መጽሐፈ ኢዮብ።
ምዕራፍ 11
ነዕማታዊውም ሶፋር መለስ እንዲህም አለ።
2 ፤ በውኑ ለቃል ብዛት መልስ መስጠት አይገባምን? ወይስ ተናጋሪ ሰው እንደ ጻድቅ ይቈጠራልን?
3 ፤ ትምክህትህስ ሰዎችን ዝም ያሰኛቸዋልን? ብትሳለቅስ የሚያሳፍርህ የለምን?
4 ፤ አንተ። ትምህርቴ የተጣራ ነው፥ በዓይንህም ፊት ንጹሕ ነኝ ትላለህ።
5 ፤ ምነው እግዚአብሔር ቢናገርህ! በአንተም ላይ ከንፈሩን ቢከፍት!
6 ፤ የጥበቡን ምሥጢር ቢገልጥልህ! ማስተዋሉ ብዙ ነውና። እግዚአብሔር ለበደልህ ከሚገባው አሳንሶ እንደሚያስከፍልህ እወቅ።
7 ፤ የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር ልትመረምር ትችላለህን? ወይስ ሁሉን የሚችል አምላክ ፈጽመህ ልትመረምር ትችላለህን?
8 ፤ ከሰማይ ይልቅ ከፍ ይላል፤ ምን ልታደርግ ትችላለህ? ከሲኦልም ይልቅ ይጠልቃል፤ ምን ልታውቅ ትችላለህ?
9 ፤ ርዝመቱ ከምድር ይልቅ ይረዝማል፥ ከባሕርም ይልቅ ይሰፋል።
10 ፤ እርሱ ቢያልፍ፥ ቢዘጋም፥ ጉባኤንም ቢሰበስብ፥ የሚከለክለው ማን ነው?
11 ፤ ምናምንቴዎችን ሰዎች ያውቃልና፥ በደልንም ሲያይ ዝም ብሎ አይመለከትም።
12 ፤ የሜዳ አህያ ግልገል ሰው ሆኖ ቢወለድ፥ ያን ጊዜ ከንቱ ሰው ጥበብን ያገኛል።
13 ፤
14 ፤ በእጅህ በደል ቢኖር አርቀው፤ በድንኳንህም ኃጢአት አይኑር፤ አንተ ልብህን ቅን ብታደርግ፥ እጅህንም ወደ እርሱ ብትዘረጋ፥
15 ፤ በዚያን ጊዜ በእውነት ፊትህን ያለ ነውር ታነሣለህ፤ ትበረታለህ፥ አትፈራምም።
16 ፤ መከራህንም ትረሳለህ፤ እንዳለፈ ውኃ ታስበዋለህ።
17 ፤ ከቅትር ይልቅ ሕይወትህ ይበራል፤ ጨለማም ቢሆን እንደ ጥዋት ይሆናል።
18 ፤ ተስፋም ስላለህ ተዘልለህ ትቀመጣለህ፤ በዙሪያህ ትመለከታለህ፥ በደኅንነትም ታርፋለህ።
19 ፤ ትተኛለህ፥ የሚያስፈራህም የለም፤ ብዙ ሰዎችም ልመና ያቀርቡልሃል።
20 ፤ የክፉዎች ዓይን ግን ትጨልማለች፤ የሚሸሹበትንም ያጣሉ፥ ተስፋቸውም ነፍሳቸውን ማውጣት ነው።