መጽሐፈ ዜና መዋዕል ቀዳማዊ።

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25 26 27 28 29


ምዕራፍ 18

ከዚህም በኋላ ዳዊት ፍልስጥኤማውያንን መታ፥ አዋረዳቸውም፥ ከፍልስጥኤማውያንም እጅ ጌትንና መንደሮችዋን ወሰደ።
2 ፤ ሞዓብን መታ፤ ሞዓባውያንም ለዳዊት ገባሮች ሆኑ፤ ግብርም አመጡለት።
3 ፤ ዳዊትም በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ የነበረውን ግዛት ለመያዝ በሄደ ጊዜ የሱባን ንጉሥ አድርአዛርን እስከ ሃማት ድረስ መታ።
4 ፤ ዳዊትም ከእርሱ አንድ ሺህ ሰረገሎች፥ ሰባት ሺህም ፈረሰኞች፥ ሀያ ሺህም እግረኞች ወሰደ፤ ዳዊት ለመቶ ሰረገሎች የሚሆኑትን ብቻ አስቀርቶ የሰረገሎቹን ፈረሶች ቋንጃ ቆረጠ።
5 ፤ ከደማስቆም ሶርያውያን የሱባን ንጉሥ አድርአዛርን ሊረዱ በመጡ ጊዜ ዳዊት ከሶርያውያን ሀያ ሁለት ሺህ ሰዎችን ገደለ።
6 ፤ ዳዊትም በደማስቆ ሶርያ ጭፍሮች አኖረ፤ ሶርያውያንም ለዳዊት ገባሮች ሆኑ፥ ግብርም አመጡለት። እግዚአብሔርም ዳዊት በሄደበት ሁሉ ድል ይሰጠው ነበር።
7 ፤ ዳዊትም ለአድርአዛር ባሪያዎች የነበሩትን የወርቅ ጋሻዎች ወሰደ፥ ወደ ኢየሩሳሌምም ይዞአቸው መጣ።
8 ፤ ከአድርአዛርም ከተሞች ከጢብሐትና ከኩን ዳዊት እጅግ ብዙ ናስ ወሰደ፤ ከዚህም ሰሎሞን የናሱን ኵሬና ዓምዶች የናሱንም ዕቃ ሠራ።
9 ፤ የሐማትም ንጉሥ ቶዑ ዳዊት የሱባን ንጉሥ የአድርአዛርን ጭፍራ ሁሉ እንደ መታ ሰማ።
10 ፤ ቶዑም ከአድርአዛር ጋር ሁል ጊዜ ይዋጋ ነበርና ዳዊት አድርአዛርን ወግቶ ስለመታው ደኅንነቱን ይጠይቅ ዘንድ ይመርቀውም ዘንድ ልጁን አዶራምን ወደ ዳዊት ላከው፤ እርሱም የወርቅና የብር የናስም ዕቃ ይዞ መጣ።
11 ፤ ንጉሡም ዳዊት ከአሕዛብ ሁሉ ከኤዶምና ከሞዓብ ከአሞንም ልጆች ከፍልስጥኤማውያንም ከአማሌቅም ከማረከው ብርና ወርቅ ጋር እነዚህን ደግሞ ለእግዚአብሔር ቀደሰ።
12 ፤ ደግሞ የጽሩያ ልጅ አቢሳ ከኤዶማውያን በጨው ሸለቆ ውስጥ አሥራ ስምንት ሺህ ሰዎች ገደለ።
13 ፤ በኤዶምያስም ጭፍሮች አኖረ፥ ኤዶማውያንም ሁሉ ለዳዊት ገባሮች ሆኑ። እግዚአብሔርም ዳዊት በሄደበት ሁሉ ድል ይሰጠው ነበር።
14 ፤ ዳዊትም በእስራኤል ሁሉ ላይ ነገሠ፤ ለሕዝቡም ሁሉ ፍርድንና ጽድቅም አደረገላቸው።
15 ፤ የጽሩያ ልጅ ኢዮአብም የሠራዊት አለቃ ነበረ፤ የአሒሉድም ልጅ ኢዮሣፍጥ ታሪክ ጸሐፊ ነበረ።
16 ፤ የአኪጦብም ልጅ ሳዶቅ፥ የአቤሜሌክም ልጅ አብያታር ካህናት ነበሩ፤ ሱሳ ጸሐፊ ነበረ።
17 ፤ የዮዳሄ ልጅ በናያስ በከሊታውያንና በፈሊታውያን ላይ ነበረ፤ የዳዊትም ልጆች በንጉሡ አጠገብ አለቆች ነበሩ።