ምዕራፍ 35

ሙሴም የእስራኤልን ልጆች ማኅበር ሁሉ ሰብስቦ እንዲህ አላቸው። ታደርጉ ዘንድ እግዚአብሔር ያዘዘው ቃል ይህ ነው፤
2 ፤ ስድስት ቀን ሥራ ይደረጋል፥ ሰባተኛው ቀን ግን ለእግዚአብሔር የዕረፍት ሰንበት የተቀደሰ ቀን ይሆንላችኋል፤ የሚሠራበትም ሁሉ ይገደል።
3 ፤ በማደሪያዎቻችሁ ውስጥ በሰንበት ቀን እሳትን አታንድዱ።
4 ፤ ሙሴም ለእስራኤል ልጆች ማህበር ሁሉ አላቸው። እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ያዘዘው ነገር ይህ ነው፤
5 ፤ ከእናንተ ዘንድ ለእግዚአብሔር ቍርባንን አቅርቡ፤ የልብ ፈቃድ ያለው የእግዚአብሔርን ቍርባን ያምጣ፤ ወርቅና ብርም ናስም፤
6 ፤ ሰማያዊም ሐምራዊም ቀይ ግምጃም፥ ጥሩ በፍታም፥ የፍየል ጠጕርም፤
7 ፤ ቀይም የአውራ በግ ቁርበት፥ የአቆስጣም ቁርበት፥ የግራርም እንጨት፤
8 ፤ ለመብራትም ዘይት፥ ለቅብዓት ዘይትና ለጣፋጭ ዕጣን ቅመም፤
9 ፤ መረግድ ለኤፉዱና ለደረት ኪስ የሚደረግ ፈርጥ ያምጣ።
10 ፤ በእናንተም ዘንድ ያሉ በልባቸው ጥበበኞች ሁሉ መጥተው እግዚአብሔር ያዘዘውን ሁሉ ያድርጉ።
11 ፤ ማደሪያውን፥ ድንኳኑንም መደረቢያውንም፥ መያዣዎቹንም፥ ሳንቆቹንም፥ መወርወሪያዎቹንም፥ ምሰሶቹንም፥ እግሮቹንም፤
12 ፤ ታቦቱን መሎጊያዎቹንም፥ የስርየት መክደኛውንም በእርሱም ፊት የሚሸፍነውን መጋረጃ፤
13 ፤ ገበታውን መሎጊያዎቹንም ዕቃውንም ሁሉ፥ የገጹንም ኅብስት፤
14 ፤ መብራት የሚያበሩበትን መቅረዙን ዕቃውንም፥ ቀንዲሉንም፥ የመብራቱንም ዘይት፤
15 ፤ የዕጣኑን መሠዊያም መሎጊያዎቹንም፥ የቅብዓቱንም ዘይት፥ ጣፋጩንም ዕጣን፥ ለማደሪያውም ደጃፍ የሚሆን የደጃፉን መጋረጃ፤
16 ፤ ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነውን መሠዊያውን፥ የናሱንም መከታ፥ መሎጊያዎቹንም፥ ዕቃውንም ሁሉ፤ የመታጠቢያውን ሰንም መቀመጫውንም፤
17 ፤ የአደባባዩን መጋረጆች ምሰሶቹንም እግሮቻቸውንም፥ የአደባባዩንም ደጃፍ መጋረጃ፤
18 ፤ የማደሪያውን ካስማዎች፥ የአደባባዩንም ካስማዎች አውታሮቻቸውንም፤
19 ፤ በመቅደስ ውስጥ ለማገልገል በብልሃት የተሠሩትን ልብሶች፥ በክህነት ያገለግሉበት ዘንድ የተቀደሱትን የካህኑን የአሮን ልብሶች፥ የልጆቹንም ልብሶች።
20 ፤ የእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ ከሙሴ ፊት ወጡ።
21 ፤ ከእነርሱም ሰው ሁሉ ልቡ እንዳነሣሣው መንፈሱም እሺ እንዳሰኘው ለመገናኛው ድንኳን ሥራ ለማገልገያውም ሁሉ ለተቀደሰውም ልብስ ለእግዚአብሔር ስጦታ አመጡ።
22 ፤ ወንዶችና ሴቶችም ልባቸው እንደ ፈቀደ ማርዳዎችን፥ ሎቲዎችንም፥ ቀለበቶችንም፥ ድሪዎችንም፥ የወርቅ ጌጦችንም ሁሉ አመጡ፤ ሰዎችም ሁሉ የወርቅ ስጦታ ወደ እግዚአብሔር አቀረቡ።
23 ፤ ሰማያዊም ሐምራዊም ቀይ ግምጃም፥ ጥሩ በፍታም፥ የፍየል ጠጕርም፥ ቀይ የአውራ በግ ቁርበትም፥ የአቆስጣ ቁርበትም ያላቸው ሰዎች ሁሉ አመጡ።
24 ፤ ስእለት የተሳለ ሁሉ የብርንም የናስንም ስጦታ ለእግዚአብሔር ቍርባን አቀረበ፤ የግራርም እንጨት ያለው ሁሉ ለማገልገያ ሥራ አመጣ።
25 ፤ በልባቸው ጥበበኞች የሆኑ ሴቶችም በእጃቸው ፈተሉ፥ የፈተሉትንም ሰማያዊውን ሐምራዊውንም ቀዩንም ግምጃ፥ ጥሩውንም በፍታ አመጡ።
26 ፤ ልባቸውም በጥበብ ያስነሣቸው ሴቶች ሁሉ የፍየልን ጠጕር ፈተሉ።
27 ፤ አለቆችም መረግድን፥ ለኤፉድና ለደረት ኪስ የሚገቡትንም ፈርጦችን፥
28 ፤ ለመብራትም ለቅብዓት ዘይትም ለጣፋጭ ዕጣንም ሽቱንና ዘይትን አመጡ።
29 ፤ ከእስራኤል ልጆችም ያመጡ ዘንድ ልባቸው ያስነሣቸው ወንዶችና ሴቶች ሁሉ ሙሴ ይሠራ ዘንድ እግዚአብሔር ላዘዘው ሥራ ሁሉ ለእግዚአብሔር ስጦታ በፈቃዳቸው አመጡ።
30 ፤ ሙሴም የእስራኤልን ልጆች አላቸው። እዩ፥ እግዚአብሔር ከይሁዳ ነገድ የሆነውን የሆር የልጅ ልጅ፥ የኡሪ ልጅ ባስልኤልን በስሙ ጠራው።
31 ፤ በሥራ ሁሉ ብልሃት በጥበብም በማስተዋልም በእውቀትም የእግዚአብሔርን መንፈስ ሞላበት፤
32 ፤ የጥበብን ሥራ ያስተውል ዘንድ፥ በወርቅና በብር በናስም ይሠራ ዘንድ፥
33 ፤ በፈርጥ የሚሆነውን የዕንቍ ድንጋይ ይቀርጽ ዘንድ፥ እንጨቱንም ይጠርብ ዘንድ፥ የብልሃት ሥራውንም ሁሉ ይሠራ ዘንድ።
34 ፤ እርሱና የዳን ነገድ የሆነው የአሂሳሚክ ልጅ ኤልያብ ያስተምሩ ዘንድ በልባቸው አሳደረባቸው።
35 ፤ በአንጥረኛ፥ በብልህ ሠራተኛም፥ በሰማያዊና በሐምራዊ በቀይም ግምጃ በጥሩ በፍታም በሚሠራ ጠላፊ፥ በሸማኔም ሥራ የሚሠራውን፥ ማናቸውንም ሥራና በብልሃት የሚሠራውን ሁሉ ያደርጉ ዘንድ በእነርሱ ልብ ጥበብን ሞላ።