ምዕራፍ 24

ሁሉን ከሚችል አምላክ ዘንድ ዘመናት አልተሰወረምና እርሱን የሚያውቁ ለምን ወራቱን አያዩም?
2 ፤ የድንበሩን ምልክት የሚያፈርሱ አሉ፤ መንጋዎቹን በዝብዘው ያሰማራሉ።
3 ፤ የድሀ አድጎቹን አህያ ይነዳሉ፤ የመበለቲቱን በሬ ስለ መያዣ ይወስዳሉ።
4 ፤ ድሆቹን ከመንገዱ ያወጣሉ፤ የምድርም ችግረኞች ሁሉ ይሸሸጋሉ።
5 ፤ እነሆ፥ በምድረ በዳ እንዳሉ እንደ ሜዳ አህዮች፥ መብልን ፈልገው ወደ ሥራቸው ይወጣሉ፤ ምድረ በዳውም ለልጆቻቸው መብልን ይሰጣቸዋል።
6 ፤ እነዚያ በእርሻ ውስጥ እህላቸውን ያጭዳሉ፤ የበደለኛውንም ወይን ይቃርማሉ።
7 ፤ ራቁታቸውን ያለ ልብስ ያድራሉ፥ በብርድ ጊዜ መጐናጸፊያ የላቸውም።
8 ፤ ከተራሮች በሚወርድ ዝናብ ይረጥባሉ፤ መጠጊያም አጥተው ቋጥኙን ያቅፋሉ።
9 ፤ ድሀ አደጉን ልጅ ከጡቱ የሚነጥሉ አሉ ከችግረኛውም መያዣ ይወስዳሉ።
10 ፤ ያለ ልብስ ራቁታቸውን ይሄዳሉ፤ ተርበውም ነዶዎችን ይሸከማሉ፤
11 ፤ በእነዚህ ሰዎች አጥር ውስጥ ዘይት ያደርጋሉ፤ ወይንም ይጠምቃሉ፥ ነገር ግን ይጠማሉ።
12 ፤ ከከተማውና ከገዛ ቤቶቻቸው ይባረራሉ፤ የልጆችም ነፍስ ለእርዳታ ትጮኻለች፤ እግዚአብሔር ግን ስንፍናቸውን አይመለከትም።
13 ፤ እነዚህ በብርሃን ላይ የሚያምፁ ናቸው፤ መንገዱን አያውቁም፥ በጎዳናውም አይጸኑም።
14 ፤ ነፍሰ ገዳዩም ሳይነጋ ማልዶ ይነሣል፤ ችግረኞችንና ድሆችን ይገድላል፤ በሌሊትም እንደ ሌባ ነው።
15 ፤ የአመንዝራም ዓይን ድግዝግዝታን ይጠብቃል። የማንም ዓይን አያየኝም ይላል፥ ፊቱንም ይሸፍናል።
16 ፤ ቤቶቹን በጨለማ ይነድላሉ፤ በቀን ይሸሸጋሉ፤ ብርሃንም አያውቁም።
17 ፤ የጥዋት ብርሃን ለእነርሱ ሁሉ እንደ ሞት ጥላ ነው፤ የሞትን ጥላ ድንጋጤ ያውቃሉና።
18 ፤ እነርሱ በውኃ ፊት ላይ በርረው ያልፋሉ፤ እድል ፈንታቸውም በምድር ላይ የተረገመች ናት፤ ወደ ወይኑ ቦታ መንገድ አይዞሩም።
19 ፤ ድርቅና ሙቀት የአመዳዩን ውኃ ያጠፋሉ፤ እንዲሁ ሲኦል በደለኞችን ታጠፋለች።
20 ፤ ማኅፀን ትረሳዋለች፤ ትልም በደስታ ይጠባዋል፤ ዳግመኛም አይታሰብም፤ ክፋትም እንደ ዛፍ ይሰበራል።
21 ፤ የማትወልደውን መካኒቱን ይበድላታል፤ ለመበለቲቱም በጎነት አያደርግም።
22 ፤ ነገር ግን በኃይሉ ኃያላንን ይስባል፤ እርሱም በተነሣ ጊዜ ሰው በሕይወቱ አይታመንም።
23 ፤ እግዚአብሔር በደኅና አኑሮአቸዋል፥ በዚያም ይታመናሉ፤ ዓይኖቹ ግን በመንገዳቸው ላይ ናቸው።
24 ፤ ጥቂት ጊዜ ከፍ ከፍ ይላሉ፤ ይሄዳሉ፥ ይጠወልጋሉም፤ እንደ ሌሎች ሁሉ ይከማቻሉ፤ እንደ እሸትም ራስ ይቈረጣሉ።
25 ፤ እንዲህስ ባይሆን ሐሰተኛ የሚያደርገኝ፥ ነገሬንስ እንደ ምናምን የሚያደርገው ማን ነው?