ምዕራፍ 35

የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
2 ፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ ፊትህን ወደ ሴይር ተራራ አድርግ፥ ትንቢትም ተናገርበት፥
3 ፤ እንዲህም በለው። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የሴይር ተራራ ሆይ፥ እነሆ፥ በአንተ ላይ ነኝ፥ እጄንም እዘረጋብሃለሁ ባድማና ውድማም አደርግሃለሁ።
4 ፤ ከተሞችህንም አፈራርሳቸዋለሁ፥ አንተም ባድማ ትሆናለህ፥ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃለህ።
5 ፤ የዘላለም ጥል ስላለህ በመከራቸውም ጊዜ በኋለኛይቱ የኃጢአታቸው ቀጠሮ ጊዜ የእስራኤልን ልጆች በሰይፍ እጅ ጥለሃቸዋልና
6 ፤ ስለዚህ እኔ ሕያው ነኝና ለደም አሳልፌ እሰጥሃለሁ ደምም ያሳድድሃል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ደምን ስላልጠላህ ደም ያሳድድሃል።
7 ፤ የሴይርንም ተራራ ውድማ አደርገዋለሁ፥ የሚሄደውንና የሚመለሰውንም ከእርሱ አጠፋለሁ።
8 ፤ ተራሮቹንም በተገደሉት ሰዎች እሞላለሁ፤ በኮረብቶችህና በሸለቆችህ በፈሳሾችህም ሁሉ ላይ በሰይፍ የተገደሉት ሁሉ ይወድቃሉ።
9 ፤ ለዘላለምም ባድማ አደርግሃለሁ ከተሞችህም ሰው የማይኖርባቸው ይሆናሉ፥ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።
10 ፤ እግዚአብሔርም በዚያ ሳለ፥ አንተ። እነዚህ ሁለቱ ሕዝቦች እነዚህም ሁለቱ አገሮች ለእኔ ይሆናሉ እኛም እንወርሳቸዋለን ብለሃልና
11 ፤ ስለዚህ እኔ ሕያው ነኝና እንደ ቍጣህ መጠን እነርሱንም ጠልተህ እንዳደረግኸው እንደ ቅንዓትህ መጠን እኔ እሠራለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ በፈረድሁብህም ጊዜ በእነርሱ ዘንድ የታወቅሁ እሆናለሁ።
12 ፤ አንተም። ፈርሰዋል መብልም ሆነው ለእኛ ተሰጥተዋል ብለህ በእስራኤል ተራሮች ላይ የተናገርኸውን ስድብ ሁሉ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሰማሁት ታውቃለህ።
13 ፤ በአፋችሁም ተመካችሁብኝ፥ ቃላችሁንም አበዛችሁብኝ፤ እኔም ሰምቼዋለሁ።
14 ፤ ጌታ እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል። ምድር ሁሉ ደስ ሲላት አንተን ባድማ አደርግሃለሁ።
15 ፤ የእስራኤል ቤት ርስት ባድማ ስለ ሆነ በላዩ ደስ እንዳለህ፥ እንዲሁ አደርግብሃለሁ፤ የሴይር ተራራ ሆይ፥ አንተና ኤዶምያስ ሁሉ ሁለንተናውም ባድማ ትሆናላችሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።