ምዕራፍ 3

እርሱም። የሰው ልጅ ሆይ፥ ያገኘኸውን ብላ፤ ይህን መጽሐፍ ብላ፥ ሄደህም ለእስራኤል ቤት ተናገር አለኝ።
2 ፤ አፌንም ከፈትሁ መጽሐፉንም አጐረሰኝ።
3 ፤ እርሱም። የሰው ልጅ ሆይ፥ አፍህ ይብላ፥ በምሰጥህም በዚህ መጽሐፍ ሆድህን ሙላ አለኝ። እኔም በላሁት፥ በአፌም ውስጥ እንደ ማር ጣፈጠ።
4 ፤ እንዲህም አለኝ። የሰው ልጅ ሆይ፥ ተነሥተህ ወደ እስራኤል ቤት ሂድ፥ ቃሌንም ተናገራቸው።
5 ፤ ወደ እስራኤል ቤት እንጂ ንግግራቸው ወደ ጠለቀው ቋንቋቸውም ወደማይታወቅ ሕዝብ አልተላክህምና፤
6 ፤ ንግግራቸው ወደ ጠለቀው ቋንቋቸውም ወደማይታወቅ ቃላቸውንም ታውቅ ዘንድ ወደማይቻልህ ሕዝብ አልላክሁህም። ወደ እነዚያስ ልኬህ ቢሆን ኖሮ በሰሙህ ነበር።
7 ፤ ነገር ግን የእስራኤል ቤት ሁሉ የጠነከረ ግምባርና የደነደነ ልብ አላቸውና፥ እኔንም መስማት እንቢ ብለዋልና የእስራኤል ቤት አንተን አይሰሙም።
8 ፤ እነሆ፥ ፊትህን በፊታቸው ግምባርህንም በግምባራቸው አጠንክሬአለሁ።
9 ፤ ከቡላድ ድንጋይ ይልቅ እንዳለ አልማዝ ግምባርህን አጠንክሬአለሁ፤ እነርሱ ዓመፀኛ ቤት ቢሆኑ አትፍራቸው፤ ከፊታቸውም የተነሣ አትደንግጥ።
10 ፤ እርሱም። የሰው ልጅ ሆይ፥ የነገርሁህን ቃሌን ሁሉ በልብህ ተቀበል በጆሮህም ስማ።
11 ፤ ተነሥተህም ወደ ተማረኩ ወደ ወገንህ ልጆች ሂድ፤ እነርሱም ቢሰሙ ወይም ባይሰሙ። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ብለህ ንገራቸው አለኝ።
12 ፤ መንፈስም አነሣኝ፥ በኋላዬም። የእግዚአብሔር ክብር ከቦታው ይባረክ የሚል የጽኑ ንውጥውጥታ ድምፅ ሰማሁ።
13 ፤ የአራቱም እንስሳ ክንፎች እርስ በርሳቸው ሲማቱ፥ በአጠገባቸውም የመንኰራኵሮችን ድምፅ፥ የጽኑውንም ንውጥውጥታ ድምፅ ሰማሁ።
14 ፤ መንፈስ አንሥቶ አስወገደኝ፥ እኔም በምሬትና በመንፈሴ ሙቀት ሄድሁ፥ የእግዚአብሔርም እጅ በላዬ በርትታ ነበር።
15 ፤ በቴልአቢብም ወዳሉ በኮቦርም ወንዝ አጠገብ ወደ ተቀመጡ ምርኮኞች መጣሁ፥ በተቀመጡበትም ቦታ ተቀመጥሁ፤ በዚያም ሰባት ቀን በድንጋጤ በመካከላቸው ተቀመጥሁ።
16 ፤ ከሰባቱም ቀን በኋላ የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
17 ፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ ለእስራኤል ቤት ጠባቂ አድርጌሃለሁ፤ ስለዚህ የአፌን ቃል ስማ ከእኔም ዘንድ አስጠንቅቃቸው።
18 ፤ እኔ ኃጢአተኛውን። በእርግጥ ትሞታለህ ባልሁት ጊዜ፥ አንተም ባታስጠነቅቀው ነፍሱም እንድትድን ከክፉ መንገዱ ይመለስ ዘንድ ለኃጢአተኛው አስጠንቅቀህ ባትነግረው፥ ያ ኃጢአተኛ በኃጢአት ይሞታል፤ ደሙን ግን ከእጅህ እፈልጋለሁ።
19 ፤ ነገር ግን አንተ ኃጢአተኛውን ብታስጠነቅቅ እርሱም ከኃጢአቱና ከክፉ መንገዱ ባይመለስ፥ በኃጢአቱ ይሞታል፥ አንተ ግን ነፍስህን አድነሃል።
20 ፤ ደግሞ ጻድቁ ከጽድቁ ተመልሶ ኃጢአት በሠራ ጊዜ እኔ በፊቱም ዕንቅፋትን ሳደርግ፥ እርሱ ይሞታል፤ አንተም አላስጠነቀቅኸውምና በኃጢአቱ ይሞታል ያደረጋትም ጽድቅ ነገር አትታሰብለትም፤ ደሙን ግን ከእጅህ እፈልጋለሁ።
21 ፤ ነገር ግን ኃጢአት እንዳይሠራ ጻድቁን ብታስጠነቅቅ እርሱም ኃጢአት ባይሠራ፥ ተጠንቅቆአልና በእርግጥ በሕይወት ይኖራል፤ አንተም ነፍስህን አድነሃል።
22 ፤ በዚያም የእግዚአብሔር እጅ በእኔ ላይ ነበረች፥ እርሱም። ተነሥተህ ወደ ቈላው ሂድ በዚያም እናገርሃለሁ አለኝ።
23 ፤ እኔም ተነሥቼ ወደ ቈላው ሄድሁ፤ እነሆም፥ በኮቦር ወንዝ እንዳየሁት ክብር ያለ የእግዚአብሔር ክብር በዚያ ቆሞ ነበር፥ በግምባሬም ተደፋሁ።
24 ፤ መንፈስም ገባብኝ በእግሬም አቆመኝ፥ ተናገረኝም እንዲህም አለኝ። ሂድ፥ ገብተህ ቤትህን ዝጋ።
25 ፤ አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ እነሆ፥ ገመድ ያደርጉብሃል ያስሩህማል፥ አንተም በመካከላቸው አትወጣም፤
26 ፤ እኔም ምላስህን ከትናጋህ ጋር አጣብቃታለሁ አንተም ዲዳ ትሆናለህ፥ እነርሱም ዓመፀኛ ቤት ናቸውና የሚዘልፍ ሰው አትሆንባቸውም።
27 ፤ ነገር ግን በተናገርሁህ ጊዜ አፍህን እከፍታለሁ፥ እነርሱም ዓመፀኛ ቤት ናቸውና አንተ። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የሚሰማ ይስማ፥ የማይሰማም አይስማ ትላቸዋለህ።