መጽሐፈ ዜና መዋዕል ቀዳማዊ።

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25 26 27 28 29


ምዕራፍ 20

እንዲህም ሆነ፤ በዓመት መለወጫ ነገሥታት ወደ ሰልፍ በሚወጡበት ጊዜ ኢዮአብ ሠራዊቱን አወጣ፥ የአሞንንም ልጆች አገር አጠፋ፤ መጥቶም ረባትን ከበበ። ዳዊትም በኢየሩሳሌም ቈይቶ ነበር።
2 ፤ ኢዮአብም ረባትን መትቶ አፈረሳት። ዳዊትም የንጉሣቸውን ዘውድ ከራሱ ላይ ወሰደ፥ ክብደቱም አንድ መክሊት ወርቅ ያህል ነበረ፥ ክቡርም ዕንቍ ነበረበት፥ በዳዊትም ራስ ላይ አስቀመጡት፤ ከከተማይቱም እጅግ ብዙ ምርኮ አወጣ።
3 ፤ በውስጥዋም የነበረውን ሕዝብ አውጥቶ በመጋዝና በብረት መቈፈሪያ በመጥረቢያም እንዲሠሩ አደረጋቸው። እንዲሁም ዳዊት በአሞን ልጆች ከተሞች ሁሉ አደረገ። ዳዊትም ሕዝቡም ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።
4 ፤ ከዚህም በኋላ በጌዝር ላይ ከፍልስጥኤማውያን ጋር ሰልፍ ሆነ፤ ኩሳታዊውም ሴቦካይ ከራፋይም ወገን የነበረውን ሲፋይን ገደለ።
5 ፤ ደግሞም ከፍልስጥኤማውያን ጋር ሰልፍ ነበረ፤ የያዒርም ልጅ ኤልያናን የጦሩ የቦ እንደ ሸማኔ መጠቅለያ የነበረውን የጌት ሰው የጎልያድን ወንድም ለሕሚን ገደለ።
6 ፤ ደግሞ በጌት ላይ ሰልፍ ነበረ፤ ከዚያም በእጁና በእግሩ ስድስት ስድስት ሁላሁሉ ሀያ አራት ጣቶች ያሉት አንድ ረጅም ሰው ነበረ፤ እርሱም ደግሞ ከራፋይም የተወለደ ነበረ።
7 ፤ እስራኤልንም በተገዳደረ ጊዜ የዳዊት ወንድም የሳምዓ ልጅ ዮናታን ገደለው።
8 ፤ እነዚያም በጌት ውስጥ ከራፋይም የተወለዱ ነበሩ፤ በዳዊትም እጅ በባሪያዎቹም እጅ ወደቁ።