መጽሐፈ ኢዮብ።
ምዕራፍ 22
ቴማናዊውም ኤልፋዝ መለሰ እንዲህም አለ።
2 ፤ በውኑ ሰው እግዚአብሔርን ይጠቅመዋልን? በእውነት ጥበበኛ ሰው ራሱን ይጠቅማል።
3 ፤ ጻድቅ መሆንህስ ሁሉን የሚችለውን አምላክ ደስ ያሰኘዋልን? መንገድህን ማቅናትህስ ይጠቅመዋልን?
4 ፤ እርሱንስ ስለ ፈራህ ይዘልፍሃልን? ወደ ፍርድስ ከአንተ ጋር ይገባልን?
5 ፤ ክፋትህስ የበዛ አይደለምን? ለኃጢአትህም ፍጻሜ የላትም።
6 ፤ የወንድሞችህን መያዣ በከንቱ ወስደሃል፥ የእርዘኞቹንም ልብስ ዘርፈሃል።
7 ፤ ለደካማ ውኃ አላጠጣህም፥ ለራብተኛም እንጀራን ከልክለሃል።
8 ፤ በክንድ የበረታ ምድርን ገዛ፤ ከበርቴውም ሰው ተቀመጠባት።
9 ፤ መበለቲቱን አንዳች አልባ ሰድደሃታል፤ የድሀ አደጎችም ክንድ ተሰብሮአል።
10 ፤ ስለዚህ አሽክላ ከብቦሃል፥ ድንገተኛ ፍርሃትም አናውጦሃል።
11 ፤ እንዳታይ ብርሃን ጨለማ ሆነችብህ፥ የውኆችም ብዛት አሰጠመህ።
12 ፤ እግዚአብሔር በሰማያት ከፍ ከፍ አይልምን? ከዋክብትም እንዴት ከፍ ከፍ እንዳሉ ተመልከት።
13 ፤ አንተም። እግዚአብሔር ምን ያውቃል? በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ሆኖ ሊፈርድ ይችላልን?
14 ፤ እንዳያይ የጠቈረ ደመና ጋርዶታል፤ በሰማይ ክበብ ላይ ይራመዳል ብለሃል።
15 ፤ በውኑ ኃጢአተኞች ሰዎች የረገጡአትን የዱሮይቱን መንገድ ትጠብቃለህን?
16 ፤ ጊዜያቸው ሳይደርስ ተነጠቁ፤ መሠረታቸውም እንደ ፈሳሽ ውኃ ፈሰሰ።
17 ፤ እግዚአብሔርንም። ከእኛ ዘንድ ራቅ፤ ሁሉንም የሚችል አምላክ ምን ሊያደርግልን ይችላል? አሉት።
18 ፤ ነገር ግን ቤታቸውን በመልካም ነገር ሞላ፤ የኃጥአን ምክር ከእኔ ዘንድ የራቀች ናት።
19 ፤ ጻድቃን ያዩታል፥ ደስም ይላቸዋል፤ ንጹሐንም በንቀት ይስቁባቸዋል።
20 ፤ በእውነት ሀብታቸው ጠፋ፥ የቀረውንም እሳት በላች።
21 ፤ አሁንም ከእርሱ ጋር ተስማማ፥ ሰላምም ይኑርህ፤ በዚያም በጎነት ታገኛለህ።
22 ፤ ከአፉም ሕጉን ተቀበል፥ በልብህም ቃሉን አኑር፤
23 ፤ ሁሉን ወደሚችል አምላክ ብትመለስ፥ ብትዋረድም፥ ኃጢአትንም ከድንኳንህ ብታርቅ፥
24 ፤ የወርቅን ዕቃ በአፈር ውስጥ፥ የኦፊርንም ወርቅ በጅረት ድንጋይ መካከል ብትጥል፥
25 ፤ ሁሉን የሚችል አምላክ ወርቅና የሚብለጨለጭ ብር ይሆንልሃል።
26 ፤ የዚያን ጊዜ ሁሉን በሚችል አምላክ ደስ ይልሃል፥ ፊትህንም ወደ እግዚአብሔር ታነሣለህ።
27 ፤ ወደ እርሱም ትጸልያለህ፥ እርሱም ይሰማሃል፤ ስእለትህንም ትሰጣለህ።
28 ፤ ነገርንም ትመክራለህ፥ እርሱም ይሳካልሃል፤ ብርሃንም በመንገድህ ላይ ይበራል።
29 ፤ ቢያዋርዱህ አንተ ከፍ ከፍ ትላለህ፤ ትሑቱንም ሰው ያድነዋል።
30 ፤ ንጹሑን ሰው ያድነዋል፤ በእጅህም ንጽሕና ትድናለህ።