ምዕራፍ 6

ኢዮብም መለሰ እንዲህም አለ።
2 ፤ ትካዜዬ ምነው በተመዘነ ኖሮ! መከራዬም ሁሉ ምነው በሚዛን ላይ በተደረገ ኖሮ!
3 ፤ ከባሕር አሸዋ ይልቅ ይከብድ ነበርና፤ ስለዚህ ቃሌ ደፋር ሆኖአል።
4 ፤ ሁሉን የሚችል የአምላክ ፍላጻ በሥጋዬ ውስጥ ነው፥ መርዙንም ነፍሴ ትጠጣለች፤ የእግዚአብሔር ድንጋጤ በላዬ ተሰልፎአል።
5 ፤ በውኑ የሜዳ አህያ ሣር ሳለው ይጮኻልን? ወይስ በሬ ገለባ ሳለው ይጮኻልን?
6 ፤ የማይጣፍጥስ ነገር ያለ ጨው ይበላልን? ወይስ የእንቁላል ውኃ ይጥማልን?
7 ፤ ሰውነቴ ትነካው ዘንድ እንቢ አለችው፤ እንደሚያስጸይፍ መብል ሆነብኝ።
8 ፤ ልመናዬ ምነው በደረሰልኝ! እግዚአብሔርም ምኞቴን ምነው በሰጠኝ!
9 ፤ እግዚአብሔርም ያደቀኝ ዘንድ እጁንም ለቅቆ ያጠፋኝ ዘንድ ወድዶ ቢሆን ኖሮ!
10 ፤ መጽናናት በሆነልኝ ነበር፤ በማይራራ ሕመም ሐሤት ባደረግሁ ነበር፥ የቅዱሱን ቃል አልካድሁምና።
11 ፤ እጠብቅ ዘንድ ጕልበቴ ምንድር ነው? እታገሥም ዘንድ ፍጻሜዬ ምንድር ነው?
12 ፤ ጕልበቴ የድንጋይ ጕልበት ነውን? ሥጋዬስ እንደ ናስ ነውን?
13 ፤ በውኑ ረድኤት በእኔ እንደሌለ ጥበብም ሁሉ ከእኔ ዘንድ እንደ ተባረረ አይደለምን?
14 ፤ ሁሉን የሚችለውን የአምላክን መፍራት ለሚተው፥ ለመዛል ለቀረበው ስንኳ ወዳጁ ቸርነትን ሊያሳይ ይገባል።
15 ፤ ወንድሞቼ እንደ ፈፋ፥ እንደሚያልፍ ፈፋ ሐሰተኞች ሆኑብኝ።
16 ፤ ከበረዶ የተነሣ ደፈረሱ፥ አመዳይም ተሰወረባቸው፤
17 ፤ ፀሐይ በተኰሰች ጊዜ ይደርቃሉ፤ በሙቀትም ጊዜ ከስፍራቸው ይጠፋሉ።
18 ፤ በየዳርቻቸውም የሚሄዱ ነጋዴዎች ፈቀቅ ይላሉ፤ ወደ በረሃ ወጥተው ይጠፋሉ።
19 ፤ የቴማን ነጋዴዎች ተመለከቱ፥ የሳባ መንገደኞችም ተጠባበቁአቸው።
20 ፤ ተስፋ አድርገዋቸው ነበርና አፈሩ፤ ወደዚያ ደረሱ፥ እፍረትም ያዛቸው።
21 ፤ አሁንም እናንተ እንደዚሁ ሆናችኋል፤ መከራዬን አይታችሁ ፈራችሁ።
22 ፤ በውኑ። አንዳች ነገር አምጡልኝ፤ ወይስ። ከብልጥግናችሁ ስጦታ አቅርቡልኝ፤
23 ፤ ወይስ። ከጠላቴ እጅ አስጥሉኝ፤ ወይስ። ከአስጨናቂው እጅ አድኑኝ አልኋችሁን?
24 ፤ አስተምሩኝ፥ እኔም ዝም እላለሁ፤ የተሳሳትሁትንም ንገሩኝ።
25 ፤ የቅንነት ቃል እንዴት ኃይለኛ ነው! የእናንተ ሙግት ግን ምን ይገሥጻል?
26 ፤ ተስፋ የሌለው ሰው ንግግር እንደ ነፋስ ነውና ቃሌን ትገሥጹ ዘንድ ታስባላችሁን?
27 ፤ በድሀ አደጉ ላይ ዕጣ ትጣጣላላችሁ፤ ለወዳጆቻችሁም ጕድጓድ ትቈፍራላችሁ።
28 ፤ አሁንም፥ እባካችሁ፥ ወደ እኔ ተመልከቱ፤ በፊታችሁም ሐሰት አልናገርም።
29 ፤ እባካችሁ፥ ተመለሱ፤ በደል አይሁን፤ ጽድቄ በዚህ ነገር ነውና አንድ ጊዜ ተመለሱ።
30 ፤ በውኑ በአንደበቴ በደል ይገኛልን? አፌስ ተንኰልን ይለይ ዘንድ አይችልምን?