ምዕራፍ 9

ኢዮብም መለሰ እንዲህም አለ።
2 ፤ በእውነት እንዲህ እንደ ሆነ አወቅሁ፤ ሰውስ በእግዚአብሔር ፊት ጻድቅ መሆን እንዴት ይችላል?
3 ፤ ከእርሱ ጋር ይከራከር ዘንድ ቢወድድ፥ ከሺህ ነገር አንዱን መመለስ አይችልም።
4 ፤ ልቡ ጠቢብ፥ ኃይሉም ታላቅ ነው፤ ደፍሮትስ በደኅና የሄደ ማን ነው?
5 ፤ ተራሮችን ይነቅላል፤ አያውቁትም፤ በቍጣውም ይገለብጣቸዋል።
6 ፤ ምድርን ከስፍራው ያናውጣታል፥ ምሰሶችዋም ይንቀጠቀጣሉ።
7 ፤ ፀሐይን ያዝዛታል፥ አትወጣምም፤ ከዋክብትንም ያትማል።
8 ፤ ሰማያትን ብቻውን ይዘረጋል፥ በባሕሩም ማዕበል ላይ ይረግጣል።
9 ፤ ድብ የሚባለውን ኮከብና ኦሪዮን የሚባለውን ኮከብ፥ ሰባቱንም ከዋክብት፥ በደቡብም በኩል ያሉትን የከዋክብት ማደርያዎች ሠርቶአል።
10 ፤ የማይመረመረውን ታላላቅ ነገር፥ የማይቈጠረውንም ተአምራት ያደርጋል።
11 ፤ እነሆ፥ ቢመጣብኝ አላየውም፤ ቢያልፍብኝም አላውቀውም።
12 ፤ እነሆ፥ ፈጥኖ ቢነጥቅ የሚከለክለው ማን ነው? እርሱንስ። ምን ታደርጋለህ? የሚለው ማን ነው?
13 ፤ እግዚአብሔር ቍጣውን አይመልስም፤ ከእርሱ በታች ረዓብን የሚረዱ ይዋረዳሉ።
14 ፤ ይልቁንስ እመልስለት ዘንድ፥ ቃሌንስ በፊቱ እመርጥ ዘንድ እኔ ማን ነኝ?
15 ፤ ጻድቅ ብሆን ኖሮ አልመልስለትም ነበር፤ ወደ ፈራጄም እለምን ነበር።
16 ፤ ብጠራው እርሱም ቢመልስልኝ ኖሮ፥ ቃሌን እንደ ሰማ አላምንም ነበር።
17 ፤ በዐውሎ ነፋስ ይሰብረኛል፥ ቍስሌንም ያለ ምክንያት ያበዛል።
18 ፤ እተነፍስ ዘንድ አይተወኝም፥ ነገር ግን መራራን ነገር አጥግቦኛል።
19 ፤ የኃይል ነገር ቢሆን እርሱ ኃያል ነው፤ የፍርድ ነገር ቢሆን። ጊዜን ወሳኙ ማን ነው? ይላል።
20 ፤ ጻድቅ ብሆን አፌ ይወቅሰኛል፤ ፍጹምም ብሆን ጠማማ ያደርገኛል።
21 ፤ ፍጹም ነኝ ራሴንም አልመለከትም፤ ሕይወቴንም እንቃታለሁ።
22 ፤ ይህ ሁሉ አንድ ነው፤ ስለዚህ። ፍጹማንንና ክፉዎችን ያጠፋል እላለሁ።
23 ፤ መቅሠፍቱ ፈጥኖ ቢገድል፥ በንጹሐን ፈተና ይሳለቃል።
24 ፤ ምድር በኃጥአን እጅ ተሰጥታለች፤ የፈራጆችዋን ፊት ሸፍኖአል፤ እርሱ ካልሆነ ማን ነው?
25 ፤ ዘመኔ ከሚሮጥ ሰው ይልቅ ይፈጥናል፤ ይሸሻል፥ መልካምንም አያይም።
26 ፤ የደንገል ታንኳ እንደሚፈጥን፥ ንስርም ወደ ንጥቂያው እንደሚበርር ያልፋል።
27 ፤ እኔ። የኀዘን እንጕርጕሮዬን እረሳለሁ፤ ፊቴን መልሼ እጽናናለሁ ብል፥
28 ፤ ንጹሕ እንደማታደርገኝ እኔ አውቃለሁና ከመከራዬ ሁሉ እፈራለሁ።
29 ፤ በደለኛ እንደሚሆን ሰው እሆናለሁ፤ ስለ ምንስ በከንቱ እደክማለሁ?
30 ፤ በአመዳይ ውስጥ ብታጠብ፥ እጆቼንም እጅግ ባነጻ፥
31 ፤ በአዘቅት ውስጥ ታሰጥመኛለህ፥ ልብሴም ይጸየፈኛል።
32 ፤ እንድመልስለት አብረን ወደ ፍርድ እንገባ ዘንድ፥ እርሱ እንደ እኔ ሰው አይደለም።
33 ፤ እጁን በሁለታችን ላይ የሚያኖር ዳኛ በመካከላችን ምነው በተገኘ!
34 ፤ በትሩን ከእኔ ላይ ያርቅ፥ ግርማውም አያስፈራኝ፤
35 ፤ እናገርም ነበር፥ አልፈራውምም ነበር፤ በራሴ እንዲህ አይደለሁምና።