መጽሐፈ ዜና መዋዕል ቀዳማዊ።
ምዕራፍ 17
እንዲህም ሆነ፤ ዳዊት በቤቱ በተቀመጠ ጊዜ ዳዊት ነቢዩን ናታንን። እነሆ፥ እኔ ከዝግባ በተሠራ ቤት ተቀምጫለሁ፤ የእግዚአብሔርም ቃል ኪዳን ታቦት በመጋረጃዎች ውስጥ ተቀምጦአል አለው።
2 ፤ ናታንም ዳዊትን። እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነውና በልብህ ያለውን ሁሉ አድርግ አለው።
3 ፤ በዚያም ሌሊት የእግዚአብሔር ቃል ወደ ናታን መጣ እንዲህም አለው።
4 ፤
5 ፤ ሂድ፥ ለባሪያዬ ለዳዊት ንገረው። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እስራኤልን ካወጣሁበት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ከድንኳን ወደ ድንኳን፥ ከማደሪያም ወደ ማደሪያ እሄድ ነበር እንጂ በቤት ውስጥ አልኖርሁምና የምኖርበትን ቤት አትሠራልኝም።
6 ፤ ከእስራኤል ሁሉ ጋር ባለፍሁበት ስፍራ ሁሉ። ስለ ምን ቤትን ከዝግባ እንጨት አልሠራችሁልኝም? ብዬ ሕዝቤን ይጠብቅ ዘንድ ከእስራኤል ፈራጆች ላዘዝሁት ለአንዱ በውኑ ተናግሬአለሁን?
7 ፤ አሁንም ባሪያዬን ዳዊትን እንዲህ በለው። የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። አንተ መንጋውን ስትከተል በሕዝቤ በእስራኤል ላይ አለቃ ትሆን ዘንድ ከበግ ጥበቃ ወሰድሁህ።
8 ፤ በሄድህበትም ሁሉ ከአንተ ጋር ነበርሁ፥ ጠላቶችህንም ሁሉ ከፊትህ አጠፋሁ፤ በምድርም ላይ እንዳሉ እንደታላላቆች ስም ለአንተ ስም አደርጋለሁ።
9 ፤
10 ፤ ለሕዝቤም ለእስራኤል ስፍራ አደርግለታለሁ፥ እተክለውማለሁ፥ በስፍራውም ይቀመጣል፥ ከዚያም በኋላ አይናወጥም፤ እንደቀድሞው ዘመንና በሕዝቤም በእስራኤል ላይ ፈራጆች እንዳስነሣሁበት ጊዜ ግፈኞች ተመልሰው አያስጨንቁትም፤ ጠላቶችህንም ሁሉ አዋርዳቸዋለሁ። እግዚአብሔር ደግሞ ቤት እንዲሠራልህ እነግርሃለሁ።
11 ፤ ወደ አባቶችህም ትሄድ ዘንድ ዕድሜህ በተፈጸመ ጊዜ ከልጆችህ የሚሆነውን ዘርህን ከአንተ በኋላ አስነሣለሁ፤ መንግሥቱንም አጸናለሁ።
12 ፤ እርሱ ቤት ይሠራልኛል፤ ዙፋኑንም ለዘላለም አጸናለሁ።
13 ፤ እኔም አባት እሆነዋለሁ፥ እርሱም ልጅ ይሆነኛል፤ ከአንተ አስቀድሞ ከነበረው እንዳራቅሁ፥ ምሕረቴን ከእርሱ አላርቅም።
14 ፤ በቤቴና በመንግሥቴም ለዘላለም አቆመዋለሁ፤ ዙፋኑም ለዘላለም ይጸናል።
15 ፤ እንደዚህ ነገር ሁሉ እንደዚህም ራእይ ሁሉ ናታን ለዳዊት ነገረው።
16 ፤ ንጉሡም ዳዊት ገባ፥ በእግዚአብሔርም ፊት ተቀምጦ እንዲህ አለ። አቤቱ አምላክ ሆይ፥ እስከዚህ ያደረስኸኝ እኔ ማን ነኝ? ቤቴስ ምንድር ነው?
17 ፤ አምላክ ሆይ ይህ በፊትህ ጥቂት ነበረ፤ አቤቱ አምላክ ሆይ፥ ስለ ባሪያህ ቤት ደግሞ ለሩቅ ዘመን ተናገርህ፤ እንደ አንድ ባለ ማዕርግ ሰው ተመለከትኸኝ።
18 ፤ አንተ ባሪያህን ታውቀዋለህና ለባሪያህ ስለ ተደረገ ክብር ዳዊት ጨምሮ የሚለው ምንድር ነው?
19 ፤ አቤቱ፥ ይህን ታላቅ ነገር ሁሉ ታስታውቀው ዘንድ ስለ ባሪያህ እንደ ልብህም ይህን ታአምራት ሁሉ አድርገሃል።
20 ፤ አቤቱ፥ እንዳንተ ያለ የለም፥ በጆሮአችንም እንደሰማን ሁሉ ከአንተ በቀር አምላክ የለም።
21 ፤ አንተ እግዚአብሔር ከግብጽ ካወጣኸው ከሕዝብህ ፊት አሕዛብን በማሳደድ በታላቅና በሚያስፈራ ነገር ለአንተ ስም ታደርግ ዘንድ፥ ለአንተም ሕዝብ ትቤዥ ዘንድ እንደሄድህለት እንዳንተ ሕዝብ እንደ እስራኤል ያለ በምድር ላይ ሌላ ሕዝብ አለን?
22 ፤ ሕዝብህንም እስራኤልን ለዘላለም ሕዝብህ አደረግኸው፤ አንተም፥ አቤቱ፥ አምላክ ሆነኸዋል።
23 ፤ አሁንም፥ አቤቱ፥ ስለ ባሪያህና ስለ ቤቱ የተናገርኸው ለዘላለም የጸና ይሁን፤ እንደተናገርህም አድርግ።
24 ፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እርሱ የእስራኤል አምላክ ነው፥ በእውነት የእስራኤል አምላክ ነው ይባል ዘንድ ስምህ ለዘላለም ጽኑና ታላቅ ይሁን፤ የባሪያህም የዳዊት ቤት በፊትህ ጸንቶአል።
25 ፤ አምላኬ ሆይ፥ ቤት እንድሠራለት ለባሪያህ ገልጠሃልና ስለዚህ ባሪያህ ወዳንተ ይጸልይ ዘንድ በልቡ ደፈረ።
26 ፤ አሁንም፥ አቤቱ፥ አንተ አምላክ ነህ፥ ይህንም መልካም ነገር ለባሪያህ ተናግረሃል።
27 ፤ አሁንም በፊትህ ለዘላለም ይኖር ዘንድ የባሪያህን ቤት እንድትባርክ ፈቅደሃል፤ አንተም፥ አቤቱ፥ ባርከኸዋል፥ ለዘላለምም ቡሩክ ይሆናል።