ምዕራፍ 1

ዖፅ በሚባል አገር ስሙ ኢዮብ የተባለ አንድ ሰው ነበረ፤ ያም ሰው ፍጹምና ቅን፥ እግዚአብሔርንም የሚፈራ፥ ከክፋትም የራቀ ነበረ።
2 ፤ ሰባትም ወንዶች ሦስትም ሴቶች ልጆች ተወልደውለት ነበር።
3 ፤ ሀብቱም ሰባት ሺህ በጎች፥ ሦስት ሺህም ግመሎች፥ አምስት መቶም ጥማድ በሬ፥ አምስት መቶም እንስት አህዮች ነበረ፥ እጅግ ብዙም ባሪያዎች ነበሩት፤ ያም ሰው በምሥራቅ ካሉ ሰዎች ሁሉ ይልቅ ታላቅ ነበረ።
4 ፤ ወንዶች ልጆቹም ሄደው በየተራ በያንዳንዳቸው ቤት ግብዣ ያደርጉ ነበር፤ ሦስቱ እኅቶቻቸውም ከእነርሱ ጋር ይበሉና ይጠጡ ዘንድ እነርሱ ልከው ይጠሩአቸው ነበር።
5 ፤ የግብዣውም ቀኖች ባለፉ ጊዜ ኢዮብ። ምናልባት ልጆቼ በድለው፥ እግዚአብሔርንም በልባቸው ሰድበው ይሆናል ብሎ ይልክና ይቀድሳቸው ነበር፤ ኢዮብም ማልዶ ተነሣ፥ እንደ ቍጥራቸውም ሁሉ የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረበ። እንዲሁ ኢዮብ ሁልጊዜ ያደርግ ነበር።
6 ፤ ከዕለታት አንድ ቀን እንዲህ ሆነ፤ የአምላክ ልጆች በእግዚአብሔር ፊት ለመቆም መጡ፥ ሰይጣንም ደግሞ በመካከላቸው መጣ።
7 ፤ እግዚአብሔርም ሰይጣንን። ከወዴት መጣህ? አለው። ሰይጣንም። ምድርን ሁሉ ዞርሁአት፥ በእርስዋም ተመላለስሁ ብሎ ለእግዚአብሔር መለሰ።
8 ፤ እግዚአብሔርም ሰይጣንን። በውኑ ባሪያዬን ኢዮብን ተመለከትኸውን? በምድር ላይ እንደ እርሱ ፍጹምና ቅን፥ እግዚአብሔርንም የሚፈራ፥ ከክፋትም የራቀ ሰው የለም አለው።
9 ፤ ሰይጣንም ለእግዚአብሔር እንዲህ ብሎ መለሰለት። በውኑ ኢዮብ እግዚአብሔርን የሚፈራ በከንቱ ነውን?
10 ፤ እርሱንና ቤቱን በዙሪያውም ያሉትን ሁሉ አላጠርህለትምን? የእጁን ሥራ ባርከህለታል፥ ከብቱም በምድር ላይ በዝቶአል።
11 ፤ ነገር ግን እጅህን ዘርግተህ ያለውን ሁሉ ዳብስ፤ በእውነት በፊትህ ይሰድብሃል።
12 ፤ እግዚአብሔርም ሰይጣንን። እነሆ ለእርሱ ያለው ሁሉ በእጅህ ነው፥ ነገር ግን በእርሱ ላይ እጅህን አትዘርጋ አለው። ሰይጣንም ከእግዚአብሔር ፊት ወጣ።
13 ፤ አንድ ቀንም እንዲህ ሆነ፤ የኢዮብ ወንዶችና ሴቶች ልጆች በታላቅ ወንድማቸው ቤት ይበሉና የወይን ጠጅ ይጠጡ ነበር።
14 ፤ መልክተኛም ወደ ኢዮብ መጥቶ። በሬዎች እርሻ ያርሱ፥ በአጠገባቸውም አህዮች ይሰማሩ ነበር፤
15 ፤ የሳባም ሰዎች አደጋ ጣሉ፥ ወሰዱአቸውም፥ ብላቴኖቹንም በሰይፍ ስለት ገደሉ፤ እኔም እነግርህ ዘንድ ብቻዬን አመለጥሁ አለው።
16 ፤ እርሱም ገና ሲናገር ሌላ መጥቶ። የእግዚአብሔር እሳት ከሰማይ ወደቀች፥ በጎቹንም አቃጠለች፥ ጠባቂዎችንም በላች፤ እኔም እነግርህ ዘንድ ብቻዬን አመለጥሁ አለው።
17 ፤ እርሱም ገና ሲናገር ሌላ መጥቶ። ከለዳውያን በሦስት ረድፍ ተከፍለው በግመሎች ላይ አደጋ ጣሉ፥ ወሰዱአቸውም፥ ብላቴኖቹንም በሰይፍ ስለት ገደሉ፤ እኔም እነግርህ ዘንድ ብቻዬን አመለጥሁ አለው።
18 ፤ እርሱም ገና ሲናገር ሌላ መጥቶ። ወንዶችና ሴቶች ልጆችህ በታላቅ ወንድማቸው ቤት ይበሉና የወይን ጠጅ ይጠጡ ነበር፤
19 ፤ እነሆም፥ ዐውሎ ነፋስ ከምድረ በዳ መጥቶ የቤቱን አራቱን ማዕዘን መታው፥ በብላቴኖቹም ላይ ወደቀ፥ ሞቱም፤ እኔም እነግርህ ዘንድ ብቻዬን አመለጥሁ አለው።
20 ፤ ኢዮብም ተነሣ መጐናጸፊያውንም ቀደደ፥ ራሱንም ተላጨ፥ በምድርም ላይ ተደፍቶ ሰገደ፤
21 ፤ እንዲህም አለ። ራቁቴን ከእናቴ ማኅፀን ወጥቻለሁ፥ ራቁቴንም ወደዚያ እመለሳለሁ፤ እግዚአብሔር ሰጠ፥ እግዚአብሔርም ነሣ፤ የእግዚአብሔር ስም የተባረከ ይሁን።
22 ፤ በዚህ ሁሉ ኢዮብ አልበደለም፥ ለእግዚአብሔርም ስንፍናን አልሰጠም።