ትንቢተ ሕዝቅኤል
ምዕራፍ 24
በዘጠነኛው ዓመት በአሥረኛው ወር ከወሩም በአሥረኛው ቀን የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
2 ፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ የዚህን ቀን፥ የዛሬን ቀን ስም ጻፍ፤ በዚህ ቀን የባቢሎን ንጉሥ ወደ ኢየሩሳሌም ቀረበ።
3 ፤ ለዓመፀኛውም ቤት ምሳሌን ተናገር እንዲህም በላቸው። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ጣድ፥ ምንቸቲቱን ጣድ፥ ውኃም ጨምርባት።
4 ፤ ቍራጭዋንም፥ መልካሙን ቍራጭ ሁሉ፥ ጭኑንና ወርቹን በእርስዋ ውስጥ ሰብስብ፥ የተመረጡትንም አጥንቶች ሙላባት።
5 ፤ ከመንጋው የተመረጠውን ውሰድ፥ አጥንቶቹም እንዲበስሉ እንጨት በበታችዋ ማግድ፤ አጥንቶቹም በውስጥዋ ይቀቀሉ።
6 ፤ ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ዝገትዋ ላለባት ዝገትዋም ከእርስዋ ላልወጣ ምንቸት፥ ለደም ከተማ ወዮላት! ቍራጭ ቍራጩን አውጣ፤ ዕጣ አልወደቀባትም።
7 ፤ ደምዋ በውስጥዋ አለ። በተራቈተ ድንጋይ ላይ አደረገችው እንጂ በአፈር ይከደን ዘንድ በመሬት ላይ አላፈሰሰችውም፤
8 ፤ መዓቴን አወጣ ዘንድ፥ በቀሌንም እበቀል ዘንድ፥ ደምዋ እንዳይከደን በተራቈተ ድንጋይ ላይ አደረግሁ።
9 ፤ ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ለደም ከተማ ወዮላት! እኔ ደግሞ ማገዶዋን ታላቅ አደርገዋለሁ።
10 ፤ እንጨቱን አብዛ፤ እሳቱን አንድድ፤ ሥጋውን ቀቅል፤ መረቁን አጣፍጠው፤ አጥንቶቹ ይቃጠሉ።
11 ፤ ትሞቅም ዘንድ ናስዋም ትግል ዘንድ ርኵሰትዋም በውስጥዋ ይቀልጥ ዘንድ ዝገትዋም ይጠፋ ዘንድ ባዶዋን በፍም ላይ አድርጋት።
12 ፤ በከንቱ ደከመች፤ ሆኖም ዝገትዋ በእሳት ስንኳ አልለቀቀም።
13 ፤ በርኵሰትሽ ሴሰኝነት አለ፤ አነጻሁሽ አልነጻሽምና መዓቴን በላይሽ እስክጨርስ ድረስ እንግዲህ ከርኵሰትሽ አትነጺም።
14 ፤ እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁ፤ ይመጣል፥ እኔም አደርገዋለሁ፤ አልመለስም፥ አልራራም፥ አልጸጸትም፤ እንደ መንገድሽና እንደ ሥራሽ ይፈርዱብሻል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
15 ፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
16 ፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ እነሆ፥ የዓይንህን አምሮት በመቅሠፍት እወስድብሃለሁ፤ አንተም ወይ አትበል አታልቅስም እንባህንም አታፍስስ።
17 ፤ በቀስታ ተክዝ፤ ለምዋቾችም አታልቅስ፥ መጠምጠሚያህን በራስህ ላይ አድርግ፥ ጫማህንም በእግርህ አጥልቅ፥ ከንፈሮችህንም አትሸፍን የሰዎችንም እንጀራ አትብላ።
18 ፤ እኔም በማለዳ ለሕዝቡ ተናገርሁ፥ ወደ ማታም ሚስቴ ሞተች፤ በነጋውም እንደ ታዘዝሁ አደረግሁ።
19 ፤ ሕዝቡም። ይህ የምታደርገው ነገር ለእኛ ምን እንደ ሆነ አትነግረንምን? አሉኝ።
20 ፤ እኔም እንዲህ አልኋቸው። የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
21 ፤ ለእስራኤል ቤት ተናገር እንዲህም በል። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ የኃይላችሁን ትምክሕት፥ የዓይናችሁን አምሮት፥ የነፍሳችሁን ምኞት መቅደሴን አረክሳለሁ፤ ያስቀራችኋቸውም ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁ በሰይፍ ይወድቃሉ።
22 ፤ እኔም እንዳደረግሁ እናንተ ታደርጋላችሁ፤ ከንፈራችሁን አትሸፍኑም የሰዎችንም እንጀራ አትበሉም።
23 ፤ መጠምጠሚያችሁም በራሳችሁ ጫማችሁም በእግራችሁ ይሆናል፤ ዋይ አትሉም አታለቅሱምም፤ በኃጢአታችሁም ትሰለስላላችሁ፥ እርስ በርሳችሁም ታንጐራጕራላችሁ።
24 ፤ ሕዝቅኤልም ምልክት ይሆናችኋል፤ እርሱ እንዳደረገ ሁሉ እናንተ ታደርጋላችሁ፤ ይህም በመጣ ጊዜ እኔ ጌታ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።
25 ፤ አንተም የሰው ልጅ ሆይ፥ ኃይላቸውን፥ የተመኩበትንም ደስታ፥ የዓይናቸውን አምሮት፥ የነፍሳቸውንም ምኞት፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን በወሰድሁባቸው ቀን፥
26 ፤ በዚያ ቀን ያመለጠው ይህን ነገር በጆሮህ ያሰማ ዘንድ ወደ አንተ ይመጣል።
27 ፤ በዚያ ቀን አፍህ ላመለጠው ይከፈታል፥ አንተም ትናገራለህ ከዚያ ወዲያም ዲዳ አትሆንም፤ ምልክትም ትሆናቸዋለህ፥ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።