ምዕራፍ 21

ኢዮብም መለሰ እንዲህም አለ።
2 ፤ ስሙ፥ ቃሌን ስሙ፤ ይህም መጽናናታችሁ ይሁን።
3 ፤ እናገር ዘንድ ተዉኝ፤ ከተናገርሁም በኋላ ተሳለቁ።
4 ፤ በውኑ የኀዘን እንጉርጕሮዬ ለሰው እናገራለሁን? አለመታገሥ ስለ ምን አይገባኝም?
5 ፤ ወደ እኔ ተመልከቱ፥ ተደነቁም፤ እጃችሁንም በአፋችሁ ላይ አኑሩ።
6 ፤ እኔ ባሰብሁ ቍጥር እጨነቃለሁ፥ ፃዕርም ሥጋዬን ይይዛል።
7 ፤ ስለ ምን ኃጢአተኞች በሕይወት ይኖራሉ? ስለ ምንስ ያረጃሉ? በባለጠግነትስ ስለ ምን ይበረታሉ?
8 ፤ ዘራቸው ከእነርሱ ጋር ጸንቶ ይኖራል፥ ልጆቻቸውም በዓይናቸው ፊት ናቸው።
9 ፤ ቤታቸው ከፍርሃት ወጥቶ የታመነ ነው፥ የእግዚአብሔርም በትር የለባቸውም።
10 ፤ ኮርማቸው ይወልዳል፥ ዘሩንም አይጥለውም፤ ላማቸውም ትወልዳለች፥ አትጨነግፍም።
11 ፤ ሕፃናቶቻቸውን እንደ መንጋ ያወጣሉ፥ ልጆቻቸውም ይዘፍናሉ።
12 ፤ ከበሮና መሰንቆ ወስደው ይዘምራሉ፥ በእምቢልታ ድምፅ ደስ ይላቸዋል።
13 ፤ ዕድሜያቸውንም በተድላ ይፈጽማሉ፤ ድንገትም ወደ ሲኦል ይወርዳሉ።
14 ፤ እግዚአብሔርንም። ከእኛ ዘንድ ራቅ፤ መንገድህን እናውቅ ዘንድ አንወድድም።
15 ፤ እናመልከውስ ዘንድ ሁሉን የሚችል አምላክ ማን ነው? ወይስ ወደ እርሱ ብንጸልይ ምን ይጠቅመናል? ይላሉ።
16 ፤ እነሆ፥ ሀብታቸው በእጃቸው ውስጥ አይደለምን? የኃጥአን ምክር ከእኔ ዘንድ የራቀች ናት።
17 ፤ የኃጥአን መብራት የጠፋው፥ መቅሠፍትም የመጣባቸው፥ እግዚአብሔርም በቍጣው መከራ የከፈላቸው፥
18 ፤ በነፋስ ፊት እንደ ገለባ፥ ዐውሎ ነፋስም እንደሚወስደው ትቢያ የሆኑ ስንት ጊዜ ነው?
19 ፤ እናንተ። እግዚአብሔር በደላቸውን ለልጆቻቸው ይጠብቃል ብላችኋል። እነርሱ ያውቁ ዘንድ ፍዳን ለራሳቸው ይክፈል።
20 ፤ ዓይኖቻቸው ጥፋታቸውን ይዩ፥ ሁሉን ከሚችል አምላክ ቍጣ ይጠጡ።
21 ፤ የወራታቸውስ ቍጥር ቢቈረጥ፥ ከእነርሱ በኋላ የቤታቸው ደስታ ምን ይሆናቸዋል?
22 ፤ ከፍ ከፍ ባሉትስ ላይ ለሚፈርድ ለእግዚአብሔር በውኑ ሰው እውቀትን ያስተምራልን?
23 ፤ አንድ ሰው በሰላም ተዘልሎ ሲቀመጥ በሙሉ ኃይሉ ሳለ ይሞታል።
24 ፤ በአንጀቱ ውስጥ ስብ ሞልቶአል፥ የአጥንቶቹም ቅልጥም ረጥቦአል።
25 ፤ ሌላውም ሰው መልካምን ነገር ከቶ ሳይቀምስ በተመረረች ነፍስ ይሞታል።
26 ፤ በአፈር ውስጥ በአንድ ላይ ይተኛሉ፥ ትልም ይከድናቸዋል።
27 ፤ እነሆ፥ አሳባችሁን፥ የመከራችሁብኝንም ክፉ ምክር አውቄዋለሁ።
28 ፤ እናንተ። የከበርቴው ቤት የት ነው? ኃጢአተኛውም ያደረበት ድንኳን የት ነው? ብላችኋል።
29 ፤ መንገድ አላፊዎችን አልጠየቃችሁምን? ምልክታቸውን አታውቁምን?
30 ፤ ኃጢአተኛው በመቅሠፍት ቀን እንደ ተጠበቀ፥ በቍጣው ቀን እንደሚድን።
31 ፤ መንገዱን በፊቱ የሚናገር ማን ነው? የሠራውንስ የሚመልስበት ማን ነው?
32 ፤ እርሱን ግን ወደ መቃብር ይሸከሙታል፥ ሰዎቹም በመቃብሩ ላይ ይጠብቃሉ።
33 ፤ የሸለቆው ጓል ይጣፍጥለታል፤ በኋላውም ሰው ሁሉ ይሳባል፥ በፊቱም ቍጥር የሌለው ጉባኤ አለ።
34 ፤ የምትመልሱልኝ ውስልትና ነውና በከንቱ እንዴት ታጽናኑኛላችሁ?