መጽሐፈ ኢዮብ።
ምዕራፍ 18
ሹሐዊውም በልዳዶስ መለሰ እንዲህም አለ።
2 ፤ እስከ መቼ ቃልን ታጠምዳለህ?  አስተውል፥ ከዚያም በኋላ እንናገራለን።
3 ፤ ስለ ምንስ እንደ እንስሶች ተቈጠርን?  ስለ ምንስ በዓይንህ ፊት ረከስን?
4 ፤ ቍጣ ወርሶሃል፤ አንተስ የሞትህ እንደ ሆነ፥  ምድር ስለ አንተ ባድማ ትሆናለችን?  ወይስ ዓለት ከስፍራው ይነቀላልን?
5 ፤ የኃጢአተኛ መብራት ይጠፋል፥  የእሳቱም ነበልባል ብልጭ አይልም።
6 ፤ ብርሃን በድንኳኑ ውስጥ ይጨልማል፥  መብራቱም በላዩ ይጠፋል።
7 ፤ የኃይሉም እርምጃ ትጠብባለች፥  ምክሩም ትጥለዋለች።
8 ፤ እግሩ በወጥመድ ትያዛለች፥  በመረብም ላይ ይሄዳል።
9 ፤ አሽክላ ሰኰናውን ይይዛል፥  ወስፈንጠርም ይበረታበታል።  
10 ፤ በምድር ላይ የሸምቀቆ ገመድ፥  በመንገዱም ላይ ወጥመድ ለእርሱ ተሰውራለች።  
11 ፤ ድንጋጤ በዙሪያው ታስፈራዋለች፥  በስተ ኋላውም ሆና ታባርራቸዋለች።  
12 ፤ ኃይሉ በራብ ትደክማለች፥  መቅሠፍትም እስኪሰናከል ተዘጋጅቶለታል።  
13 ፤ የሰውነቱ ብልቶች ይጠፋሉ፤  የሞትም በኵር ልጅ ብልቶቹን ይበላል።  
14 ፤ ከሚታመንበት ድንኳን ይነቀላል፤  ወደ ድንጋጤም ንጉሥ ያስቸኵሉታል።  
15 ፤ በድንኳኑ ውስጥ ለእርሱ የማይሆነው ይኖራል፤  በመኖሪያውም ላይ ዲን ይበተናል።  
16 ፤ ሥሩ ከበታቹ ይደርቃል፥  ጫፉም ከበላይ ይረግፋል።  
17 ፤ መታሰቢያው ከምድር ላይ ይጠፋል፥  በሜዳም ስም አይቀርለትም።  
18 ፤ ከብርሃን ወደ ጨለማ ያፈልሱታል፥  ከዓለምም ያሳድዱታል።  
19 ፤ ዘርም ትውልድም በሕዝቡ መካከል አይሆንለትም፤  በመኖሪያውም ውስጥ የሚቀመጥ ሰው አይቀርለትም።  
20 ፤ የፊተኞች ሰዎች እንደ ደነገጡ፥  እንዲሁ የኋለኞች ሰዎች ስለ ዘመኑ ይደነቃሉ።  
21 ፤ በእውነት የኃጢአተኞች ቤት እንዲሁ ናት፥  እግዚአብሔርንም የማያውቅ ሰው ስፍራ ይህ ነው።