ትንቢተ ሕዝቅኤል
ምዕራፍ 30
የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
2 ፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ ትንቢት ተናገር እንዲህም በል። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ዋይ! በሉ፥ ለቀኑ ወዮ! ቀኑ ቅርብ ነው፥
3 ፤ የእግዚአብሔር ቀን ቅርብ ነው፥ የደመና ቀን፥ የአሕዛብ ጊዜ ይሆናል።
4 ፤ ሰይፍ በግብጽ ላይ ይመጣል፥ ሁከትም በኢትዮጵያ ይሆናል፤ የተገደሉትም በግብጽ ውስጥ ይወድቃሉ፥ ብዛትዋንም ይወስዳሉ፥ መሠረትዋም ይፈርሳል።
5 ፤ ኢትዮጵያና ፉጥ ሉድም የተደባለቀም ሕዝብ ሁሉ ኩብም ቃል ኪዳንም የገባችው ምድር ልጆች ከእነርሱ ጋር በሰይፍ ይወድቃሉ።
6 ፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ግብጽን የሚደግፉ ይወድቃሉ፥ የኃይልዋም ትዕቢት ይወርዳል፤ ከሚግዶል ጀምሮ እስከ ሴዌኔ ድረስ በእርስዋ ውስጥ በሰይፍ ይወድቃሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
7 ፤ ባድማም በሆኑ አገሮች መካከል ባድማ ይሆናሉ፥ ከተሞችዋም በፈረሱ ከተሞች መካከል ይሆናሉ።
8 እሳትንም በግብጽ ባነደድሁ ጊዜ ረዳቶችዋም ሁሉ በተሰበሩ ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።
9 በዚያ ቀን መልእክተኞች ተዘልለው የሚኖሩትን ኢትዮጵያውያንን ለማስፈራት ከፊቴ በመርከብ ይወጣሉ፤ እንደ ግብጽም ቀን ሁከት ይሆንባቸዋል፤ እነሆ፥ ይመጣልና።
10 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የግብጽን ብዛት በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነፆር እጅ እሽራለሁ።
11 እርሱና የአሕዛብ ጨካኞች ሕዝቡ ምድሪቱን ለማጥፋት ይመጣሉ፤ ሰይፋቸውንም በግብጽ ላይ ይመዝዛሉ ምድሪቱንም በተገደሉት ይሞላሉ።
12 ፤ ወንዞችንም ምድረ በዳ አደርጋለሁ ምድሪቱንም በክፉ ሰዎች እጅ እሸጣለሁ፥ ምድሪቱንና ሙላዋንም በእንግዶች እጅ ባድማ አደርጋለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ተናግሬያለሁ።
13 ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ጣዖቶቹን አጠፋለሁ ምስሎችንም ከሜምፎስ እሽራለሁ፤ ከእንግዲህ ወዲያ በግብጽ ምድር አለቃ አይሆንም፥ በግብጽም ምድር ላይ ፍርሃትን አደርጋለሁ።
14 ፤ ጳትሮስንም አፈርሳለሁ፥ በጣኔዎስም እሳትን አነድዳለሁ፥ በኖእ ላይም ፍርድን አደርጋለሁ።
15 ፤ በግብጽም ምሽግ በሲን ላይ መዓቴን አፈስሳለሁ፥ የኖእንም ብዛት አጠፋለሁ።
16 ፤ በግብጽም እሳትን አነድዳለሁ፥ ሲንም ትጨነቃለች ኖእም ትሰበራለች፥ በሜምፎስም በየቀኑ ጠላቶች ይሆኑባታል።
17 ፤ የሄልዮቱ ከተማና የቡባስቱም gWlማሶች በሰይፍ ይወድቃሉ ሴቶችም ይማረካሉ።
18 ፤ የግብጽን ቀንበር በዚያ በሰበርሁ ጊዜ በጣፍናስ ቀኑ ይጨልማል የኃይልዋም ትዕቢት ይጠፋባታል፤ ደመናም ይጋርዳታል፥ ሴቶች ልጆችዋም ይማረካሉ።
19 ፤ እንዲሁ በግብጽ ላይ ፍርድን አደርጋለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።
20 ፤ እንዲህም ሆነ፤ በአሥራ አንደኛው ዓመት በመጀመሪያው ወር ከወሩም በሰባተኛው ቀን የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
21 ፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ የግብጽን ንጉሥ የፈርዖንን ክንድ ሰብሬያለሁ፤ እነሆም፥ በጨርቅ በመጠቅለል ይፈወስ ዘንድ ሰይፉንም ለመያዝ እንዲበረታ አልታሰረም።
22 ፤ ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ እኔ በግብጽ ንጉሥ በፈርዖን ላይ ነኝ፥ የጸናችውንና የተሰበረችውንም ክንዱን እሰብራለሁ፥ ሰይፉንም ከእጁ አስረግፈዋለሁ።
23 ፤ ግብጻውያንንም ወደ አሕዛብ እበትናለሁ ወደ አገሮችም እዘራቸዋለሁ።
24 ፤ የባቢሎንንም ንጉሥ ክንድ አበረታለሁ ሰይፌንም በእጁ እሰጣለሁ፤ የፈርዖንን ክንድ ግን እሰብራለሁ፥ ተወግቶም በሚሞተው እንጕርጕሮ በፊቱ ያንጐራጕራል።
25 ፤ የባቢሎንንም ንጉሥ ክንድ አጸናለሁ የፈርዖንም ክንድ ይወድቃል፤ ሰይፌንም በባቢሎን ንጉሥ እጅ በሰጠሁ ጊዜ እርሱም በግብጽ ምድር ላይ በዘረጋው ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።
26 ፤ ግብጻውያንንም ወደ አሕዛብ እበትናለሁ ወደ አገሮችም እዘራቸዋለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።