መጽሐፈ ኢዮብ።
ምዕራፍ 5
አሁንም ጥራ፤ የሚመልስልህ አለን? ከቅዱሳንስ ወደማናቸው ትዞራለህ?
2 ፤ ሰነፉን ሰው ቍጣ ይገድለዋል፥ ሰነፉንም ቅንዓት ያጠፋዋል።
3 ፤ ሰነፍ ሰው ሥር ሰድዶ አየሁት፥ ድንገትም መኖሪያውን ረገምሁ።
4 ፤ ልጆቹም ከደኅንነት ርቀዋል፥ በበርም ውስጥ ተረግጠዋል፥ የሚታደጋቸውም የለም።
5 ፤ የሰበሰበውንም ራብተኛ ይበላዋል፥ ከእሾህም ውስጥ እንኳ ያወጣዋል፤ የተጠማ ሀብታቸውን ዋጠ።
6 ፤ ችግር ከትቢያ አይመጣም፥ መከራም ከመሬት አይበቅልም፤
7 ፤ የአሞራ ግልገሎች ግን ወደ ላይ እየበረሩ ከፍ እንዲሉ፥ ሰው እንዲሁ ለመከራ ተወልዶአል።
8 ፤ እኔ ግን እግዚአብሔርን እለምን ነበር፥ ነገሬንም ወደ እግዚአብሔር አቀርብ ነበር።
9 ፤ የማይመረመረውን ታላቅ ነገርና የማይቈጠረውን ተአምራት ያደርጋል።
10 ፤ በምድር ላይ ዝናብን ይሰጣል፥ በእርሻም ላይ ውኃ ይልካል።
11 ፤ የተዋረዱትን ወደ ላይ ያወጣል፥ ኀዘንተኞችንም ለደኅንነት ከፍ ከፍ ያደርጋቸዋል።
12 ፤ እጃቸውም ምክራቸውን እንዳይፈጽም የተንኰለኞችን አሳብ ከንቱ ያደርገዋል።
13 ፤ ጠቢባንን በተንኰላቸው ይይዛቸዋል፤ የጠማሞችንም ምክር ይዘረዝራል።
14 ፤ በቀን ጨለማን ያገኛሉ፥ በቀትርም ጊዜ በሌሊት እንዳሉ ይርመሰመሳሉ።
15 ፤ ድሀውንም ከአፋቸው ሰይፍ ከኃያሉም እጅ ያድነዋል።
16 ፤ ለምስኪኑም ተስፋ አለው፤ ክፋት ግን አፍዋን ትዘጋለች።
17 ፤ እነሆ፥ እግዚአብሔር የሚገሥጸው ሰው ምስጉን ነው፤ ስለዚህ ሁሉን የሚችለውን የአምላክን ተግሣጽ አትናቅ።
18 ፤ እርሱ ይሰብራል፥ ይጠግንማል፤ ያቈስላል፥ እጆቹም ይፈውሳሉ።
19 ፤ በስድስት ክፉ ነገር ውስጥ ያድንሃል፥ በሰባትም ውስጥ ክፋት አትነካህም።
20 ፤ በራብ ጊዜ ከሞት፥ በሰልፍም ከሰይፍ እጅ ያድንሃል።
21 ፤ ከምላስ ጅራፍ ትሰወራለህ፤ ጥፋትም ሲመጣ አትፈራም።
22 ፤ በጥፋትና በራብ ላይ ትስቃለህ፤ ከምድረ በዳ አራዊትም አትፈራም፤
23 ፤ ቃል ኪዳንህ ከምድረ በዳ ድንጋይ ጋር ይሆናልና፤ የምድረ በዳም አራዊት ከአንተ ጋር ይስማማሉና።
24 ፤ ድንኳንህም በሰላም እንዲሆን ታውቃለህ፤ በረትህን ትጐበኛለህ አንዳችም አይጐድልብህም።
25 ፤ ዘርህም ታላቅ እንዲሆን፥ ትውልድህም እንደ ምድር ሣር እንዲሆን ታውቃለህ።
26 ፤ በወራቱ የእህሉ ነዶ ወደ አውድማ እንዲገባ፥ በረጅም ዕድሜ ወደ መቃብር ትገባለህ።
27 ፤ እነሆ፥ ይህችን መረመርን፥ የሰማነውም ይህ ነው፤ አንተ ግን አንዳች ሠርተህ እንደ ሆነ ለራስህ እወቀው።