ትንቢተ ሕዝቅኤል
ምዕራፍ 13
የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
2 ፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ ትንቢት በሚናገሩ በእስራኤል ነቢያት ላይ ትንቢት ተናገር፥ ከገዛ ልባቸውም ትንቢት የሚናገሩትን። የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ በላቸው፤
3 ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ምንምን ሳያዩ የገዛ መንፈሳቸውን ለሚከተሉ ለሰነፎች ነቢያት ወዮላቸው!
4 ፤ እስራኤል ሆይ፥ ነቢያትህ በምድረ በዳ እንደሚኖሩ ቀበሮች ናቸው።
5 ፤ ወደ ተሰበረው ቅጥር አልወጣችሁም፥ በእግዚአብሔርም ቀን በሰልፍ ትቆሙ ዘንድ ለእስራኤል ቤት ቅጥር አልሠራችሁም።
6 ፤ እግዚአብሔር ሳይልካቸው። እግዚአብሔር ይላል የሚሉ ሰዎች ከንቱ ነገርንና ውሸተኛ ምዋርትን አይተዋል፤ ቃሉም ይጠና ዘንድ ተስፋ አስደርገዋል።
7 ፤ እኔም ሳልናገር። እግዚአብሔር እንዲህ ብሎአል ስትሉ፥ ከንቱ ራእይን ያያችሁ ውሸተኛንም ምዋርት የተናገራችሁ አይደላችሁምን?
8 ፤ ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ከንቱ ነገርን ስለ ተናገራችሁ ውሸተኛ ራእይንም ስላያችሁ፥ ስለዚህ፥ እነሆ፥ እኔ በእናንተ ላይ ነኝ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
9 ፤ እጄም ከንቱ ራእይን በሚያዩ፥ በውሸትም በሚያምዋርቱ ነቢያት ላይ ትሆናለች፤ እነርሱም በሕዝቤ ማኅበር ውስጥ አይገኙም፥ በእስራኤልም ቤት መጽሐፍ አይጻፉም፥ ወደ እስራኤልም ምድር አይገቡም፤ እኔም ጌታ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።
10 ፤ ሰላም ሳይኖር። ሰላም እያሉ ሕዝቤን አታልለዋልና፤ አንዱም ሰው ቅጥር ሲሠራ፥ እነሆ፥ ገለባ በሌለበት ጭቃ ይመርጉታልና
11 ፤ ገለባ በሌለበት ጭቃ ለሚመርጉት ሰዎች። ይወድቃል በላቸው። የሚያሰጥም ዝናብ ይዘንባል፥ ታላቅም የበረዶ ድንጋይ ይወድቃል፥ ዐውሎ ነፋስም ይሰነጣጥቀዋል።
12 ፤ እነሆ፥ ግንቡ በወደቀ ጊዜ። የመረጋችሁት ጭቃ ወዴት አለ? አይሉአችሁምን?
13 ፤ ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በመዓቴ በዐውሎ ነፋስ እሰነጣጥቀዋለሁ፥ ያጠፋውም ዘንድ በቍጣዬ የሚያሰጥም ዝናብ፥ በመዓቴም ታላቅ የበረዶ ድንጋይ ይወርዳል።
14 ፤ ገለባም በሌለበት ጭቃ የመረጋችሁትን ቅጥር አፈርሳለሁ ወደ ምድርም እጥለዋለሁ፥ መሠረቱም ይታያል። እርሱም ይናዳል በመካከሉም ትጠፋላችሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።
15 ፤ መዓቴንም በግንቡ ላይ ገለባም በሌለበት ጭቃ በመረጉት ላይ እፈጽማለሁ፤ እኔም። ግንቡና መራጊዎቹ የሉም እላችኋለሁ።
16 ፤ እነርሱም ስለ ኢየሩሳሌም ትንቢት የሚናገሩ የሰላምን ራእይ የሚያዩላት የእስራኤል ነቢያት ናቸው፥ ሰላምም የለም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
17 ፤ አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ ከገዛ ልባቸው ትንቢት በሚናገሩ በሕዝብህ ሴቶች ልጆች ላይ ፊትህን አድርግ፤ ትንቢትም ተናገርባቸው፥
18 ፤ እንዲህም በል። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ነፍስን ለማጥመድ ለእጅ ድጋፍ ሁሉ መከዳ ለሚሰፉ ለሰውም ሁሉ ራስ እንደ እየቁመቱ ሽፋን ለሚሠሩ ሴቶች ወዮላቸው! የሕዝቤንም ነፍስ ብታጠምዱ በውኑ ነፍሳችሁን ታድናላችሁን?
19 ፤ ውሸታችሁን ለሚሰሙት ሕዝቤ እየዋሻችሁ ሞት የማይገባቸውን ነፍሳት ትገድሉ ዘንድ በሕይወትም መኖር የማይገባቸውን ነፍሳት በሕይወት ታኖሩ ዘንድ ስለ ጭብጥ ገብስና ስለ ቍራሽ እንጀራ በሕዝቤ ዘንድ አርክሳችሁኛል።
20 ፤ ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ እኔ ነፍሳትን እንደ ወፍ በምታጠምዱባት በመከዳችሁ ላይ ነኝ፥ ከክንዳችሁም ወስጄ እቀድዳታለሁ፥ እንደ ወፍም የምታጠምዱአቸውን ነፍሳት እለቅቃለሁ።
21 ፤ ሽፋኖቻችሁን ደግሞ እቀድዳለሁ ሕዝቤንም ከእጃችሁ አድናለሁ፥ ከዚያም ወዲያ በእጃችሁ ለመታደን አይሆኑም፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።
22 ፤ እኔም ያላሳዘንሁትን የጻድቁን ልብ በውሸት አሳዝናችኋልና፥ በሕይወትም ይኖር ዘንድ ከክፉ መንገድ እንዳይመለስ የኃጢአተኛውን እጅ አበርትታችኋልና
23 ፤ ስለዚህ ከንቱን ራእይ እንግዲህ አታዩም ምዋርትንም አታምዋርቱም፥ ሕዝቤንም ከእጃችሁ አድናለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።