ምዕራፍ 32

እንዲህም ሆነ፤ በአሥራ ሁለተኛው ዓመት በአሥራ ሁለተኛው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
2 ፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ ስለ ግብጽ ንጉሥ ስለ ፈርዖን ሙሾ አሙሽ፥ እንዲህም በለው። የአሕዛብን አንበሳ መስለህ ነበር፥ ነገር ግን እንደ ባሕር ዘንዶ ሆነሃል፤ በወንዞችህም ወጥተሃል፥ ወኃውንም በእግርህ አደፍርሰሃል፥ ወንዞችህንም አሳድፈሃል።
3 ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በብዙ አሕዛብ ጉባኤ መረቤን እዘረጋብሃለሁ፥ እነርሱም በመረቤ ያወጡሃል።
4 ፤ በምድርም ላይ እተውሃለሁ፥ በምድረ በዳም ፊት እጥልሃለሁ፥ የሰማይንም ወፎች ሁሉ አሳርፍብሃለሁ፥ የምድርንም አራዊት ሁሉ ከአንተ አጠግባቸዋለሁ።
5 ፤ ሥጋህን በተራሮች ላይ አደርጋለሁ ሸለቆቹንም በሬሳህ ክምር እሞላለሁ።
6 ፤ የምትዋኝባትንም ምድር እስከ ተራሮች ድረስ በደምህ አጠጣለሁ፥ መስኖችም ከአንተ ይሞላሉ።
7 ፤ ባጠፋሁህም ጊዜ ሰማዮችን እሸፍናለሁ፥ ከዋክብቶችንም አጨልማለሁ፤ ፀሐዩንም በደመና እሸፍናለሁ ጨረቃም ብርሃኑን አይሰጥም።
8 ፤ የሰማይን ብርሃኖች ሁሉ በላይህ አጨልማለሁ፥ በምድርህም ላይ ጨለማ አደርጋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
9 ፤ በማታውቃቸውም አገሮች ባሉ በአሕዛብ ዘንድ ጥፋትህን ባመጣሁ ጊዜ የብዙ ሕዝብን ልብ አስጨንቃለሁ።
10 ፤ ብዙም አሕዛብን አስደንቅብሃለሁ ሰይፌንም በፊታቸው ባወዛወዝሁ ጊዜ ነገሥታቶቻቸው ስለ አንተ እጅግ አድርገው ይፈራሉ፤ በወደቅህበትም ቀን እያንዳንዱ ስለ ነፍሱ በየጊዜው ሁሉ ይንቀጠቀጣል።
11 ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። የባቢሎን ንጉሥ ሰይፍ ይመጣብሃል።
12 ፤ በኃያላን ሰይፍ የሕዝብህን ብዛት እጥላለሁ፤ ሁሉ የአሕዛብ ጨካኞች ናቸው፤ የግበጽንም ትዕቢት ያጠፋሉ ብዛትዋም ሁሉ ይጠፋል።
13 ፤ በብዙም ውኃ አጠገብ ያሉትን እንስሶች ሁሉ አጠፋለሁ፤ ከእንግዲህም ወዲያ የሰው እግር አያደፈርሰውም የእንስሳም ኮቴ አይረግጠውም።
14 ፤ በዚያን ጊዜ ውኃቸውን አጠራለሁ፥ ወንዞቻቸውም እንደ ዘይት እንዲፈስሱ አደርጋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
15 ፤ የግብጽንም ምድር ባድማና ውድማ ባደረግሁ ጊዜ፥ ሞላዋንም ያጣች ምድር ባደረግኋት ጊዜ፥ የሚኖሩባትንም ሁሉ በቀሠፍሁ ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።
16 ፤ የሚያለቅሱበት ልቅሶ ይህ ነው፤ የአሕዛብ ቈነጃጅት ያለቅሱበታል፤ ስለ ግብጽና ስለ ብዛትዋ ሁሉ ያለቅሱበታል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
17 ፤ እንዲህም ሆነ፤ በአሥራ ሁለተኛው ዓመት ከወሩም በአሥራ አምስተኛው ቀን የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
18 ፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ ስለ ግብጽ ብዛት ዋይ በል፥ እርስዋንና የብርቱዎችን አሕዛብ ሴቶች ልጆች ወደ ጕድጓድ ከሚወርዱ ጋር ወደ ታችኛው ምድር ጣላቸው።
19 ፤ በውበት የምትበልጪው ማን ነው? ውረጂ ካልተገረዙትም ጋር ተኚ።
20 ፤ በሰይፍ በተገደሉት መካከል ይወድቃሉ፤ ለሰይፍ ተሰጥታለች፤ እርስዋንና ብዛትዋን ሁሉ ጐትቱ።
21 ፤ የኃያላን አለቆች በሲኦል ውስጥ ሆነው ከረዳቶቹ ጋር ይናገሩታል፤ በሰይፍም የተገደሉት ያልተገረዙ ወርደው ተኝተዋል።
22 ፤ አሦርና ጉባኤዋ ሁሉ በዚያ አሉ፤ መቃብራቸው በዙሪያቸው ነው፤ ሁሉም በሰይፍ ወድቀው ተገደሉ።
23 ፤ መቃብራቸው በጕድጓዱ በውስጠኛው ክፍል ነው፥ ጉባኤዋም በመቃብርዋ ዙሪያ ነው፤ በሕያዋን ምድር ያስፈሩ ሁሉ በሰይፍ ወድቀው ተገድለዋል።
24 ፤ ኤላምም በዚያ አለች ብዛትዋም ሁሉ በመቃብርዋ ዙሪያ ነው፤ በሕያዋን ምድር ያስፈሩ ሁሉ በሰይፍ ወድቀው ተገድለዋል ሳይገረዙም ወደ ታችኛው ምድር ወርደዋል፥ ወደ ጕድጓድም ከሚወርዱ ጋር እፍረታቸውን ተሸክመዋል።
25 ፤ በተገደሉት መካከል ከብዛትዋ ሁሉ ጋር መኝታን አድርገውላታል፤ መቃብርዋ በዙሪያዋ ነው ሁሉም ያልተገረዙና በሰይፍ የተገደሉ ናቸው፤ በሕያዋንም ምድር ያስፈሩ ነበር ወደ ጕድጓድም ከሚወርዱ ጋር እፍረታቸውን ተሸክመዋል፥ በተገደሉትም መካከል ተሰጥተዋል።
26 ፤ ሞሳሕና ቶቤል ብዛታቸውም ሁሉ በዚያ አሉ መቃብራቸውም በዙሪያቸው ነው፤ ሁሉም ሳይገረዙ በሰይፍ ተገድለዋል፤ በሕያዋን ምድር ያስፈሩ ነበርና።
27 ፤ በሕያዋንም ምድር ኃያላኑን ያስፈሩ ነበርና መሣሪያቸውን ይዘው ወደ ሲኦል ከወረዱ፥ ሰይፋቸውንም ከራሳቸው በታች ካደረጉ፥ ኃጢአታቸውም በአጥንታቸው ላይ ከሆነ ጋር ከወደቁ ካልተገረዙ ኃያላን ጋር ይተኛሉ።
28 ፤ አንተም ባልተገረዙት መካከል ትሰበራለህ፥ በሰይፍም ከተገደሉት ጋር ትተኛለህ።
29 ፤ ኤዶምያስና ነገሥታቶችዋ አለቆችዋም ሁሉ በዚያ አሉ፤ በሰይፍ ከተገደሉት ጋር በኃይላቸው ተኝተዋል፤ ካልተገረዙትና ወደ ጕድጓድ ከሚወርዱ ጋር ይተኛሉ።
30 ፤ የሰሜን አለቆች ሁሉ ሲዶናውያንም ሁሉ ከተገደሉት ጋር ወርደው በዚያ አሉ፤ በኃይላቸውም ያስፈሩ በነበረው ፍርሃት አፍረዋል፥ በሰይፍም ከተገደሉት ጋር ሳይገረዙ ተኝተዋል፥ ወደ ጕድጓድም ከሚወርዱት ጋር እፍረታቸውን ተሸክመዋል።
31 ፤ በሰይፍ የተገደሉ ፈርዖንና ሠራዊቱ ሁሉ ያዩአቸዋል ፈርዖንም ስለ ብዛቱ ሁሉ ይጽናናል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
32 ፤ መፈራቱን በሕያዋን ምድር አድርጌአለሁ፥ ፈርዖንና ብዛቱም ሁሉ በሰይፍ በተገደሉት ባልተገረዙት መካከል ይተኛሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።