ምዕራፍ 16

ኢዮብም መለሰ እንዲህም አለ።
2 ፤ እንደዚህ ያለ ዓይነት ነገር እጅግ ሰማሁ፤ እናንተ ሁላችሁ የምታደክሙ አጽናኞች ናችሁ።
3 ፤ በውኑ ከንቱ ቃል ይፈጸማልን? ወይስ ትመልስ ዘንድ ያነሣሣህ ምንድር ነው?
4 ፤ እኔ ደግሞ እንደ እናንተ እናገር ዘንድ ይቻለኝ ነበር፤ ነፍሳችሁ በነፍሴ ፋንታ ቢሆን ኖሮ፥ እኔ በእናንተ ላይ ቃል ማሳካት፥ ራሴንም በእናንተ ላይ መነቅነቅ በተቻለኝ ነበር።
5 ፤ በአፌም ነገር ባበረታኋችሁ ነበር፤ የከንፈሬን ማጽናናት ባልከለከልሁም ነበር።
6 ፤ እኔ ብናገር ሕማሜ አይቀነስም፤ ዝምም ብል ከእኔ አይወገድም።
7 ፤ አሁን ግን አድክሞኛል፤ ወገኔንም ሁሉ አፍርሰሃል።
8 ፤ መጨማተሬ ይመሰክርብኛል፤ ክሳቴም ተነሥቶብኛል፤ በፊቴም ይመሰክርብኛል።
9 ፤ በቍጣው ቀደደኝ፥ እርሱም ጠላኝ፤ ጥርሶቹንም አፋጨብኝ፤ ጠላቴ ዓይኑን አፈጠጠብኝ፤
10 ፤ እነርሱም አፋቸውን ከፈቱብኝ፤ እያላገጡ ጕንጬን ጠፈጠፉኝ፤ በአንድነትም ተሰበሰቡብኝ።
11 ፤ እግዚአብሔር ለጠማማ ሰው አሳልፎ ሰጠኝ፥ በክፉዎችም እጅ ጣለኝ።
12 ፤ ተዘልዬ ተቀምጬ ነበር፥ እርሱም ሰበረኝ፤ አንገቴንም ይዞ ቀጠቀጠኝ፤ እንደ ዓላማ አድርጎ አቆመኝ።
13 ፤ ቀስተኞቹ ከበቡኝ፤ ኵላሊቴንም ቈራረጠ፥ እርሱም አልራራም፤ ሐሞቴን በምድር ላይ አፈሰሰ።
14 ፤ በቍስል ላይ ቍስል ጨመረብኝ፤ እንደ ኃያል እየሠገገ ይሮጥብኛል።
15 ፤ በቁርበቴ ላይ ማቅ ሰፋሁ፥ ቀንዴንም በመሬት ላይ አኖርሁ።
16 ፤ ፊቴ ከልቅሶ የተነሣ ቀላ፤ የሞት ጥላ በዓይኖቼ ቆብ ላይ አለ፤
17 ፤ ነገር ግን በእጄ ዓመፅ የለም፤ ጸሎቴም ንጹሕ ነው።
18 ፤ ምድር ሆይ፥ ደሜን አትክደኚ፥ ለጩኸቴም ማረፊያ አይሁን።
19 ፤ አሁንም፥ እነሆ፥ ምስክሬ በሰማይ አለ፥ የሚመሰክርልኝም በአርያም ነው።
20 ፤ ጸሎቴ ወደ እግዚአብሔር ይድረስ፥ ዓይኔም በፊቱ እንባ ታፍስስ።
21 ፤ የሰው ልጅ ከባልንጀራው ጋር እንደሚምዋገት፥ ሰው በእግዚአብሔር ፊት ለመምዋገት ምነው በቻለ!
22 ፤ ጥቂቶች ዓመታት ካለፉ በኋላ እኔ ወደማልመለስበት መንገድ እሄዳለሁ።