትንቢተ ሕዝቅኤል
ምዕራፍ 17
የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
2 ፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ በእንቈቅልሽ አጫውት ለእስራኤልም ቤት ምሳሌ ንገር፥ እንዲህም በል።
3 ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ታላቅ ክንፍ ረጅምም ማርገብገቢያ ያለው ላባም የተሞላ፥ መልከ ዝንጕርጕር ታላቅ ንስር ወደ ሊባኖስ መጣ፥ የዝግባንም ጫፍ ወሰደ።
4 ፤ ቀንበጡንም ቀነጠበ ወደ ከነዓንም ምድር ወሰደው በነጋዶችም ከተማ አኖረው።
5 ፤ ከምድርም ዘር ወሰደ በፍሬያማ እርሻ ተከለው በብዙም ውኃ አጠገብ እንደ አኻያ ዛፍ አኖረው።
6 ፤ በበቀለም ጊዜ ቁመቱ ያጠረ አረጉም ወደ እርሱ የሚመለስ ሥሩም በበታቹ የነበረ ሰፊ ወይን ሆነ፥ እንዲሁ ወይን ሆነ አረግም ሰደደ ቀንበጥም አወጣ።
7 ፤ ታላቅ ክንፍና ብዙ ላባም ያለው ሌላ ታላቅ ንስር ነበረ፤ እነሆም፥ ያጠጣው ዘንድ ይህ ወይን ሥሩን ወደ እርሱ አዘነበለ አረጉንም ከተተከለበት ከመደቡ ወደ እርሱ ሰደደ።
8 ፤ አረግም ያወጣ ፍሬም ያፈራ የከበረም ወይን ይሆን ዘንድ በመልካም መሬት ውስጥ በብዙም ውኃ አጠገብ ተተክሎ ነበር።
9 ፤ እንዲህም በል። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በውኑ ይከናወንለት ይሆንን? ይደርቅስ ዘንድ፥ አዲስ የበቀለውስ ቅጠሉ ይጠወልግ ዘንድ ሥሩን አይነቅለውምን? ፍሬውንስ አይለቅመውምን? ሥሩም የተነቀለው በብርቱ ክንድና በብዙ ሕዝብ አይደለም።
10 ፤ ተተክሎስ፥ እነሆ፥ ይከናወንለት ይሆንን? የምሥራቅ ነፋስ ባገኘው ጊዜ ፈጽሞ አይደርቅምን? በተተከለበት መደብ ላይ ይደርቃል።
11 ፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
12 ፤ ለዓመፀኛ ቤት። ይህ ትርጓሜ ምን እንደ ሆነ አታውቁምን? በላቸው። እንዲህም ብለህ ንገራቸው። እነሆ፥ የባቢሎን ንጉሥ ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፥ ንጉሥዋንና መኳንንቶችዋንም ማረከ፥ ወደ እርሱም ወደ ባቢሎን ወሰዳቸው።
13 ፤ ከመንግሥትም ዘር ወስዶ ቃል ኪዳን ከእርሱ ጋር አደረገ፤ አማለውም፥ የምድሪቱንም ኃያላን ወሰደ፤
14 ፤ ይኸውም ቃል ኪዳኑን በመጠበቅ እንድትጸና እንጂ መንግሥቱ እንድትዋረድና ከፍ እንዳትል ነው።
15 ፤ እርሱ ግን በእርሱ ላይ ሸፈተ ፈረሶችንና ብዙንም ሕዝብ ይሰጡት ዘንድ መልእክተኞችን ወደ ግብጽ ላከ። በውኑ ይከናወንለት ይሆንን? ይህንስ ያደረገ ያመልጣልን? ቃል ኪዳንንስ አፍርሶ ያመልጣልን?
16 ፤ እኔ ሕያው ነኝና ያነገሠውና መሐላውን የናቀበቱ፥ ቃል ኪዳኑንም ያፈረሰበቱ ንጉሥ በሚኖርበት ስፍራ ከእርሱ ጋር በባቢሎን መካከል በእርግጥ ይሞታል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
17 ፤ ብዙዎችን ነፍሳት ለማስወገድ አፈርን በደለደሉ ምሽግም በሠሩ ጊዜ፥ ፈርዖን ከብዙ ሠራዊቱና ከታላቁ ጉባኤው ጋር በሰልፍ አይረዳውም።
18 ፤ ቃል ኪዳኑንም በማፍረስ መሐላውን ንቆአል፤ እነሆም፥ እጁን ሰጠ፥ ይህንም ሁሉ አድርጎአል፤ ስለዚህ አያመልጥም።
19 ፤ ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እኔ ሕያው ነኝና የናቀውን መሐላዬን ያፈረሰውንም ቃል ኪዳኔን በራሱ ላይ አመጣለሁ።
20 ፤ መረቤንም በእርሱ ላይ እዘረጋለሁ በወጥመድም ይያዛል፥ ወደ ባቢሎንም አመጣዋለሁ በእኔም ላይ ስላደረገው ዓመፅ በዚያ ከእርሱ ጋር እፋረዳለሁ።
21 ፤ ጭፍሮቹም ሁሉ በሰይፍ ይወድቃሉ፥ የቀሩትም ሁሉ ወደ እየነፋሳቱ ይበተናሉ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ተናገርሁ ታውቃላችሁ።
22 ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ከረጅሙ ዝግባ ጫፍ ላይ ቀንበጥን ወስጄ አኖረዋለሁ፤ ከጫፎቹ አንዱን ቀንበጥ እቀነጥበዋለሁ፤ በረጅምና በታላቅ ተራራም ላይ እተክለዋለሁ።
23 ፤ ከፍ ባለው በእስራኤል ተራራ ላይ እተክለዋለሁ፥ ቅርንጫፎችም ያወጣል ፍሬም ያፈራል የከበረም ዝግባ ይሆናል፤ በበታቹም ወፎች ሁሉ ያርፋሉ፥ በቅርንጫፎቹም ጥላ በክንፍ የሚበርር ሁሉ ይጠጋል።
24 ፤ የዱር ዛፎች ሁሉ ረጅሙን ዛፍ ዝቅ ያደረግሁ፥ አጭሩንም ዛፍ ከፍ ያደረግሁ፥ የለመለመውንም ዛፍ ያደረቅሁ፥ የደረቀውንም ዛፍ ያለመለምሁ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ፤ እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁ እኔም አድርጌአለሁ።