ምዕራፍ 39

የበረሃ ፍየል የምትወልድበትን ጊዜ ታውቃለህን? ዋላይቱስ የምታምጥበትን ጊዜ ትመለከታለህን?
2 ፤ እርስዋ የምትፈጽመውንስ ወራት ትቈጥራለህን? የምትወልድበትንስ ጊዜ ታውቃለህን?
3 ፤ ይንበረከካሉ፥ ልጆቻቸውንም ይወልዳሉ፥ ከምጣቸውም ያርፋሉ።
4 ፤ ልጆቻቸው ይጠነክራሉ፥ በሜዳም ያድጋሉ፤ ይወጣሉ፥ ወደ እነርሱም አይመለሱም።
5 ፤ የሜዳውስ አህያ አርነት ማን አወጣው? የበረሃውንስ አህያ ከእስራቱ ማን ፈታው?
6 ፤ በረሃውን ለእርሱ ቤት አድርጌ ሰጠሁት፤ መኖሪያውም በጨው ምድር ነው።
7 ፤ በከተማ ውካታ ይዘብታል፤ የነጂውን ጩኸት አይሰማም።
8 ፤ ተራራውን እንደ መሰምርያው ይመለከተዋል፥ ለምለሙንም ሁሉ ይፈልጋል።
9 ፤ ጐሽ ያገለግልህ ዘንድ ይታዘዛልን? ወይስ በግርግምህ አጠገብ ያድራልን?
10 ፤ ጐሽ ይተልምልህ ዘንድ ትጠምደዋለህን? ወይስ ከአንተ በኋላ በእርሻ ላይ ይጐለጕላልን?
11 ፤ ጕልበቱስ ብርቱ ስለ ሆነ ትታመነዋለህን? ተግባርህንስ ለእርሱ ትተዋለህን?
12 ፤ ዘርህንስ ይመልስልህ ዘንድ፥ በአውድማህስ ያከማችልህ ዘንድ ትታመነዋለህን?
13 ፤ የሰጐን ክንፍ በደስታ ይንቀሳቀሳል፤ ነገር ግን ክንፉና ላባው ጭምተኛ ነውን?
14 ፤ እንቍላልዋን በመሬት ላይ ትተዋለች፥ በአፈርም ውስጥ ታሞቀዋለች፤
15 ፤ እግር ይሰብረው ዘንድ፥ የምድረ በዳም አውሬ ይረግጠው ዘንድ ትረሳለች።
16 ፤ የእርስዋ እንዳልሆኑ በልጆችዋ ትጨክናለች። በከንቱም ብትሠራ አትፈራም፤
17 ፤ እግዚአብሔር ጥበብን ከእርስዋ ከልክሎአልና፥ ማስተዋልንም አልሰጣትምና።
18 ፤ ወደ ላይ ከፍ ከፍ ስትል በፈረስና በፈረሰኛው ትሳለቃለች።
19 ፤ ለፈረስ ጕልበቱን ሰጥተኸዋልን? አንገቱንስ ጋማ አልብሰኸዋልን?
20 ፤ እንደ አንበጣስ አፈናጠርኸውን? የማንኰራፋቱ ክብር የሚያስፈራ ነው።
21 ፤ በኮቴው በሸለቆው ውስጥ ይጐደፍራል፥ በጉልበቱም ደስ ይለዋል፤ ሰይፍም የታጠቁትን ለመገናኘት ይወጣል።
22 ፤ በፍርሃት ላይ ይስቃል፥ እርሱም አይደነግጥም፤ ከሰይፍም ፊት አይመለስም።
23 ፤ በእርሱ ላይ የፍላጻ ኮረጆና ብልጭልጭ የሚል ጦር ሰላጢንም ያንኳኳሉ።
24 ፤ በጭካኔና በቍጣ መሬትን ይውጣል፤ የመለከትም ድምፅ ቢሰማ አይቆምም።
25 ፤ የመለከትም ድምፅ ሲሰማ። እሰይ! ይላል፤ ከሩቅ ሆኖ ሰልፍንና የአለቆቹን ጩኸት፥ የሠራዊቱንም ውካታ ያሸታል።
26 ፤ በውኑ ከጥበብህ የተነሣ ጭልፊት ያንዣብባልን? ወይስ ክንፎቹን ወደ ደቡብ ይዘረጋልን?
27 ፤ በአፍህ ትእዛዝ ንስር ከፍ ከፍ ይላልን? ቤቱንስ በአርያም ላይ ያደርጋልን?
28 ፤ በገደል ላይ ይኖራል፤ በገደሉ ገመገምና በጥጉ ያድራል።
29 ፤ በዚያም ሆኖ የሚነጥቀውን ይጐበኛል፤ ዓይኑም በሩቅ ትመለከታለች።
30 ፤ ጫጩቶቹም ደም ይጠጣሉ፤ በድን ባለባትም ስፍራ እርሱ በዚያ አለ።