መጽሐፈ ኢዮብ።
ምዕራፍ 13
እነሆ፥ ይህን ሁሉ ዓይኔ አየች፤  ጆሮዬም ሰምታ አስተዋለችው።
2 ፤ እናንተ የምታውቁትን እኔ ደግሞ አውቃለሁ፤  ከእናንተ የማንስ አይደለሁም።
3 ፤ ነገር ግን ሁሉን ለሚችል አምላክ መናገር እፈልጋለሁ፥  ከእግዚአብሔርም ጋር ለመዋቀስ እሻለሁ።
4 ፤ እናንተ ግን በሐሰት ለባጮች ናችሁ፤  ሁላችሁ የማትጠቅሙ ባለ መድኃኒቶች ናችሁ።
5 ፤ ምነው ዝም ብላችሁ ብትኖሩ!  ይህ ጥበብ በሆነላችሁ ነበር።
6 ፤ አሁንም ክርክሬን ስሙ፥  የከንፈሬንም ሙግት አድምጡ።
7 ፤ በውኑ ስለ እግዚአብሔር ሐሰትን ትናገራላችሁን?  ስለ እርሱም ሽንገላን ታወራላችሁን?
8 ፤ ለፊቱስ ታደላላችሁን?  ስለ እግዚአብሔርስ ትከራከራላችሁን?
9 ፤ ቢመረምራችሁስ መልካም ይሆንልችኋልን?  ወይስ በሰው እንደምትሳለቁ ትሳለቁበታላችሁን?  
10 ፤ በስውር ለሰው ፊት ብታደሉ  ዘለፋ ይዘልፋችኋል።  
11 ፤ ክብሩስ አያስፈራችሁምን?  ግርማውስ አይወድቅባችሁምን?  
12 ፤ ምስሌዎቻችሁ የአመድ ምሳሌዎች ናቸው፤  ምሽጎቻችሁ የጭቃ ምሽጎች ናቸው።  
13 ፤ ዝም በሉ፥ እናገርም ዘንድ ተዉኝ፤  የሆነው ነገር ይምጣብኝ።  
14 ፤ ሥጋዬን በጥርሴ እይዛለሁ፥  ሕይወቴንም በእጄ አኖራለሁ።  
15 ፤ እነሆ፥ ቢገድለኝ ስንኳ እርሱን በትዕግሥት እጠባበቃለሁ፤  ነገር ግን መንገዴን በፊቱ አጸናለሁ።  
16 ፤ ዝንጉ ሰው በፊቱ አይገባምና  እርሱ መድኃኒት ይሆንልኛል።  
17 ፤ ነገሬን ተግታችሁ ስሙ፥  ምስክርነቴንም በጆሮአችሁ አድምጡ።  
18 ፤ እነሆ፥ ሙግቴን አዘጋጅቻለሁ።  እንደምጸድቅም አውቃለሁ።  
19 ፤ ከእኔስ ጋር የሚፋረድ ማን ነው?  አሁን እኔ ዝም ብል እሞታለሁ።  
20 ፤ ነገር ግን ሁለት ነገር አታድርግብኝ፤  የዚያን ጊዜ ከፊትህ አልሰወርም፤  
21 ፤ እጅህን ከእኔ አርቅ፤  ግርማህም አታስደንግጠኝ።  
22 ፤ ከዚያም በኋላ ጥራኝ፥ እኔም እመልስልሃለሁ።  ወይም እኔ ልናገር፥ አንተም መልስልኝ።  
23 ፤ ያለብኝስ በደልና ኃጢአት ምን ያህል ነው?  መተላለፌንና ኃጢአቴን አስታውቀኝ።  
24 ፤ ፊትህን ከእኔ የሰወርህ፥  እንደ ጠላትህም የቈጠርኸኝ ስለ ምን ነው?  
25 ፤ የረገፈውን ቅጠል ታስጨንቃለህን?  ወይስ የደረቀውን ዕብቅ ታሳድዳለህን?  
26 ፤ የመረረ ነገር ጽፈህብኛልና፤  የሕፃንነቴንም ኃጢአት ታወርሰኛለህ።  
27 ፤ እግሬንም በእግር ግንድ አግብተሃል፥  መንገዴንም ሁሉ መርምረሃል፤  የእግሬን ፍለጋ ወስነሃል።  
28 ፤ እኔ እንደሚጠፋ በስባሳ ነገር፥  ብልም እንደሚበላው ልብስ ነኝ።