ምዕራፍ 9

እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። ወደ ፈርዖን ዘንድ ገብተህ ንገረው። የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ያገለግሉኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ።
2 ፤ ልትለቅቃቸውም እንቢ ብትል ብትይዛቸውም፥
3 ፤ እነሆ የእግዚአብሔር እጅ በሜዳ ውስጥ ባሉት በከብቶችህ፥ በፈረሶችም በአህዮችም በግመሎችም በበሬዎችም በበጎችም ላይ ትሆናለች፤ ብርቱ ቸነፈርም ይወርዳል።
4 ፤ እግዚአብሔርም በእስራኤልና በግብፅ ከብቶች መካከል ይለያል፤ ከእስራኤልም ልጆች ከብት አንዳች አይጠፋም።
5 ፤ እግዚአብሔርም። ነገ እግዚአብሔር ይህን ነገር በምድር ላይ ያደርጋል ብሎ ጊዜን ወሰነ።
6 ፤ እግዚአብሔርም ያንን ነገር በነጋው አደረገ፥ የግብፅም ከብት ሁሉ ሞተ፤ ከእስራኤል ልጆች ከብት ግን አንድ ስንኳ አልሞተም።
7 ፤ ፈርዖንም ላከ፥ እነሆም ከእስራኤል ልጆች ከብት አንድ ስንኳ አልሞተም። የፈርዖን ልብ ግን ደነደነ፥ ሕዝቡንም አልለቀቀም።
8 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን። እጃችሁን ሞልታችሁ ከምድጃ አመድ ውሰዱ፥ ሙሴም በፈርዖን ፊት ወደ ሰማይ ይበትነው።
9 ፤ እርሱም በግብፅ አገር ሁሉ ትቢያ ይሆናል፥ በግብፅም አገር ሁሉ በሰውና በእንስሳ ላይ ሻህኝ የሚያመጣ ቍስል ይሆናል አላቸው።
10 ፤ ከምድጃውም አመድ ወስደው በፈርዖን ፊት ቆሙ፤ ሙሴም ወደ ሰማይ በተነው፥ በሰውና በእንስሳም ላይ ሻህኝ የሚያወጣ ቍስል ሆነ።
11 ፤ ጠንቋዮችም ቍስል ስለ ነበረባቸው በሙሴ ፊት መቆም አልቻሉም፤ ቍስል በጠንቋዮችና በግብፃያን ሁሉ ላይ ነበረና።
12 ፤ እግዚአብሔርም የፈርዖንን ልብ አጸና፤ እግዚአብሔር ለሙሴ እንደተናገረው አልሰማቸውም።
13 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። ማልደህ ተነሣ፥ በፈርኦንም ፊት ቆመህ በለው። የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እንዲያገለግሉኝ ሕዝቤን ልቀቅ።
14 ፤ በምድር ሁሉ እንደ እኔ ያለ እንደሌለ ታውቅ ዘንድ በሰውነትህ በባሪያዎችህም በሕዝብህም ላይ መቅሠፍቴን ሁሉ አሁን እልካለሁ።
15 ፤ አሁን እጄን ዘርግቼ አንተን ሕዝብህንም በቸነፈር በመታሁህ ነበር፥ አንተም ከምድር በጠፋህ ነበር፤
16 ፤ ነገር ግን ኃይሌን እገልጥብህ ዘንድ ስሜም በምድር ሁሉ ላይ ይነገር ዘንድ ስለዚህ አስነሥቼሃለሁ።
17 ፤ እንዳትለቅቃቸው ገና በሕዝቤ ላይ ትታበያለህን?
18 ፤ እነሆ ነገ በዚህ ጊዜ፥ ከተመሰረተች ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ እንደ እርሱ ያለ በግብፅ ሆኖ የማያውቅ፥ እጅግ ታላቅ በረዶ አዘንብብሃለሁ።
19 ፤ በሜዳ የተገኘ ወደ ቤት ያልገባ ሰውና እንስሳ ሁሉ በረዶ ወርዶበት ይሞታልና አሁን እንግዲህ ላክ፥ ከብቶችህንም በሜዳም ያለህን ሁሉ አስቸኵል።
20 ፤ ከፈርዖንም ባሪያዎች የእግዚአብሔርን ቃል የፈራ ባሪያዎቹንና ከብቶቹን ወደ ቤቶቹ አሸሸ፤
21 ፤ የእግዚአብሔርንም ቃል ያላሰበ ባሪያዎቹንና ከብቶቹን በሜዳ ተወ።
22 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን። በግብፅ አገር በሰው በእንስሳም በእርሻም ቡቃያ ሁሉ ላይ፥ በግብፅ አገር ሁሉ በረዶ ይሆን ዘንድ እጅህን ወደ ሰማይ ዘርጋ አለው።
23 ፤ ሙሴም በትሩን ወደ ሰማይ ዘረጋ፤ እግዚአብሔርም ነጎድጓድና በረዶ ላከ፥ እሳትም ወደ ምድር ወረደ፤ እግዚአብሔርም በግብፅ አገር ላይ በረዶ አዘነበ።
24 ፤ በረዶም ነበረ፥ በበረዶውም መካከል እሳት ይቃጠል ነበር፥ በረዶውም በግብፅ አገር ሁሉ ሕዝብ ከሆነ ጀምሮ እንደ እርሱ ያልሆነ እጅግ ታላቅ ነበረ።
25 ፤ በረዶውም በግብፅ አገር ሁሉ በሜዳ ያለውን ሁሉ ሰውንና እንስሳን መታ፤ በረዶውም የእርሻን ቡቃያ ሁሉ መታ፥ የአገሩንም ዛፍ ሁሉ ሰበረ።
26 ፤ የእስራኤል ልጆች ተቀምጠው በነበሩባት በጌሤም አገር ብቻ በረዶ አልወረደም።
27 ፤ ፈርዖንም ልኮ ሙሴንና አሮንን ጠራ። በዚህ ጊዜ በደልሁ፤ እግዚአብሔር ጻድቅ ነው፥ እኔና ሕዝቤም ኃጢያተኞች ነን።
28 ፤ የአምላክ ነጎድጓድ በረዶውም በዝቶአልና ወደ እግዚአብሔር ጸልዩ፤ እለቅቃችሁማለሁ፥ ከዚያም በኋላ በዚህ አትቀመጡም አላቸው።
29 ፤ ሙሴም። ከከተማ በወጣሁ ጊዜ እጄን ወደ እግዚአብሔር እዘረጋለሁ፤ ምድሪቱ ለእግዚአብሔር እንደሆነች ታውቅ ዘንድ ነጎድጓዱ ይቀራል፥ በረዶውም ደግሞ አይወርድም።
30 ፤ ነገር ግን አንተና ባሪያዎችህ አምላክን እግዚአብሔርን ገና እንደማትፈሩ አውቃለሁ አለው።
31 ፤ ገብሱ እሸቶ ተልባውም ኣፍርቶ ነበርና ተልባና ገብሱ ተመታ።
32 ፤ ስንዴውና አጃው ግን ጊዜው ገና ነበርና አልተመታም።
33 ፤ ሙሴም ከፈርዖን ዘንድ ከከተማ ወጣ፥ እጁንም ወደ እግዚአብሔር ዘረጋ፤ ነጎድጓዱም በረዶውም ተቋረጠ፥ ዝናቡም በምድር ላይ አልፈሰሰም።
34 ፤ ፈርዖንም ዝናቡ በረዶውም ነጎድጓዱም እንደ ተቋረጠ ባየ ጊዜ ኃጢያትን ጨመረ፥ እርሱና ባሪያዎቹም ልባቸውን አደነደኑ።
35 ፤ የፈርዖንም ልብ ጸና፤ እግዚአብሔርም በሙሴ አፍ እንደተናገር የእስራኤልን ልጆች አልለቀቀም።