ምዕራፍ 44

ወደ ምሥራቅም ወደሚመለከተው በስተ ውጭ ወዳለው ወደ መቅደሱ በር አመጣኝ፤ ተዘግቶም ነበር።
2 ፤ እግዚአብሔርም። ይህ በር ተዘግቶ ይኖራል እንጂ አይከፈትም፥ ሰውም አይገባበትም፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ገብቶበታልና ተዘግቶ ይኖራል።
3 ፤ አለቃው ግን እርሱ በእግዚአብሔር ፊት እንጀራ ይበላ ዘንድ ይቀመጥበታል፤ በበሩ ደጀ ሰላም መንገድ ይገባል በዚያም መንገድ ይወጣል።
4 ፤ በሰሜኑም በር መንገድ በቤቱ ፊት አመጣኝ፤ እኔም አየሁ፥ እነሆም፥ የእግዚአብሔር ክብር የእግዚአብሔርን ቤት ሞልቶት ነበር፤ እኔም በግምባሬ ተደፋሁ።
5 ፤ እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ። የሰው ልጅ ሆይ፥ ልብ አድርግ ስለ እግዚአብሔርም ቤት ሥርዓትና ሕግ ሁሉ የምናገርህን ሁሉ በዓይንህ ተመልከት በጆሮህም ስማ፤ የቤቱንም መግቢያ የመቅደሱንም መውጫ ሁሉ ልብ አድርግ።
6 ፤ ለዓመፀኛው ለእስራኤል ቤት እንዲህ በል። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እናንተ የእስራኤል ቤት ሆይ፥
7 ፤ እንጀራዬን፥ ስብንና ደምን፥ በምታቀርቡበት ጊዜ በመቅደሴ ውስጥ ይሆኑ ዘንድ ቤቴንም ያረክሱ ዘንድ በልባቸውና በሥጋቸው ያልተገረዙትን እንግዶችን ሰዎች አግብታችኋልና፥ እነርሱም በርኵሰታችሁ ሁሉ ላይ ይጨመሩ ዘንድ ቃል ኪዳኔን አፍርሰዋልና ርኵሰታችሁ ሁሉ ይብቃችሁ።
8 ፤ በመቅደሴ ውስጥ ለራሳችሁ ሥርዓቴን ጠባቂዎች አደረጋችሁ እንጂ የተቀደሰውን ነገሬን ሥርዓት አልጠበቃችሁም።
9 ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በእስራኤል ልጆች መካከል ካሉት ሁሉ በልቡና በሥጋው ያልተገረዘ እንግዳ ሁሉ ወደ መቅደሴ አይግባ።
10 ፤ ከእኔ ዘንድ የራቁ፥ እስራኤልም በሳቱ ጊዜ ጣዖታቸውን ተከትለው ከእኔ ዘንድ የሳቱ ሌዋውያን ኃጢአታቸውን ይሸከማሉ።
11 ፤ ነገር ግን በመቅደሴ ውስጥ አገልጋዮች ይሆናሉ፥ በቤቱም በሮች በረኞች ይሆናሉ በቤቱም ውስጥ ያገለግላሉ፤ ለሕዝቡም የሚቃጠለውን መሥዋዕትና ሌላ መሥዋዕቱን ያርዳሉ፥ ያገለግሉአቸውም ዘንድ በፊታቸው ይቆማሉ።
12 ፤ በጣዖቶቻቸውም ፊት አገልግለዋቸው ነበሩና፥ ለእስራኤልም ቤት የኃጢአት ዕንቅፋት ሆነዋልና ስለዚህ እጄን በላያቸው አንሥቻለሁ፥ ኃጢአታቸውንም ይሸከማሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
13 ፤ ካህናትም ይሆኑኝ ዘንድ ወደ እኔ አይቀርቡም፥ ወደ ተቀደሰውም ነገሬና ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ነገር አይቀርቡም፤ እፍረታቸውንና የሠሩትንም ርኵሰታቸውን ይሸከማሉ።
14 ፤ ነገር ግን ለአገልግሎቱ ሁሉና በእርሱ ውስጥ ለሚደረገው ሁሉ የቤቱን ሥርዓት ጠባቂዎች አደርጋቸዋለሁ።
15 ፤ ነገር ግን የእስራኤል ልጆች ከእኔ ዘንድ በሳቱ ጊዜ የመቅደሴን ሥርዓት የጠበቁ የሳዶቅ ልጆች ሌዋውያን ካህናት ያገለግሉኝ ዘንድ ወደ እኔ ይቀርባሉ፤ ስቡንና ደሙንም ወደ እኔ ያቀርቡ ዘንድ በፊቴ ይቆማሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
16 ፤ ወደ መቅደሴም ይገባሉ ያገለግሉኝም ዘንድ ወደ ገበታዬ ይቀርባሉ ሥርዓቴንም ይጠብቃሉ።
17 ፤ ወደ ውስጠኛውም አደባባይ በር በገቡ ጊዜ የተልባ እግር ልብስ ይልበሱ፤ በውስጠኛውም አደባባይ በርና በቤቱ ውስጥ ባገለገሉ ጊዜ ከበግ ጠጕር አንዳች ነገር በላያቸው አይሁን።
18 ፤ በራሳቸው ላይ የተልባ እግር መጠምጠሚያ ይሁን፥ በወገባቸውም ላይ የተልባ እግር ሱሪ ይሁን፤ የሚያወዛም ነገር አይታጠቁ።
19 ፤ ወደ ውጭውም አደባባይ ወደ ሕዝብ በወጡ ጊዜ ያገለገሉበትን ልብሳቸውን ያውልቁ በተቀደሰውም ዕቃ ቤት ውስጥ ያኑሩት፥ ሕዝቡንም በልብሳቸው እንዳይቀድሱ ሌላውን ልብስ ይልበሱ።
20 ፤ ራሳቸውንም አይላጩ የራሳቸውንም ጠጕር ይከርከሙ እንጂ ጠጕራቸውን አያሳድጉ።
21 ፤ ካህናቱም ሁሉ በውስጠኛው አደባባይ ሲገቡ የወይን ጠጅ አይጠጡ።
22 ፤ መበለቲቱንና የተፈታችይቱን አያግቡ፤ ከእስራኤል ቤት ዘር ግን ድንግሊቱን ወይም የካህን ሚስት የነበረችይቱን መበለት ያግቡ።
23 ፤ በተቀደሰውና ባልተቀደሰው መካከል ይለዩ ዘንድ ሕዝቤን ያስተምሩ፥ ንጹሕና ንጹሕ ባልሆነው መካከል ይለዩ ዘንድ ያሳዩአቸው።
24 ፤ ክርክርም በሆነ ጊዜ ለመፍረድ ይቁሙ፤ እንደ ፍርዴ ይፍረዱ፤ በበዓላቴ ሁሉ ሕጌንና ሥርዓቴን ይጠብቁ፥ ሰንበታቴንም ይቀድሱ።
25 ፤ እንዳይረክሱም ወደ ሞተ ሰው አይግቡ፤ ነገር ግን ለአባት ወይም ለእናት ወይም ለወንድ ልጅ ወይም ለሴት ልጅ ወይም ለወንድም ወይም ላልተዳረች እኅት ይርከሱ።
26 ፤ ከነጻም በኋላ ሰባት ቀን ይቈጠርለት።
27 ፤ በመቅደስም ውስጥ ያገለግል ዘንድ ወደ ውስጠኛው አደባባይ ወደ መቅደሱ በሚገባበት ቀን፥ የኃጢአትን መሥዋዕት ያቅርብ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
28 ፤ ርስት ይሆንላቸዋል፤ እኔ ርስታቸው ነኝ፤ በእስራኤልም ዘንድ ግዛት አትሰጡአቸው፤ እኔ ግዛታቸው ነኝ።
29 ፤ የእህሉን ቍርባንና የኃጢአትን መሥዋዕት የበደልንም መሥዋዕት ይበላሉ፤ በእስራኤልም ዘንድ እርም የሆነው ነገር ሁሉ ለእነርሱ ይሆናል።
30 ፤ የበኵራቱ ሁሉ መጀመሪያ ከየዓይነቱ ከቍርባናችሁም ሁሉ የማንሣት ቍርባን ሁሉ ለካህናት ይሆናል፤ በቤታችሁም ውስጥ በረከት ያድር ዘንድ የዱቄታችሁን በኵራት ለካህናቱ ትሰጣላችሁ።
31 ፤ የበከተውንና የተሰበረውን፥ ወፍ ወይም እንስሳ ቢሆን፥ ካህናት አይብሉት።