መጽሐፈ ዜና መዋዕል ቀዳማዊ።

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25 26 27 28 29


ምዕራፍ 13

ዳዊትም ከሻለቆችና ከመቶ አለቆች ከአለቆቹም ሁሉ ጋር ተማከረ።
2 ፤ ዳዊትም የእስራኤልን ጉባኤ ሁሉ። መልካም መስሎ የታያችሁ እንደሆነ፥ ከአምላካችን ከእግዚአብሔርም ወጥቶ እንደ ሆነ፥ በእስራኤል አገር ሁሉ ለቀሩት ወንድሞቻችን በከተሞቻቸውና በመሰምሪያዎቻቸውም ለሚቀመጡ ካህናትና ሌዋውያን ወደ እኛ ይሰበሰቡ ዘንድ እንላክ፤
3 ፤ በሳኦልም ዘመን አልፈለግነውምና የአምላካችንን ታቦት ወደ እኛ እንመልስ አላቸው።
4 ፤ ነገሩም በሕዝቡ ሁሉ ዓይን ዘንድ ቅን ነበረና ጉባኤው ሁሉ። እንዲሁ እናደርጋለን አሉ።
5 ፤ የእግዚአብሔርንም ታቦት ከቂርያትይዓሪም ያመጡ ዘንድ ዳዊት እስራኤልን ሁሉ ከግብጽ ወንዝ ከሺሖር ጀምሮ እስከ ሐማት መግቢያ ድረስ ሰበሰበ።
6 ፤ ዳዊትም እስራኤልም ሁሉ በኪሩቤል ላይ የተቀመጠውን ስሙም በእርሱ የተጠራውን የአምላክን የእግዚአብሔርን ታቦት ከዚያ ያወጡ ዘንድ በይሁዳ ወዳለችው ቂርያትይዓሪም ወደ ተባለች ወደ በኣላ ሄዱ።
7 ፤ የእግዚአብሔርንም ታቦት በአዲስ ሰረገላ ላይ ጫኑት፥ ከአሚናዳብም ቤት አመጡት፤ ዖዛና አሒዮም ሠረገላውን ይነዱ ነበር።
8 ፤ ዳዊትና እስራኤል ሁሉ በቅኔና በበገና በመሰንቆና በከበሮ በጸናጽልና በመለከት በእግዚአብሔር ፊት በሙሉ ኃይላቸው ይጫወቱ ነበር።
9 ፤ ወደ ኪዶንም አውድማ በደረሱ ጊዜ በሬዎቹ ይፋንኑ ነበርና ታቦቱን ሊይዝ ዖዛ እጁን ዘረጋ።
10 ፤ የእግዚአብሔርም ቍጣ በዖዛ ላይ ነደደ፥ እጁንም ወደ ታቦቱ ስለ ዘረጋ ቀሠፈው፤ በዚያም በእግዚአብሔር ፊት ሞተ።
11 ፤ እግዚአብሔርም ዖዛን ስለ ቀሠፈው ዳዊት አዘነ፤ እስከ ዛሬም ድረስ የዚያን ስፍራ ስም የዖዛ ስብራት ብሎ ጠራው።
12 ፤ በዚያም ቀን ዳዊት። የእግዚአብሔርን ታቦት ወደ እኔ እንዴት አመጣለሁ ብሎ እግዚአብሔርን ፈራ።
13 ፤ ዳዊትም ታቦቱን ወደ ጌት ሰው ወደ አቢዳራ ቤት አሳለፈው እንጂ ወደ እርሱ ወደ ዳዊት ከተማ አላመጣውም።
14 ፤ የእግዚአብሔርም ታቦት በአቢዳራ ቤተሰብ ዘንድ በቤቱ ውስጥ ሦስት ወር ተቀመጠ፤ እግዚአብሔርም የአቢዳራን ቤትና ያለውን ሁሉ ባረከ።