ምዕራፍ 16

የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
2 ፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ ለኢየሩሳሌም ርኵሰትዋን አስታውቃት፥
3 ፤ እንዲህም በል። ጌታ እግዚአብሔር ለኢየሩሳሌም እንዲህ ይላል። ዘርሽና ትውልድሽ ከከነዓን ምድር ነው፤ አባትሽ አሞራዊ ነበረ እናትሽም ኬጢያዊት ነበረች።
4 ፤ በተወለድሽ ጊዜ በዚያው ቀን እትብትሽ አልተቈረጠም ንጹሕም ትሆኚ ዘንድ በውኃ አልታጠብሽም፥ በጨውም አልተቀባሽም በጨርቅም አልተጠቀለልሽም።
5 ፤ በተወለድሽበት ቀን ከሰውነትሽ ጕስቍልና የተነሣ በሜዳ ላይ ተጣልሽ እንጂ ከዚህ አንዳች ይደረግልሽ ዘንድ ዓይን አልራራልሽም፥ ማንም አላዘነልሽም።
6 ፤ በአንቺም ዘንድ ባለፍሁ ጊዜ በደምሽም ውስጥ ተለውሰሽ ባየሁሽ ጊዜ። በደምሽ እንዳለሽ በሕይወት ኑሪ አልሁሽ፤ አዎን። በደምሽ እንዳለሽ በሕይወት ኑሪ አልሁሽ።
7 ፤ በእርሻ ላይ እንዳለ ቡቃያ አበዛሁሽ፥ አንቺም አደግሽ ታላቅም ሆንሽ፥ በእጅጉም አጌጥሽ፤ ጡቶችሽም አጐጠጐጡ ጠጕርሽም አደገ፥ ነገር ግን ዕርቃንሽን ሆንሽ፥ ተራቍተሽም ነበርሽ።
8 ፤ በአንቺ ዘንድ ባለፍሁና ባየሁሽ ጊዜ፥ እነሆ፥ ጊዜሽ የፍቅር ጊዜ ነበረ፤ እኔም መጐናጸፊያዬን በላይሽ ዘረጋሁ ኀፍረተ ሥጋሽንም ከደንሁ፤ ማልሁልሽም ከአንቺም ጋር ቃል ኪዳን ገባሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፥ አንቺም ለእኔ ሆንሽ።
9 ፤ በውኃም አጠብሁሽ ከደምሽም አጠራሁሽ በዘይትም ቀባሁሽ።
10 ፤ ወርቀ ዘቦም አለበስሁሽ በአቆስጣ ቁርበትም ጫማ አደረግሁልሽ፤ በጥሩ በፍታ አስታጠቅሁሽ በሐርም ከደንሁሽ።
11 ፤ በጌጥም አስጌጥሁሽ በእጅሽም ላይ አንባር በአንገትሽም ላይ ድሪ አደረግሁልሽ።
12 ፤ በአፍንጫሽም ቀለበት በጆሮሽም ጕትቻ በራስሽም ላይ የክብር አክሊል አደረግሁ።
13 ፤ በወርቅና በብር አጌጥሽ፥ ልብስሽም ጥሩ በፍታና ሐር ወርቀ ዘቦም ነበረ፤ አንቺም መልካምን ዱቄትና ማርን ዘይትንም በላሽ፤ እጅግ በጣም ውብ ሆንሽ ለመንግሥትም ደረስሽ።
14 ፤ ባንቺ ላይ ካኖርኋት ከክብሬ የተነሣ ውበትሽ ፍጹም ነበረና ዝናሽ በአሕዛብ መካከል ወጣ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
15 ፤ ነገር ግን በውበትሽ ታምነሻል ስለ ዝናሽም አመንዝረሻል ምንዝርናሽንም ከመንገድ አላፊ ሁሉ ጋር አበዛሽ።
16 ፤ ከልብስሽም ወስደሽ በኮረብቶች ላይ በዝንጕርጕር ልብስ ያስጌጥሻቸውን መስገጆች ለራስሽ ሠራሽ በዚያም ገለሞትሽ፤ እንዲህም ያለ ነገር ከአሁን በፊት አልነበረም፥ ከእንግዲህም ወዲያ አይሆንም።
17 ፤ ከሰጠሁሽም ከወርቄና ከብሬ የተሠራውን የክብርሽን ዕቃ ወስደሽ የወንድ ምስሎች ለራስሽ አድርገሻል አመንዝረሽባቸውማል።
18 ፤ ወርቀዘቦውን ልብስሽንም ወስደሽ ደረብሽላቸው፥ ዘይቴንና ዕጣኔንም በፊታቸው አኖርሽ።
19 ፤ የሰጠሁሽንም እንጀራዬን ያበላሁሽንም መልካሙን ዱቄትና ዘይቱን ማሩንም ጣፋጭ ሽታ አድርገሽ በፊታቸው አኖርሽ፥ እንዲሁም ሆኖአል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
20 ፤ ለእኔም የወለድሻቸውን ወንዶችና ሴቶች ልጆችሽን ወስደሽ መብል ይሆኑ ዘንድ ሠዋሽላቸው።
21 ፤ ልጆቼን አረድሽ፤ ለእነርሱም በእሳት በኩል አሳልፈሽ ሰጠሽ፤ በውኑ ግልሙትናሽ ጥቂት ነውን?
22 ፤ በርኵስነትሽና በግልሙትናሽ ሁሉ ዕርቃንሽን ሆነሽ ተራቍተሽም ሳለሽ በደምሽም ተለውሰሽ ሳለሽ የሕፃንነትሽን ወራት አላሰብሽም።
23 ፤ ወዮ! ወዮልሽ! ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤
24 ፤ ከክፋትሽም ሁሉ በኋላ የምንዝርናን ስፍራ፥ በየአደባባዩም ከፍ ያለ ቦታን ለራስሽ ሠራሽ።
25 ፤ በየመንገዱ ራስ ከፍ ያለውን ቦታሽን ሠራሽ፥ ውበትሽንም አረከስሽ፥ ለመንገድ አላፊም ሁሉ እግርሽን ገለጥሽ ግልሙትናሽንም አበዛሽ።
26 ፤ ሥጋቸውም ከወፈረ ከጐረቤቶችሽ ከግብጻውያን ጋር አመነዘርሽ፥ እኔንም ታስቈጭ ዘንድ ግልሙትናሽን አበዛሽ።
27 ፤ ስለዚህ፥ እነሆ፥ እጄን በአንቺ ላይ ዘርግቻለሁ ድርጐሽንም አጕድያለሁ፤ ለሚጠሉሽም ከክፉ መንገድሽ የተነሣ ለሚያፍሩ ለፍልስጥኤም ሴቶች ልጆች ፈቃድ አሳልፌ ሰጥቼሻለሁ።
28 ፤ አልጠገብሽምና ከአሦራውያን ጋር ደግሞ ገለሞትሽ ከዚህም ጋር ገና አልጠገብሽም።
29 ፤ እስከ ነጋዴዎች ምድር እስከ ከላውዴዎን ድረስ ግልሙትናሽን አበዛሽ። ከዚህም ጋር ገና አልጠገብሽም።
30 ፤ የማታፍረውን የጋለሞታን ሥራ ሁሉ ሠርተሻልና ልብሽ ምንኛ ደካማ ነው? ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
31 ፤ በየመንገዱ ራስ የምንዝርናሽን ስፍራ ሠርተሻል በየአደባባዩም ከፍ ያለውን ቦታሽን አድርገሻል። ዋጋዋን እንደምትንቅ እንደ ጋለሞታ አልሆንሽም።
32 ፤ በባልዋ ፋንታ ሌሎችን ተቀብላ የምታመነዝር ሴትን ትመስያለሽ።
33 ፤ ለጋለሞቶች ሁሉ ዋጋ ይሰጡአቸዋል፤ አንቺ ግን ለውሽሞችሽ ሁሉ ዋጋ ትሰጫለሽ፥ ከአንቺም ጋር ለማመንዘር በዙሪያሽ ይገቡብሽ ዘንድ መማለጃ ትሰጫቸዋለሽ።
34 ፤ ግልሙትናሽ ከሌሎች ሴቶች ግልብጥ ነው፤ ማንም ለግልሙትና የሚከተልሽ የለም፤ ዋጋ ሳይሰጥሽ አንቺ ዋጋ በመስጠትሽ በዚህ ነገር ልዩ ሆነሻል።
35 ፤ ስለዚህ፥ ጋለሞታ ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሚ።
36 ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ከውሽሞችሽ ጋር ባደረግሽው በግልሙትናሽ ርኵሰትሽ ስለ ፈሰሰ ኀፍረተ ሥጋሽም ስለ ተገለጠ፥ ስለ ርኵሰትሽም ጣዖታት ሁሉ ስለ ሰጠሻቸውም ስለ ልጆች ደም፥
37 ፤ ስለዚህ፥ እነሆ፥ ከእነርሱ ጋር ደስ ያለሽን የወደድሻቸውንም ውሽሞችሽ ሁሉ ከጠላሻቸው ሁሉ ጋር እሰበስባቸዋለሁ፤ በአንቺ ላይ በዙሪያሽ እሰበስባቸዋለሁ፥ ኀፍረተ ሥጋሽንም ሁሉ እንዲያዩ በፊታቸው ኀፍረተ ሥጋሽን እገልጣለሁ።
38 ፤ በአመንዝሮችና በደም አፍሳሾች ላይ የሚፈረደውን ፍርድ እፈርድብሻለሁ፥ የመዓትንና የቅንዓትን ደምም አመጣብሻለሁ።
39 ፤ በእጃቸውም አሳልፌ እሰጥሻለሁ፥ የምንዝርናሽንም ስፍራ ያፈርሳሉ ከፍ ያለውንም ቦታሽን ይገለብጣሉ፤ ልብስሽንም ይገፉሻል የክብርሽንም ጌጥ ይወስዳሉ፥ ዕርቃንሽን አድርገው ዕራቁትሽን ይተዉሻል።
40 ፤ ጉባኤን ያመጡብሻል በድንጋይም ይወግሩሻል፥ በሰይፋቸውም ይወጉሻል።
41 ፤ ቤቶችሽንም በእሳት ያቃጥላሉ በብዙም ሴቶች ፊት በላይሽ ፍርድን ያደርጉብሻል፤ ግልሙትናሽንም አስተውሻለሁ፥ እንግዲህስ ዋጋ አትሰጭም።
42 ፤ መዓቴንም በአንቺ ላይ እጨርሳለሁ ቅንዓቴም ከአንቺ ይርቃል፥ እኔም ዝም እላለሁ ደግሞም አልቈጣም።
43 ፤ የሕፃንነትሽን ወራት አላሰብሽምና፥ በዚህም ነገር ሁሉ አስቈጥተሽኛልና ስለዚህ፥ እነሆ፥ እኔ ደግሞ መንገድሽን በራስሽ ላይ አመጣለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፥ ሌላንም ነውር በርኵሰትሽ ሁሉ ላይ አትጨምሪም።
44 ፤ እነሆ፥ በምሳሌ የሚናገር ሁሉ። እንደ እናቲቱ እንዲሁ ሴት ልጂቱ ናት እያለ ምሳሌ ይመስልብሻል።
45 ፤ አንቺ ባልዋንና ልጆችዋን የጠላሽ የእናትሽ ልጅ ነሽ፤ አንቺም ባሎቻቸውንና ልጆቻቸውን የጠሉ የእኅቶችሽ እኅት ነሽ፤ እናታችሁ ኬጢያዊት ነበረች አባታችሁም አሞራዊ ነበረ።
46 ፤ ታላቂቱም እኅትሽ ከሴቶች ልጆችዋ ጋር በስተ ግራሽ የምትቀመጥ ሰማርያ ናት፤ ታናሺቱም እኅትሽ ከሴቶች ልጆችዋ ጋር በስተ ቀኝሽ የምትቀመጥ ሰዶም ናት።
47 ፤ አንቺ ግን በመንገዳቸው አልሄድሽም እንደ ርኵሰታቸውም አላደረግሽም ያው ለአንቺ ጥቂት ነበረና በመንገድሽ ሁሉ ከእነርሱ የሚከፋ ርኵሰት አደረግሽ።
48 ፤ እኔ ሕያው ነኝና አንቺና ሴቶች ልጆችሽ እንዳደረጋችሁት እንዲሁ ሰዶምና ሴቶች ልጆችዋ አላደረጉም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
49 ፤ እነሆ፥ የእኅትሽ የሰዶም ኃጢአት ይህ ነበረ፤ ትዕቢት እንጀራን መጥገብ መዝለልና ሥራ መፍታት በእርስዋና በሴቶች ልጆችዋ ነበረ፥ የችግረኛውንና የድሀውንም እጅ አላጸናችም።
50 ፤ ኰርተው ነበር በፊቴም ርኩስ ነገር አደረጉ፤ ስለዚህ ባየሁ ጊዜ አጠፋኋቸው።
51 ፤ ሰማርያም የኃጢአትሽን እኵሌታ አልሠራችም፤ አንቺ ግን ከእኅቶችሽ ይልቅ ርኵሰትሽን አበዛሽ፥ በሥራሽም ርኵሰት ሁሉ አጸደቅሻቸው።
52 ፤ አሁንም ለእኅቶችሽ ስለ ፈረድሽ እፍረትሽን ተሸከሚ፤ ከእነርሱ የባሰ ኃጢአት ሠርተሻልና ከአንቺ ይልቅ ጻድቃን ናቸው፤ እኅቶችሽንም ስለ አጸደቅሻቸው እፈሪ እፍረትሽንም ተሸከሚ።
53 ፤ ምርኮአቸውን፥ የሰዶምና የሴቶች ልጆችዋን ምርኮ፥ የሰማርያንና የሴቶች ልጆችዋንም ምርኮ፥ በመካከላቸውም ያሉትን የምርኮኞችሽን ምርኮ እመልሳለሁ፤
54 ፤ ስለ አጽናናሻቸው፥ እፍረትን ትሸከሚ ዘንድ ስለ አደረግሽውም ሁሉ ታፍሪ ዘንድ።
55 ፤ እኅቶችሽም ሰዶምና ሴቶች ልጆችዋ ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው ይመለሳሉ፥ ሰማርያና ሴቶች ልጆችዋም ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው ይመለሳሉ፥ አንቺና ሴቶች ልጆችሽም ወደ ቀድሞ ሁኔታችሁ ትመለሳላችሁ።
56 ፤ ክፋትሽ ሳይገለጥ በትዕቢትሽ ቀን እኅትሽ ሰዶም በአፍሽ መተረቻ አልነበረችምን?
57 ፤ አሁን ለሶርያ ሴቶች ልጆችና ለጎረቤቶችዋ ሁሉ፥ በዙሪያሽም ለሚንቁሽ ለፍልስጥኤም ሴቶች ልጆች እንደ እርስዋ መሰደቢያ ሆነሻል።
58 ፤ ምንዝርነትሽንና ርኵስነትሽን ተሸክመሻል፥ ይላል እግዚአብሔር።
59 ፤ ጌታ እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል። አንቺ ቃል ኪዳንን በማፍረስ መሐላን የናቅሽ ሆይ፥ አንቺ እንዳደረግሽ እኔ ደግሞ አደርግብሻለሁ።
60 ፤ ነገር ግን በሕፃንነትሽ ወራት ከአንቺ ጋር ያደረግሁትን ቃል ኪዳኔን አስባለሁ የዘላለምንም ቃል ኪዳን አጸናልሻለሁ።
61 ፤ እኅቶችሽንም ታላቂቱንና ታናሺቱን በተቀበልሽ ጊዜ መንገድሽን ታስቢያለሽ ታፍሪማለሽ፤ ለአንቺም ልጆች ይሆኑ ዘንድ እሰጣቸዋለሁ፥ ስለ ቃል ኪዳንሽ ግን አይደለም።
62
63 ፤ ስላደረግሽውም ሁሉ ይቅር ባልሁሽ ጊዜ፥ ታስቢ ዘንድ ታፍሪም ዘንድ ስለ እፍረትሽም ደግሞ አፍሽን እንዳትከፍቺ፥ ቃል ኪዳኔን ከአንቺ ጋር አጸናለሁ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቂያለሽ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።