ኦሪት ዘጸአት
ምዕራፍ 28
አንተም ወንድምህን አሮንን ከእርሱም ጋር ልጆቹን ከእስራኤል ልጆች መካከል ለይተህ ካህናት ይሆኑልኝ ዘንድ ወደ አንተ አቅርብ፤ አሮንን የአሮንንም ልጆች፥ ናዳብን አብዮድንም አልዓዛርንም ኢታምርንም፥ አቅርብ።
2 ፤ የተቀደሰውንም ልብስ ለክብርና ለጌጥ እንዲሆን ለወንድምህ ለአሮን ሥራለት።
3 ፤ አንተም ካህን ሆኖ እንዲያገለግለኝ አሮን ቅዱስ ይሆን ዘንድ ልብስ እንዲሠሩለት የጥበብ መንፈስ ለሞላሁባቸው በልባቸው ጥበበኞች ለሆኑት ሁሉ ተናገር።
4 ፤ የሚሠሩአቸውም ልብሶች እነዚህ ናቸው፤ የደረት ኪስ ኤፉድም ቀሚስም ዝንጕርጕር ሸሚዝም መጠምጠሚያም መታጠቂያም፤ እነዚህም ካህናት ይሆኑልኝ ዘንድ ለወንድምህ ለአሮን ለልጆቹም የተቀደሰ ልብስ ያድርጉ።
5 ፤ ወርቅንም፥ ሰማያዊና ሐምራዊ ቀይም ግምጃ፥ ጥሩ በፍታም ይውሰዱ።
6 ፤ ኤፉዱንም በብልሃት የተሠራ በወርቅና በሰማያዊ በሐምራዊም በቀይም ግምጃ ከተፈተለ ከጥሩ በፍታም ብልህ ሠራተኛ እንደሚሠራ ያድርጉ።
7 ፤ ሁለቱ ወገን አንድ እንዲሆን በሁለቱ ጫንቃ ላይ የሚጋጠም ጨርቅ ይሁን።
8 ፤ በላዩም መታጠቂያ ሆኖ በብልሃት የተጠለፈው የኤፉድ ቋድ እንደ እርሱ ከእርሱም ጋር አንድ ይሁን፤ ከወርቅና ከሰማያዊ ከሐምራዊ ከቀይ ግምጃም ከተፈተለ ከጥሩ በፍታም የተሠራ ይሁን።
9 ፤ ሁለትም የመረግድ ድንጋይ ወስደህ የእስራኤልን ልጆች ስም ስማቸውን ቅረጽባቸው፤
10 ፤ እንደ አወላለዳቸው ስድስት ስም በአንድ ድንጋይ፥ የቀረውንም ስድስቱን ስም በሌላው ቅረጽ።
11 ፤ በቅርጽ ሠራተኛ ሥራ እንደ ማኅተም ቅርጽ አድርገህ የእስራኤልን ልጆች ስም በሁለት ድንጋዮች ቅረጽ በወርቅም ፈርጥ አድርግ።
12 ፤ የእስራኤል ልጆችም የመታሰቢያ ድንጋዮች ይሆኑ ዘንድ ሁለቱን ዕንቍዎች በኤፉዱ ጫንቃዎች ላይ ታደርጋለህ፤ አሮንም በሁለቱ ጫንቃዎች ላይ ለመታሰቢያ ስማቸውን በእግዚአብሔር ፊት ይሸከማል።
13 ፤
14 ፤ የወርቅም ፈርጦች ሁለትም ድሪዎች ከጥሩ ወርቅ ሥራ፤ እንደ ተጐነጐነም ገመድ አድርግ፤ የተጐነጐኑትንም ድሪዎች በፈርጦቹ ላይ አንጠልጥል።
15 ፤ ብልህ ሠራተኛም እንደሚሠራ የፍርዱን የደረት ኪስ ሥራው እንደ ኤፉዱም አሠራር ሥራው፤ ከወርቅና ከሰማያዊ ከሐምራዊም ከቀይም ግምጃ ከጥሩ በፍታም ሥራው።
16 ፤ ርዝመቱ ስንዝር ስፋቱም ስንዝር ሆኖ ትክክልና ድርብ ይሆናል።
17 ፤ በአራት ተራ የሆነ የዕንቍ ፈርጥ አድርግበት፤ በፊተኛው ተራ ሰርድዮን፥ ቶጳዝዮን፥ የሚያብረቀርቅ ዕንቍ፤
18 ፤ በሁለተኛውም ተራ በሉር፥ ሰንፔር፥ አልማዝ፤
19 ፤ በሦስተኛውም ተራ ያክንት፥ ኬልቄዶን፥ አሜቴስጢኖስ፤
20 ፤ በአራተኛውም ተራ ቢረሌ፥ መረግድ፥ ኢያስጲድ በወርቅ ፈርጥ ይደረጋሉ።
21 ፤ የዕንቈቹም ድንጋዮች እንደ እስራኤል ልጆች ስሞች አሥራ ሁለት ይሆናሉ፤ በየስማቸውም ማተሚያ እንደሚቀረጽ ይቀረጹ፤ ስለ አሥራ ሁለቱ ነገዶችም ይሁኑ።
22 ፤ ለደረቱ ኪስም የተጐነጐኑትን ድሪዎች እንደ ገመድ አድርገህ ከጥሩ ወርቅ ሥራቸው።
23 ፤ ለደረቱ ኪስም ሁለት የወርቅ ቀለበቶች ሥራ፥ ሁለቱንም ቀለበቶች በደረቱ ኪስ በሁለቱ ወገን አድርጋቸው።
24 ፤ የተጐነጐኑትንም ሁለቱን የወርቅ ድሪዎች በደረቱ ኪስ ወገኖች ወዳሉት ወደ ሁለቱ ቀለበቶች ታገባቸዋለህ።
25 ፤ የሁለቱንም ድሪዎች ጫፎች በሁለቱ ፈርጦች ውስጥ አግብተህ በኤፉዱ ጫንቃዎች ላይ በፊታቸው ታደርጋቸዋለህ።
26 ፤ ሁለት የወርቅ ቀለበቶችም ሥራ፥ እነርሱንም በኤፉዱ ፊት ለፊት ባለው በደረቱ ኪስ በሁለቱ ጫፎች ላይ ታደርጋቸዋለህ።
27 ፤ ደግሞም ሁለት የወርቅ ቀለበቶች ሥራ፥ በኤፉዱም ፊት ከጫንቃዎች በታች በብልሃት ከተጠለፈ ከኤፉዱ ቋድ በላይ በመያዣው አጠገብ ታደርጋቸዋለህ።
28 ፤ የደረቱም ኪስ በብልሃት ከተጠለፈ ከኤፉዱ ቋድ በላይ እንዲሆን ከኤፉዱም እንዳይለይ፥ የደረቱን ኪስ ከቀለበቶቹ ወደ ኤፉዱ ቀለበቶች በሰማያዊ ፈትል ያስሩታል።
29 ፤ አሮንም ወደ መቅደስ በገባ ጊዜ በእግዚአብሔር ፊት ለዘላለም መታሰቢያ የእስራኤልን ልጆች ስሞች በፍርዱ በደረት ኪስ ውስጥ በልቡ ላይ ይሸከም።
30 ፤ በፍርዱ በደረት ኪስም ውስጥ ኡሪምንና ቱሚምን ታደርጋለህ፤ በእግዚአብሔርም ፊት በገባ ጊዜ በአሮን ልብ ላይ ይሆናሉ፤ አሮንም በእግዚአብሔር ፊት ሁልጊዜ የእስራኤልን ልጆች ፍርድ በልቡ ላይ ይሸከማል።
31 ፤ የኤፉዱንም ቀሚስ ሁሉ ሰማያዊ አድርገው።
32 ፤ ከላይም በመካከል አንገትጌ ይሁንበት፤ እንዳይቀደድም እንደ ጥሩር የተሠራ ጥልፍ በአንገትጌው ዙሪያ ይሁንበት።
33 ፤ በታችኛውም ዘርፍ ዙሪያ ከሰማያዊ ከሐምራዊም ከቀይም ግምጃ ሮማኖች አድርግ፤ በዚያም መካከል በዙሪያው የወርቅ ሻኵራዎች አድርግ፤
34 ፤ የወርቅ ሻኵራ ሮማንም፥ ሌላም የወርቅ ሻኵራ ሮማንም በቀሚሱ ዘርፍ ዙሪያውን ይሆናሉ።
35 ፤ በማገልገል ጊዜም በአሮን ላይ ይሆናል፤ እርሱም እንዳይሞት ወደ መቅደሱ በእግዚአብሔር ፊት ሲገባና ሲወጣ ድምፁ ይሰማል።
36 ፤ ከጥሩ ወርቅም ቅጠል የሚመስል ምልክት ሥራ፥ በእርሱም እንደ ማኅተም ቅርጽ አድርገህ። ቅድስና ለእግዚአብሔር የሚል ትቀርጽበታለህ።
37 ፤ በሰማያዊም ፈትል በመጠምጠሚያው ፊት ላይ ታንጠለጥለዋለህ።
38 ፤ በአሮንም ግምባር ላይ ይሆናል፥ አሮንም የእስራኤል ልጆች በሚያቀርቡትና በሚቀድሱት በቅዱስ ስጦታቸው ሁሉ ላይ ያለውን ኃጢአት ይሸከም፤ በእግዚአብሔርም ፊት ሞገስ እንዲሆንላቸው ቅጠል የሚመስለው ምልክቱ ሁልጊዜ በግምባሩ ላይ ይሁን።
39 ፤ ሸሚዙንም ከጥሩ በፍታ ዝንጕርጕር አድርገህ፥ መጠምጠሚያውን ከበፍታ ትሠራለህ፤ በጥልፍ አሠራር መታጠቂያም ትሠራለህ።
40 ፤ ለአሮንም ልጆች ሸሚዞችን መታጠቂያዎችንም ቆቦችንም ለክብርና ለጌጥ ታደርግላቸዋለህ።
41 ፤ ይህንም ሁሉ ወንድምህን አሮንን ከእርሱም ጋር ልጆቹን ታለብሳቸዋለህ፤ በክህነት እንዲያገለግሉኝ ትቀባቸዋለህ፥ ትክናቸዋለህ፥ ትቀድሳቸውማለህ።
42 ፤ ኀፍረተ ሥጋቸውንም ይከድኑበት ዘንድ የበፍታ ሱሪ ታደርግላቸዋለህ፤ ከወገባቸውም እስከ ጭናቸው ይደርሳል፤
43 ፤ ኃጢአትም እንዳይሆንባቸው እንዳይሞቱም፥ ወደ መገናኛው ድንኳን ሲገቡ በመቅደሱም ያገለግሉ ዘንድ ወደ መሠዊያው ሲቀርቡ በአሮንና በልጆቹ ላይ ይሆናል፤ ለእርሱ ከእርሱም በኋላ ለዘሩ ለዘላለም ሥርዓት ይሆናል።