ምዕራፍ 23

የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
2 ፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ የአንዲት እናት ልጆች የሆኑ ሁለት ሴቶች ነበሩ።
3 ፤ በግብጽም አመነዘሩ፥ በኰረዳነታቸው አመነዘሩ፤ በዚያ ጡቶቻቸው ምዋሸሹ በዚያም የድንግልናቸውን ጡቶች ዳበሱ።
4 ፤ ስማቸውም የታላቂቱ ኦሖላ የእኅትዋም ኦሖሊባ ነበረ፥ ለእኔም ሆኑ ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለዱ። ስማቸውም ኦሖላ ሰማርያ ናት፤ ኦሖሊባ ደግሞ ኢየሩሳሌም ናት።
5 ፤ ኦሖላም ገለሞተችብኝ፥ ውሽሞችዋንም ጎረቤቶችዋን አሦራውያንን በፍቅር ተከተለቻቸው።
6 ፤ እነርሱም ሰማያዊ ሐር የለበሱ አለቆችና ሹማምቶች፥ መልከ መልካሞች ጐበዛዝት፥ በፈረስ ላይ የሚቀመጡ ፈረሰኞች ነበሩ።
7 ፤ ግልሙትናዋንም ከተመረጡ ከአሦር ሰዎች ሁሉ ጋር አደረገች፥ በፍቅር በተከተለቻቸውም ጣዖቶቻቸው ሁሉ ረከሰች።
8 ፤ በግብጽም የነበረውን ግልሙትናዋን አልተወችም፤ በዚያ በኰረዳነትዋ ጊዜ ከእርስዋ ጋር ተኝተው ነበር፥ የድንግልናዋንም ጡቶች ዳብሰው ነበር፥ ግልሙትናቸውንም አፍስሰውባት ነበር።
9 ፤ ስለዚህ በፍቅር በተከተለቻቸው በውሽሞችዋ በአሦራውያን እጅ አሳልፌ ሰጠኋት።
10 ፤ እነርሱም ኅፍረተ ሥጋዋን ገለጡ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆችዋንም ማርከው ወሰዱ፥ እርስዋንም በሰይፍ ገደሉ፤ ፍርድንም ስላደረጉባት በሴቶች መካከል መተረቻ ሆነች።
11 ፤ እኅትዋም ኦሖሊባ ይህን አየች፤ ሆኖም ከእርስዋ ይልቅ በፍቅር በመከተልዋ ረከሰች፥ ግልሙትናዋም ከእኅትዋ ግልሙትና ይልቅ በዛ።
12 ፤ አለቆችንና ሹማምቶችን ጎረቤቶችዋን ጌጠኛ ልብስ የለበሱትን በፈረሶች ላይ የሚቀመጡትን ፈረሰኞች፥ ሁሉም መልከ መልካሞችን ጐበዛዝት አሦራውያንን በፍቅር ተከተለቻቸው።
13 ፤ የረከሰችም እንደ ሆነች አየሁ፥ ሁለቱም አንድ መንገድ ሄደዋል።
14 ፤ ግልሙትናዋንም አበዛች፤ በቀይ ቀለምም የተሳለችውን የከለዳውያንን ስዕል፥ በናስ ላይ የተሳሉትን ሰዎች አየች።
15 ፤ በወገባቸው ዝናር የታጠቁ ራሳቸውንም በቀለማዊ መጠምጠሚያ የጠመጠሙ ነበሩ፤ ሁሉም ከተወለዱባት አገር የሆኑትን የከለዳውያንን ልጆች መስለው መሳፍንትን ይመስሉ ነበር።
16 ፤ ባየቻቸውም ጊዜ በፍቅር ተከተለቻቸው፥ ወደ ከላውዴዎን ምድር ወደ እነርሱ መልእክተኞችን ላከች።
17 ፤ የባቢሎንም ሰዎች ወደ እርስዋ ፍቅር ወዳለበት መኝታ መጡ በግልሙትናቸውም አረከሱአት፤ እርስዋም ከእነርሱ ጋር ረከሰች ነፍስዋም ከእነርሱ ተለየች።
18 ፤ ግልሙትናዋንም ገለጠች ኅፍረተ ሥጋዋንም አሳየች፤ ነፍሴም ከእኅትዋ እንደ ተለየች እንዲሁ ነፍሴ ከእርስዋ ተለየች።
19 ፤ ነገር ግን በግብጽ ምድር የገለሞተችበትን የኰረዳነትዋን ዘመን አስባ ግልሙትናዋን አበዛች።
20 ፤ ሥጋቸውም እንደ አህዮች ሥጋ ዘራቸውም እንደ ፈረሶች ዘር የሆነውን እነዚያን ምልምሎች በፍቅር ተከተለቻቸው።
21 ፤ ስለ ኰረዳነትሽ ምክንያት ግብጻውያን ጡቶችሽን በዳበሱ ጊዜ የኰረዳነትሽን ሴሰኝነት አሰብሽ።
22 ፤ ስለዚህ፥ ኦሖሊባ ሆይ፥ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ነፍስሽ ከእነርሱ የተለየች ውሽሞችሽን አስነሣብሻለሁ፥ በዙሪያሽም በአንቺ ላይ አመጣቸዋለሁ።
23 ፤ እነርሱም የባቢሎን ሰዎች ከለዳውያንም ሁሉ፥ ፋቁድ፥ ሱሔ፥ ቆዓ፥ ከእነርሱም ጋር አሦራውያን ሁሉ፥ መልከ መልካሞች ጐበዛዝት፥ አለቆችና ሹማምቶች ሁሉ፥ መሳፍንቶችና አማካሪዎች ሁሉ፥ በፈረስ ላይ የተቀመጡ ናቸው።
24 ፤ በመሣሪያና በሰረገላ በመንኰራኵርም በአሕዛብም ጉባኤ ይመጡብሻል፤ ጋሻና አላባሽ ጋሻ ራስ ቍርም ይዘው በዙሪያሽ ይዘጋጁብሻል፤ ፍርድንም እሰጣቸዋለሁ፥ እንደ ፍርዳቸውም ይፈርዱብሻል።
25 ፤ ቅንዓቴንም በአንቺ ላይ አደርጋለሁ በመዓትም ያደርጉብሻል፤ አፍንጫሽንና ጆሮሽንም ከአንቺ ይቈርጣሉ፥ ከአንቺም የቀረ በሰይፍ ይወድቃል፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆችሽንም ማርከው ይወስዳሉ፥ ከአንቺም የቀረውን እሳት ትበላቸዋለች።
26 ፤ ልብስሽንም ይገፍፉሻል የክብርሽንም ጌጥ ይወስዳሉ።
27 ፤ ሴሰኝነትሽንም፥ ከግብጽ ምድር ያወጣሽውን ግልሙትናሽንም ከአንቺ አስቀራለሁ፤ ዓይንሽንም ወደ እነርሱ አታነሺም ግብጽንም ከዚያ ወዲያ አታስቢም።
28 ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። እነሆ፥ በጠላሻቸው እጅ፥ ነፍስሽ በተለየቻቸው እጅ አሳልፌ እሰጥሻለሁ፤
29 ፤ እነርሱም በጥል ያደርጉብሻል፥ የደከምሽበትንም ሁሉ ይወስዳሉ፥ ዕራቁትሽንና ዕርቃንሽን አድርገውም ይተዉሻል፤ የግልሙትናሽም ነውር፥ ሴሰኝነትሽና ግልሙትናሽም ሁሉ ይገለጣል።
30 ፤ ከአሕዛብ ጋር ስላመነዘርሽ በጣዖቶቻቸውም ስለ ረከስሽ ይህን ያደረጉብሻል።
31 ፤ በእኅትሽ መንገድ ሄደሻል፤ ስለዚህ ጽዋዋን በእጅሽ እሰጥሻለሁ።
32 ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የጠለቀውንና የሰፋውን ብዙም የሚይዘውን የእኅትሽን ጽዋ ትጠጪአለሽ፤ መሳቂያና መሳለቂያም ትሆኛለሽ።
33 ፤ በእኅትሽ በሰማርያ ጽዋ፥ በድንጋጤና በጥፋት ጽዋ፥ በስካርና በውርደት ትሞልያለሽ።
34 ፤ ትጠጪዋለሽ ትጨልጪውማለሽ ገሉንም ታኝኪዋለሽ ጡትሽንም ትሸነትሪዋለሽ፤ እኔ ተናግሬአለሁና፥ ይላል እግዚአብሔር።
35 ፤ ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ዘንግተሽኛልና፥ ወደ ኋላሽም ጥለሽኛልና አንቺ ደግሞ ሴሰኝነትሽንና ግልሙትናሽን ተሸከሚ።
36 ፤ እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ። የሰው ልጅ ሆይ፥ በኦሖላና በኦሖሊባ ትፈርዳለህን? ኃጢአታቸውንም ታስታውቃቸዋለህ?
37 ፤ አመንዝረዋልና፥ ደምም በእጃቸው አለና፥ ከጣዖቶቻቸውም ጋር አመንዝረዋልና፥ ለእኔም የወለዱአቸውን ልጆቻቸውን መብል እንዲሆኑላቸው በእሳት አሳልፈዋቸዋልና።
38 ፤ ይህን ደግሞ አድርገውብኛል፤ በዚያ ቀን መቅደሴን አርክሰዋል ሰንበታቴንም ሽረዋል።
39 ፤ ልጆቻቸውንም ለጣዖቶቻቸው በሠዉ ጊዜ፥ በዚያው ቀን ያረክሱት ዘንድ ወደ መቅደሴ ገቡ፤ እነሆም፥ በቤቴ ውስጥ እንደዚህ አደረጉ።
40 ፤ ደግሞ መልእክተኛ ወደ ተላከባቸው ከሩቅም ወደሚመጡ ሰዎች ልካችኋል፤ እነሆም መጡ፥ አንቺም ታጠብሽላቸው ዓይኖችሽንም ተኳልሽ ጌጥም አጌጥሽ፤
41 ፤ በክብር አልጋ ላይ ተቀመጥሽ፥ በፊት ለፊትዋም ማዕድ ተዘጋጅታ ነበር፥ ዕጣኔንና ዘይቴንም አኖርሽባት።
42 ፤ የደስተኞችም ድምፅ በእርስዋ ዘንድ ነበረ፤ ከብዙም ሰዎች ጉባኤ ጋር ሰካራሞቹ ከምድረ በዳ መጡ፤ በእጃቸው አንበር በራሳቸውም የተዋበ አክሊል አደረጉ።
43 ፤ እኔም በምንዝር ላረጀችው። አሁን ከእርስዋ ጋር ያመነዝራሉ እርስዋም ከእነርሱ ጋር ታመነዝራለች አልሁ።
44 ፤ ወደ ጋለሞታም እንደሚገቡ ወደ እርስዋ ገቡ፤ እንዲሁ ይሰስኑ ዘንድ ወደ ኦሖላና ወደ ኦሖሊባ ገቡ።
45 ፤ ሴቶቹ አመንዝሮች ናቸውና፥ በእጃቸውም ደም አለና ጻጽቃን ሰዎች በአመንዝሮቹና በደም አፍሳሾቹ ሴቶች ላይ በሚፈረደው ፍርድ ይፈርዱባቸዋል።
46 ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ጉባኤን አመጣባቸዋለሁ፥ ለመበተንና ለመበዝበዝም አሳልፌ አሰጣቸዋለሁ።
47 ፤ ጉባኤውም በድንጋይ ይወግሩአቸዋል በሰይፋቸውም ይቈርጡአቸዋል፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውንም ይገድላሉ፥ ቤቶቻቸውንም በእሳት ያቃጥላሉ።
48 ፤ ሴቶችም ሁሉ እንደ ሴሰኝነታችሁ እንዳይሠሩ ይማሩ ዘንድ ሴሰኝነትን ከምድር ላይ አጠፋለሁ።
49 ፤ ሴሰኝነታችሁንም በላያችሁ ላይ ይመልሳሉ፥ እናንተም የጣዖቶቻችሁን ኃጢአት ትሸከማላችሁ፤ እኔም ጌታ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።