መጽሐፈ ዜና መዋዕል ቀዳማዊ።

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25 26 27 28 29


ምዕራፍ 12

በጺቅላግም ከቂስ ልጅ ከሳኦል በተሸሸገ ጊዜ ወደ ዳዊት የመጡ እነዚህ ናቸው፤ በሰልፍም ባገዙት ኃያላን መካከል ነበሩ።
2 ፤ ቀስተኞችም ነበሩ፥ በቀኝና በግራም እጃቸው ድንጋይ ሊወነጭፉ ፍላጻም ሊወረውሩ ይችሉ ነበር፤ ከብንያም ወገን የሳኦል ወንድሞች ነበሩ።
3 ፤ አለቃቸው አሒዔዝር ነበረ፥ ከእርሱም በኋላ ኢዮአስ፥ የጊብዓዊው የሸማዓ ልጆች፤ ይዝኤል፥ ፋሌጥ፥ የዓዝሞት ልጆች፤ በራኪያ፥ ዓናቶታዊው ኢዩ፥
4 ፤ ገባዖናዊው ሰማያስ፥ እርሱ በሠላሳው መካከልና በሠላሳው ላይ ኃያል ሰው ነበረ፤ ኤርምያስ፥ የሕዚኤል፥ ዮሐናን፥
5 ፤ ገድሮታዊው ዮዛባት፥ ኤሉዛይ፥ ኢያሪሙት፥ በዓልያ፥ ሰማራያ፥ ሀሩፋዊው ሰፋጥያስ፥
6 ፤ ቆርያውያን ሕልቃና፥ ይሺያ፥ አዛርኤል፥ ዮዛር፥ ያሾቢአም፤
7 ፤ የጌዶር ሰው የይሮሃም ልጆች የኤላ፥ ዝባድያ
8 ፤ ዳዊትም ከምድረ በዳ ውስጥ ባለችው በአንባይቱ ሳለ ከጋድ ወገን የሆኑ እነዚህ ጋሻና ጦር የሚይዙ፥ ጽኑዓን ኃያላን፥ ሰልፈኞች፥ ወደ እርሱ ተጠጉ፤ ፊታቸውም እንደ አንበሳ ፊት ነበረ፥ በተራራም ላይ እንደሚዘልል ሚዳቋ ፈጣኖች ነበሩ።
9 ፤ አለቃው ዔጼር፥ ሁለተኛው አብድዩ፥
10 ፤ ሦስተኛው ኤልያብ፥ አራተኛው መስመና፥
11 ፤ አምስተኛው ኤርምያስ፥ ስድስተኛው አታይ፥
12 ፤ ሰባተኛው ኤሊኤል፥ ስምንተኛው ዮሐናን፥
13 ፤ ዘጠነኛው ኤልዛባድ፥ አሥረኛው ኤርምያስ፥ አሥራ አንደኛው መክበናይ።
14 ፤ እነዚህ የጋድ ልጆች የጭፍራ አለቆች ነበሩ፤ ከእነርሱም ታናሹ ከመቶ፥ ታላቁ ከሺህ ይመዛዘኑ ነበር።
15 ፤ በመጀመሪያው ወር ዮርዳኖስ ከዳር እስከ ዳር ሞልቶ በነበረ ጊዜ የተሻገሩት እነዚህ ናቸው፤ በሸለቆውም ውስጥ በምሥራቅና በምዕራብ በኩል የተቀመጡትን ሁሉ አባረሩ።
16 ፤ ዳዊትም ወደነበረባት ወደ አምባይቱ ከብንያምና ከይሁዳ ወገን ሰዎች መጡ።
17 ፤ ዳዊትም ሊገናኛቸው ወጥቶ። ትረዱኝ ዘንድ በሠላም ወደ እኔ መጥታችሁ እንደ ሆነ ልቤ ከእናንተ ጋር አንድ ይሆናል፤ ለጠላቶቼ አሳልፋችሁ ልትሰጡኝ መጥታችሁ እንደሆነ ግን፥ በእጄ ዓመፅ የለብኝምና የአባቶቻችን አምላክ ይመልከተው፥ ይፍረደውም አላቸው።
18 ፤ መንፈስም በሠላሳው አለቃ በአማሳይ ላይ መጣ፥ እርሱም። ዳዊት ሆይ፥ እኛ የአንተ ነን፤ የእሴል ልጅ ሆይ፥ እኛ ከአንተ ጋር ነን፤ አምላክህ ይረዳሃልና ሰላም ሰላም ለአንተ ይሁን፥ ለሚረዱህም ሰላም ይሁን አለ። ዳዊትም ተቀበላቸው፥ የጭፍራም አለቆች አደረጋቸው።
19 ፤ ዳዊትም ከፍልስጥኤማውያን ጋር ሳኦልን ሊወጋ በመጣ ጊዜ ከምናሴ ወገን ሰዎች ወደ ዳዊት ከዱ፤ የፍልስጥኤማውያን አለቆች ግን። በራሳችን ላይ ጕዳት አድርጎ ወደ ጌታው ወደ ሳኦል ይመለሳል ሲሉ ተማክረው ሰድደውታልና እነርሱ አልረዷቸውም።
20 ፤ ወደ ጺቅላግም ሲሄድ ከምናሴ ወገን የምናሴ ሻለቆች የነበሩ ዓድና፥ ዮዛባት፥ ይዲኤል፥ ሚካኤል፥ ዮዛባት፥ ኤሊሁ፥ ጺልታይ ወደ እርሱ ከዱ።
21 ፤ ሁሉም ጽኑዓን ኃያላንና በሠራዊቱ ላይ አለቆች ነበሩና በአደጋ ጣዮቹ ላይ ዳዊትን አገዙት።
22 ፤ እንደ እግዚአብሔርም ሠራዊት ታላቅ ሠራዊት እስኪሆን ድረስ ዳዊትን ለመርዳት ዕለት ዕለት ይመጡ ነበር።
23 ፤ እንደ እግዚአብሔርም ቃል የሳኦልን መንግሥት ወደ እርሱ ይመልሱ ዘንድ በኬብሮን ሳለ ወደ ዳዊት የመጡት የሠራዊቱ አለቆች ቍጥር ይህ ነው።
24 ፤ ጋሻና ጦር ተሸክመው ለሰልፍ የተዘጋጁ የይሁዳ ልጆች ስድስት ሺህ ስምንት መቶ ነበሩ።
25 ፤ ለሰልፍ ጽኑዓን ኃያላን ሰዎች የነበሩ የስምዖን ልጆች ሰባት ሺህ አንድ መቶ ነበሩ።
26 ፤ የሌዊ ልጆች አራት ሺህ ስድስት መቶ ነበሩ።
27 ፤ የአሮንም ቤት አለቃ ዮዳሄ ነበረ፥ ከእርሱም ጋር ሦስት ሺህ ሰባት መቶ ነበሩ፤
28 ፤ ከእርሱም ጋር ጽኑዕ ኃያል ጕልማሳ ሳዶቅ ነበረ፥ ከአባቱም ቤት ሃያ ሁለት አለቆች ነበሩ።
29 ፤ የሳኦልም ወንድሞች ከሆኑ ከብንያም ወንድሞች የሚበልጠው ክፍል እስከዚያ ዘመን ድረስ የሳኦልን ቤት ይከተል ነበርና ከእነርሱ ዘንድ የመጡ ሦስት ሺህ ነበሩ።
30 ፤ ጽኑዓን ኃያላን የሆኑ በአባቶቻቸውም ቤት የታወቁ የኤፍሬም ልጆች ሀያ ሺህ ስምንት መቶ ነበሩ።
31 ፤ በየስማቸውም የተጻፉ ዳዊትን ያነግሡት ዘንድ የመጡ የምናሴ ነገድ እኵሌታ አሥራ ስምንት ሺህ ነበሩ።
32 ፤ እስራኤልም የሚገባውን ያደርግ ዘንድ ዘመኑን የሚያውቁ ጥበበኞች ሰዎች የይሳኮር ልጆች አለቆች ሁለት መቶ ነበሩ፤ ወንድሞቻቸውም ሁሉ ይታዘዙአቸው ነበር።
33 ፤ በጭፍራውም ውስጥ የወጡ ለሰልፍም የተዘጋጁ፥ የማያመነቱ፥ መሣሪያም ሁሉ የያዙ የዛብሎን ሰዎች አምሳ ሺህ ነበሩ።
34 ፤ የንፍታሌምም አለቆች አንድ ሺህ ነበሩ፥ ከእነርሱም ጋር ጋሻና ጦር የሚይዙ ሠላሳ ሰባት ሺህ ነበሩ።
35 ፤ ለሰልፍም የተዘጋጁ የዳን ሰዎች ሃያ ስምንት ሺህ ስድስት መቶ ነበሩ።
36 ፤ በጭፍራውም ውስጥ የሚወጡ፥ ለሰልፍም የተዘጋጁ የአሴር ሰዎች አርባ ሺህ ነበሩ።
37 ፤ በዮርዳኖስም ማዶ ካሉ ከሮቤልና ከጋድ ሰዎች ከምናሴም ነገድ እኵሌታ መሣሪያን ሁሉ ይዘው የመጡ መቶ ሀያ ሺህ ነበሩ።
38 ፤ እነዚህ ሁሉ ዳዊትን በእስራኤል ሁሉ ላይ ያነግሡት ዘንድ አርበኞችና ሰልፈኞች እየሆኑ በፍጹም ልባቸው ወደ ኬብሮን መጡ፤ ደግሞም ከእስራኤል የቀሩት ሁሉ ዳዊትን ያነግሡት ዘንድ አንድ ልብ ነበሩ።
39 ፤ ወንድሞቻቸውም አዘጋጅተውላቸው ነበርና እየበሉና እየጠጡ በዚያ ከዳዊት ጋር ሦስት ቀን ተቀመጡ።
40 ፤ ደግሞም በእስራኤል ዘንድ ደስታ ሆኖአልና እስከ ይሳኮርና እስከ ዛብሎን እስከ ንፍታሌምም ድረስ ለእርሱ አቅራቢያ የነበሩ በአህያና በግመል በበቅሎና በበሬ ላይ እንጀራና ዱቄት የበለስ ጥፍጥፍና የዘቢበ ዘለላ የወይንም ጠጅ ዘይትም በሬዎችንና በጎችንም በብዙ አድርገው ያመጡ ነበር።