መጽሐፈ ዜና መዋዕል ቀዳማዊ።

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25 26 27 28 29


ምዕራፍ 5

የእስራኤልም በኵር የሮቤል ልጆች እነዚህ ናቸው። እርሱ የበኵር ልጅ ነበረ፤ ነገር ግን የአባቱን ምንጣፍ ስላረከሰ ብኵርናው ለእስራኤል ልጅ ለዮሴፍ ልጆች ተሰጠ፤ ትውልዱ ግን ከብኵርና ጋር አልተቈጠረም።
2 ፤ ይሁዳም በወንድሞቹ መካከል በረታ፥ አለቃም ከእርሱ ሆነ፤ ብኵርናው ግን ለዮሴፍ ነበረ።
3 ፤ የእስራኤል በኵር የሮቤል ልጆች፤ ሄኖኅ፥ ፈሉሶ፥ አስሮን፥ ከርሚ ነበሩ።
4 ፤ የኢዮኤል ልጆች፤ ልጁ ሸማያ፥
5 ፤ ልጁ ጎግ፥ ልጁ ሰሜኢ፥ ልጁ ሚካ፥
6 ፤ ልጁ ራያ፥ ልጁ ቢኤል፥ የአሦር ንጉሥ ቴልጌልቴልፌልሶር የማረከው ልጁ ብኤራ፤ እርሱ የሮቤል ነገድ አለቃ ነበረ።
7 ፤ ወንድሞቹ በየወገናቸው የትውልዶቻቸው መዝገብ በተቈጠረ ጊዜ፤ አንደኛው ኢዮኤል፥
8 ፤ ዘካርያስ፥ እስከ ናባውና እስከ በኣልሜዎን ድረስ በአሮዔር የተቀመጠው የኢዮኤል ልጅ የሽማዕ ልጅ የዖዛዝ ልጅ ቤላ፤
9 ፤ በገለዓድ ምድር እንስሶቻቸው በዝተው ነበርና በምሥራቅ በኩል ከኤፍራጥስ ወንዝ ጀምሮ እስከ ምድረ በዳው መግቢያ ድረስ ተቀመጠ።
10 ፤ በሳኦልም ዘመን ከአጋራውያን ጋር ተዋጉ፥ እነርሱም በእጃቸው ተመትተው ወደቁ፤ በገለዓድ ምሥራቅ በኩል ባለው አገር ሁሉ በድንኳኖቻቸው ተቀመጡ።
11 ፤ የጋድም ልጆች በባሳን ምድር እስከ ሰልካ ድረስ በአፋዛዣቸው ተቀመጡ።
12 ፤ አንደኛው ኢዮኤል፥ ሁለተኛው ሳፋም፥ ያናይ፥ ሳፋጥ በበሳን ተቀመጡ።
13 ፤ የአባቶቻቸውም ቤቶች ወንድሞች ሚካኤል፥ ሜሱላም፥ ሳባ፥ ዮራይ፥ ያካን፥ ዙኤ፥ ኦቤድ ሰባት ነበሩ።
14 ፤ እነዚህም የቡዝ ልጅ የዬዳይ ልጅ የኢዬሳይ ልጅ የሚካኤል ልጅ የገለዓድ ልጅ የኢዳይ ልጅ የዑሪ ልጅ የአቢካኢል ልጆች ነበሩ።
15 ፤ የአባቶቻቸውም ቤቶች አለቃ የጉኒ ልጅ የአብዲኤል ልጅ ወንድም ነበረ።
16 ፤ በገለዓድም ምድር በባሳን በመንደሮቹም በሳሮንም መሰምርያዎች ሁሉ እስከ ዳርቻቸው ድረስ ተቀምጠው ነበር።
17 ፤ እነዚህ ሁሉ በትውልዶቻቸው በይሁዳ ንጉሥ በኢዮአታም ዘመንና በእስራኤል ንጉሥ በኢዮርብዓም ዘመን ተቈጠሩ።
18 ፤ የሮቤልና የጋድ ልጆች የምናሴም ነገድ እኵሌታ፥ ጽኑዓን፥ ጋሻና ሰይፍ የሚይዙ፥ ቀስተኞችም፥ ሰልፍ የሚያውቁ ሰልፈኞችም፥ አርባ አራት ሺህ ሰባት መቶ ስድሳ ነበሩ።
19 ፤ ከአጋራውያንና ከኢጡር ከናፌስና ከናዳብ ጋር ተዋጉ።
20 ፤ በሚዋጉበትም ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኸዋልና፥ በእርሱም ታምነዋልና ተለመናቸው፤ በላያቸውም ረዳት ሆናቸው፥ አጋራውያንና ከእነርሱ ጋር የነበሩትም ሁሉ በእጃቸው ተሰጡ።
21 ፤ ከከብቶቻቸውም አምሳ ሺህ ግመሎች፥ ሁለት መቶ አምሳ ሺህም በጎች፥ ሁለት ሺህም አህዮች፥ ከሰዎችም መቶ ሺህ ማረኩ።
22 ፤ ሰልፉ ከእግዚአብሔር ዘንድ ነበረና ብዙ ሰዎች ተገድለው ወደቁ፤ እስከ ምርኮም ዘመን ድረስ በስፍራቸው ተቀመጡ።
23 ፤ የምናሴ የነገድ እኵሌታ ልጆች በምድሪቱ ተቀመጡ። ከባሳንም ጀምሮ እስከ በኣልአርሞንዔምና እስከ ሳኔር እስከ አርሞንዔም ተራራ ድረስ በዙ።
24 ፤ የአባቶቻቸውም ቤቶች አለቆች እነዚህ ነበሩ፤ ዔፌር፥ ይሽዒ፥ ኤሊኤል፥ ዓዝርኤል፥ ኤርምያ፥ ሆዳይዋ፥ ኢየድኤል፤ እነርሱ ጽኑዓን ኃያላን የታወቁ ሰዎች የአባቶቻቸውም ቤቶች አለቆች ነበሩ።
25 ፤ የአባቶቻቸውንም አምላክ በደሉ፥ እግዚአብሔርም ከፊታቸው ባጠፋቸው በምድሩ አሕዛብ አማልክት አመነዘሩ።
26 ፤ የእስራኤልም አምላክ የአሦርን ንጉሥ የፎሐን መንፈስ፥ የአሦርንም ንጉሥ የቴልጌልቴልፌልሶርን መንፈስ አስነሣ፤ የሮቤልንና የጋድን ልጆች የምናሴንም ነገድ እኵሌታ አፈለሰ፥ እስከ ዛሬም ወዳሉበት ወደ አላሔና ወደ ኦቦር፥ ወደ ሃራና ወደ ጎዛን ወንዝ አመጣቸው።