ምዕራፍ 36

አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ ለእስራኤል ተራሮች ትንቢት ተናግረህ። የእስራኤል ተራሮች ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ በል።
2 ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ጠላት በእናንተ ላይ። እሰይ፥ የጥንት ከፍታዎች ለእኛ ርስት ሆነዋል ብሎአልና
3 ፤ ስለዚህ ትንቢት ተናገር እንዲህም በል። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ለቀሩት አሕዛብ ርስት ትሆኑ ዘንድ በዙሪያችሁ ያሉ ባድማ አድርገዋችኋልና፥ ውጠዋችሁማልና፥ እናንተም የተናጋሪዎች ከንፈር መተረቻና የአሕዛብ ማላገጫ ሆናችኋልና
4 ፤ ስለዚህ፥ እናንተ የእስራኤል ተራሮች ሆይ፥ የጌታን የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ። ጌታ እግዚአብሔር ለተራሮችና ለኮረብቶች፥ ለፈሳሾችና ለሸለቆች ለምድረ በዳዎች ባዶ ለሆኑትም በዙሪያ ላሉት ለቀሩት አሕዛብ ምርኮና መሳቂያ ለሆኑት ከተሞች እንዲህ ይላል፤
5 ፤ ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ያሳድዱአትና ይበዘብዙአት ዘንድ በልባቸው ሁሉ ደስታና በነፍሳቸው ንቀት ምድሬን ርስት አድርገው ለራሳቸው በሰጡ በቀሩት አሕዛብና በኤዶምያስ ሁሉ ላይ በቅንዓቴ እሳት ተናግሬአለሁ፤
6 ፤ ስለዚህ ስለ እስራኤል ምድር ትንቢት ተናገር፥ ለተራሮችና ለኮረብቶችም ለፈሳሾችና ለሸለቆችም እንዲህ በል። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ የአሕዛብን ስድብ ስለ ተሸከማችሁ በቅንዓቴና በመዓቴ ተናግሬአለሁ፤
7 ፤ ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በዙሪያችሁ ያሉ አሕዛብ ስድባቸውን በእርግጥ ይሸከማሉ ብዬ ምያለሁ።
8 ፤ የእስራኤል ተራሮች ሆይ፥ እናንተ ግን ቅርንጫፎቻችሁን ታቈጠቍጣላችሁ፥ ይመጡም ዘንድ ቀርበዋልና ለሕዝቤ ለእስራኤል ፍሬአቸሁን ትሰጣላችሁ።
9 ፤ እነሆ፥ እኔ ለእናንተ ነኝና፤ ወደ እናንተም እመለከታለሁ፥ እናንተም ትታረሳላችሁ ይዘራባችሁማል፤
10 ፤ እኔም የእስራኤልን ቤት ሰዎች ሁሉ ሁሉንም አበዛባችኋለሁ፥ በከተሞችም ሰዎች ይኖሩባቸዋል ባድማዎቹም ስፍራዎች ይሠራሉ፤
11 ፤ ሰውንና እንስሳውንም አበዛባችኋለሁ፥ እነርሱም ይበዛሉ ያፈሩማል፤ እንደ ጥንታችሁም ሰዎችን አኖርባችኋለሁ፥ ቀድሞም ካደረግሁላችሁ ይልቅ መልካም አደርግላችኋለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።
12 ፤ ሰዎችንም፥ ሕዝቤን እስራኤልን፥ በእናንተ ላይ አስሄዳቸዋለሁ፤ እነርሱም ይወርሱሻል ርስትም ትሆኛቸዋለሽ፥ ከእንግዲህም ወዲያ ልጅ አልባ አታደርጊአቸውም።
13 ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነርሱ። ሰው በሊታ ምድር ነሽ ሕዝብሽንም ልጅ አልባ የምታደርጊ ነሽ ብለዋችኋልና
14 ፤ ስለዚህ ዳግመኛ ሰው በሊታ አትሆኝም፥ ዳግመኛም ሕዝብሽን ልጅ አልባ አታደርጊም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤
15 ፤ ዳግመኛም የአሕዛብን ውርደት አላሰማብሽም፥ ዳግመኛም የአሕዛብን ስድብ አትሸከሚም፥ ዳግመኛም ሕዝብሽን አታሰናክዪም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
16 ፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
17 ፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ የእስራኤል ቤት በምድራቸው በተቀመጡ ጊዜ በመንገዳቸውና በሥራቸው አረከሱአት፥ መንገዳቸውም በፊቴ እንደ መርገም አደፍ ነበረ።
18 ፤ በምድር ላይ ስላፈሰሱት ደም በጣዖቶቻቸውም ስላረከሱአት መዓቴን አፈሰስሁባቸው፤
19 ፤ ወደ አሕዛብም በተንኋቸው ወደ አገሮችም ተዘሩ፤ እንደ መንገዳቸውና እንደ ሥራቸው መጠን ፈረድሁባቸው።
20 ፤ ወደ መጡባቸውም ወደ አሕዛብ በመጡ ጊዜ፥ ሰዎች እነርሱን። ከምድሩ የወጡ የእግዚአብሔር ሕዝብ እነዚህ ናቸው ሲሉአቸው ቅዱስ ስሜን አረከሱ።
21 ፤ እኔ ግን የእስራኤል ቤት በመጡባቸው በአሕዛብ መካከል ስላረከሱት ስለ ቅዱስ ስሜ ስል ራራሁላቸው።
22 ፤ ስለዚህ ለእስራኤል ቤት እንዲህ በል። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የእስራኤል ቤት ሆይ፥ በመጣችሁባቸው በአሕዛብ መካከል ስላረከሳችሁት ስለ ቅዱስ ስሜ ነው እንጂ ስለ እናንተ የምሠራ አይደለሁም።
23 ፤ በአሕዛብም ዘንድ የረከሰውን፥ በመካከላቸው ያረከሳችሁትን ስሜን እቀድሰዋለሁ፤ በዓይናቸውም ዘንድ በተቀደስሁባችሁ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ አሕዛብ ያውቃሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
24 ፤ ከአሕዛብም መካከል አወጣችኋለሁ ከየአገሩም ሁሉ እሰበስባችኋለሁ ወደ ገዛ ምድራችሁም አመጣችኋለሁ።
25 ፤ ጥሩ ውኃንም እረጭባችኋለሁ እናንተም ትጠራላችሁ፥ ከርኵሰታችሁም ሁሉ ከጣዖቶቻችሁም ሁሉ አጠራችኋለሁ።
26 ፤ አዲስም ልብ እሰጣችኋለሁ አዲስም መንፈስ በውስጣችሁ አኖራለሁ፤ የድንጋዩንም ልብ ከሥጋችሁ አወጣለሁ፤ የሥጋንም ልብ እሰጣችኋለሁ።
27 ፤ መንፈሴንም በውስጣችሁ አኖራለሁ በትእዛዜም አስሄዳችኋለሁ፥ ፍርዴንም ትጠብቃላችሁ ታደርጉትማላችሁ።
28 ፤ ለአባቶቻችሁም በሰጠኋት ምድር ትኖራላችሁ፤ ሕዝብም ትሆኑኛላችሁ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ።
29 ፤ ከርኵሰታችሁም ሁሉ አድናችኋለሁ፤ እህልንም እጠራዋለሁ አበዛውማለሁ ራብንም አላመጣባችሁም።
30 ፤ ደግሞም የራብን ስድብ ከአሕዛብ ዘንድ እንዳትሸከሙ የዛፍን ፍሬና የእርሻውን ቡቃያ አበዛለሁ።
31 ፤ ክፉውን መንገዳችሁንና መልካም ያይደለውን ሥራችሁንም ታስባላችሁ፥ ስለ በደላችሁና ስለ ርኵሰታችሁም ራሳችሁን ትጸየፋላችሁ።
32 ፤ ይህን የሠራሁ ስለ እናንተ እንዳይደለ በእናንተ ዘንድ የታወቀ ይሁን፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ስለ መንገዳችሁ እፈሩና ተዋረዱ።
33 ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ከኃጢአታችሁ ሁሉ ባነጻኋችሁበት ቀን በከተሞች ሰዎችን አኖራለሁ ባድማዎቹም ስፍራዎች ይሠራሉ።
34 ፤ ባድማ የነበረች በመንገደኛም ሁሉ ዓይን ዘንድ ባድማ የነበረች ምድር ትታረሳለች።
35 ፤ ሰዎችም። ባድማ የነበረች ይህች ምድር እንደ ዔድን ገነት ሆናለች፤ የፈረሱት ባድማ የሆኑት የጠፉትም ከተሞች ተመሽገዋል ሰውም የሚኖርባቸው ሆነዋል ይላሉ።
36 ፤ በዙሪያችሁም የቀሩት አሕዛብ እኔ እግዚአብሔር የፈረሱትን ስፍራዎች እንደ ሠራሁ ውድማ የሆነውንም እንደ ተከልሁ ያውቃሉ፤ እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁ፥ እኔም አደርገዋለሁ።
37 ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ስለዚህ ደግሞ አደርግላቸው ዘንድ የእስራኤል ቤት ይሹኛል ሰውንም እንደ መንጋ አበዛላቸዋለሁ።
38 ፤ እንደ ተቀደሱ በጎች፥ በበዓላቶችዋ ቀን እንደሚሆኑ እንደ ኢየሩሳሌም በጎች፥ እንዲሁ የፈለሱት ከተሞች በሰዎች መንጋ ይሞላሉ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።