ምዕራፍ 19

አንተም በእስራኤል አለቆች ላይ ይህን ሙሾ አሙሽ፥ እንዲህም በል።
2 ፤ እናትህ ምን ነበረች? አንበሳ ነበረች፤ በአንበሶች መካከል ተጋደመች፤ በደቦል አንበሶች መካከል ግልገሎችዋን አሳደገች።
3 ፤ ከግልገሎችዋም አንዱን አወጣች እርሱም ደቦል አንበሳ ሆነ፤ ንጥቂያንም ተማረ፥ ሰዎችንም በላ።
4 ፤ አሕዛብም ወሬውን ሰሙ እርሱም በጕድጓዳቸው ተያዘ፥ በሰንሰለትም አድርገው ወደ ግብጽ ምድር ወሰዱት።
5 ፤ እርስዋም እንደ ደከመችና ተስፋዋ እንደ ጠፋ ባየች ጊዜ፥ ከግልገሎችዋ ሌላን ወስዳ ደቦል አንበሳ አደረገችው።
6 ፤ እርሱም በአንበሶች መካከል ተመላለሰ ደቦል አንበሳም ሆነ፤ ንጥቂያም ተማረ፥ ሰዎችንም በላ።
7 ፤ ግንቦቻቸውንም አወቀ፥ ከተሞቻቸውንም አፈረሰ፤ ከግሣቱም ድምፅ የተነሣ ምድሪቱና ሞላዋ ጠፋች።
8 ፤ አሕዛብም በዙሪያው ከየአገሩ ሁሉ ተሰበሰቡበት፤ መረባቸውንም በእርሱ ላይ ዘረጉ በጕድጓዳቸውም ተያዘ።
9 ፤ በሰንሰለትም አድርገው በቀፎ ውስጥ አኖሩት ወደ ባቢሎንም ንጉሥ አመጡት፤ ድምፁም በእስራኤል ተራሮች ላይ ከዚያ ወዲያ እንዳይሰማ ወደ አምባ አገቡት።
10 ፤ እናትህ በመልክህ በውኃ አጠገብ እንደ ተተከለች እንደ ወይን ግንድ ነበረች፤ ከውኃም ብዛት የተነሣ የምታፈራና የምትሰፋ ሆነች።
11 ፤ ለእርስዋም ብርቱዎች በትሮች ነበሩአት እነርሱም ለነገሥታት በትሮች ነበሩ። ቁመታቸውም በዛፎች ቅርንጫፎች መካከል ረዘመ፥ በጫፎቻቸውም ብዛትና በርዝመታቸው ታዩ።
12 ፤ ነገር ግን በመዓት ተነቀለች ወደ መሬትም ተጣለች የምሥራቅም ነፋስ ፍሬዋን አደረቀ፤ ብርቱዎች በትሮችዋም ተሰበሩና ደረቁ፥ እሳትም በላቻቸው።
13 ፤ አሁንም በምድረ በዳ፥ በደረቅና በተጠማች መሬት ተተከለች።
14 ፤ ከጫፎችዋም በትሮች እሳት ወጣች ፍሬዋንም በላች፥ የነገሥታትም በትር ይሆን ዘንድ የበረታ በትር የለባትም። ይህ ሙሾ ነው፥ ለልቅሶም ይሆናል።