ምዕራፍ 4

ቴማናዊውም ኤልፋዝ መለሰ እንዲህም አለ።
2 ፤ አንድ ሰው ከአንተ ጋር ይናገር ዘንድ ቢሞክር ትቀየማለህን? ቃልንስ ከመናገር ሊቀር የሚችል ማን ነው?
3 ፤ እነሆ፥ አንተ ብዙዎችን ታስተምር ነበር፥ የደከሙትንም እጆች ታበረታ ነበር፥
4 ፤ ቃልህ የሚሰናከለውን ያስነሣ ነበር፥ አንተም የሚብረከረከውን ጕልበት ታጸና ነበር።
5 ፤ አሁን ግን በአንተ ላይ መጥቶአል፥ አንተም ደከምህ፤ ደርሶብሃል፥ አንተም ተቸገርህ።
6 ፤ አምላክህን መፍራትህ መጽናናትህ፥ የቅንነትህም መንገድ ተስፋህ አይደለምን?
7 ፤ እባክህ አስብ፥ ንጹሕ ሆኖ የጠፋ ማን ነው? ከልበ ቅንስ የተደመሰሰ ማን ነው?
8 ፤ እኔ እንዳየሁ፥ ኃጢአትን የሚያርሱ፥ መከራንም የሚዘሩ ይህንኑ ያጭዳሉ።
9 ፤ በእግዚአብሔር እስትንፋስ ይጠፋሉ፥ በቍጣውም መንፈስ ያልቃሉ።
10 ፤ የአንበሳ ጩኸት፥ የጩዋኺ አንበሳ ድምፅ፥ የአንበሳ ደቦል ጥርስ ተሰባበረ።
11 ፤ አሮጌ አንበሳ አደን በማጣት ይሞታል፥ የአንበሳይቱም ግልገሎች ይበተናሉ።
12 ፤ ለእኔም በምሥጢር ቃል መጣልኝ፥ ጆሮዬም ሹክሹክታውን ሰማች።
13 ፤ በሌሊት ሕልም አሳብ ሲነሣ፥ የከበደም እንቅልፍ በሰው ላይ ሲወድቅ፥
14 ፤ አጥንቴን ሁሉ ያናወጡ ድንጋጤና መንቀጥቀጥ ወደቁብኝ።
15 ፤ መንፈስም በፊቴ አለፈ፤ የሥጋዬ ጠጕር ቆመ።
16 ፤ እርሱም ቆመ፥ መልኩን ግን ለመለየት አልቻልሁም፥ ምሳሌም በዓይኔ ፊት ነበረ፤ የዝምታ ድምፅ ሰማሁ።
17 ፤ በውኑ ሰው በእግዚአብሔር ፊት ጻድቅ ሊሆን፥ ወይስ ሰው በፈጣሪው ፊት ሊነጻ ይችላልን?
18 ፤ እነሆ፥ በባሪያዎቹ አይታመንም፤ መላእክቱንም ስንፍና ይከስሳቸዋል፤
19 ፤ ይልቁንስ በጭቃ ቤት የሚኖሩ፥ መሠረታቸው በትቢያ ውስጥ የሆነ፥ ከብል በፊት የሚጨፈለቁ እንዴት ይሆኑ?
20 ፤ በጥዋትና በማታ መካከል ይሰባበራሉ፤ ማንም ሳያስብ ለዘላለም ይጠፋሉ።
21 ፤ ገመዳቸው የተነቀለ አይደለምን? አለጥበብም ይሞታሉ።