መጽሐፈ ዜና መዋዕል ቀዳማዊ።

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25 26 27 28 29


ምዕራፍ 10

ፍልስጥኤማውያንም ከእስራኤል ጋር ተዋጉ፤ የእስራኤልም ሰዎች ከፍልስጥኤማውያን ፊት ሸሹ፥ ተወግተውም በጊልቦአ ተራራ ላይ ወደቁ።
2 ፤ ፍልስጥኤማውያንም ሳኦልንና ልጆቹን በእግር በእግራቸው ተከትለው አባረሩአቸው፤ ፍልስጥኤማውያንም የሳኦልን ልጆች ዮናታንንና አሚናዳብን ሜልኪሳንም ገደሉ።
3 ፤ ሰልፍም በሳኦል ላይ ጠነከረ፥ ቀስተኞችም አገኙት፤ ከቀስተኞችም የተነሣ ተጨነቀ።
4 ፤ ሳኦልም ጋሻ ጃግሬውን። እነዚህ ቈላፋን መጥተው እንዳይዘብቱብኝ ሰይፍህን መዝዘህ ውጋኝ አለው። ጋሻ ጃግሬው ግን እጅግ ፈርቶ ነበርና እንቢ አለ። ሳኦልም ሰይፉን ወስዶ በላዩ ወደቀ።
5 ፤ ጋሻ ጃግሬውም ሳኦል እንደ ሞተ ባየ ጊዜ እርሱ ደግሞ በሰይፉ ላይ ወድቆ ሞተ።
6 ፤ ሳኦልና ሦስቱ ልጆቹ የቤቱም ሰዎች ሁሉ በአንድ ላይ ሞቱ።
7 ፤ በሸለቆውም የነበሩት የእስራኤል ሰዎች ሁሉ እንደ ሸሹ፥ ሳኦልና ልጆቹም እንደ ሞቱ ባዩ ጊዜ ከተሞቻቸውን ለቅቀው ሸሹ፤ ፍልስጥኤማውያንም መጥተው ተቀመጡባቸው።
8 ፤ በነጋውም ፍልስጥኤማውያን የሞቱትን ለመግፈፍ በመጡ ጊዜ ሳኦልንና ልጆቹን በጊልቦአ ተራራ ላይ ወድቀው አገኙአቸው።
9 ፤ ገፈፉትም፥ ራሱንና መሣሪያውንም አንሥተው ለጣኦቶቻቸውና ለሕዝቡ የምሥራች ይወስዱ ዘንድ ወደ ፍልስጥኤማውያን አገር ዙሪያ ሰደዱ።
10 ፤ መሣሪያውንም በአምላኮቻቸው ቤት ውስጥ አኖሩ፤ ራሱንም በዳጎን ቤት ውስጥ ቸነከሩት።
11 ፤ የኢያቢስ ገለዓድም ሰዎች ሁሉ ፍልስጥኤማውያን በሳኦል ላይ ያደረጉትን ሁሉ በሰሙ ጊዜ፥
12 ፤ ጽኑአን ሰዎች ሁሉ ተነሥተው የሳኦልን ሬሳ የልጆቹንም ሬሳ ወሰዱ፥ ወደ ኢያቢስም አመጡአቸው፤ በኢያቢስም ካለው ከትልቁ ዛፍ በታች አጥንቶቻቸውን ቀበሩ፥ ሰባት ቀንም ጾሙ።
13 ፤ እንዲሁ ሳኦል በእግዚአብሔር ላይ ስላደረገው ኃጢአት፥ የእግዚአብሔርንም ቃል ስላልጠበቀ ሞተ። ደግሞም መናፍስት ጠሪ
14 ፤ ስለ ጠየቀ እግዚአብሔርንም ስላልጠየቀ፥ ስለዚህ ገደለው፥ መንግሥቱንም ወደ እሴይ ልጅ ወደ ዳዊት አሳለፈው።