ምዕራፍ 11

እግዚአብሔርም ሙሴን። በፈርዖንና በግብፅ ላይ ገና አንዲት መቅሰፍት አመጣለሁ፥ ከዚያ ወዲያም ይለቅቃችኋል፤ ሲለቅቃችሁም አባርሮ ይሰድዳችኋል።
2 ፤ ወንዱ ከወዳጁ ሴቲቱም ከወዳጅዋ የብርና የወርቅ ዕቃ ይሹ ዘንድ በሕዝቡ ጆሮ ተናገር አለው።
3 ፤ እግዚአብሔርም በግብፃውያን ፊት ለሕዝቡ ሞገስን ሰጠው። ሙሴም በፈርዖን ባሪያዎችና በሕዝቡ ፊት በግብፅ አገር እጅግ የከበረ ሰው ነበረ።
4 ፤ ሙሴም አለ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በእኩል ሌሊት እኔ በግብፅ መካከል እወጣለሁ፤
5 ፤ በግብፅም አገር ያለ በኵር ሁሉ፥ በዙፋኑ ከሚቀመጠው ከፈርዖን በኵር ጀምሮ በወፍጮ እግር እስካለችው እስከ ባሪያይቱ በኵር ድረስ፥ የከብቱም በኵር ሁሉ ይሞታል።
6 ፤ በግብፅም አገር ሁሉ አስቀድሞ እንደ እርሱ ያልሆነ ኋላም ደግሞ የማይሆን ታላቅ ጩኸት ይሆናል።
7 ፤ እግዚአብሔር ግን በግብፃውያንና በእስራኤል መካከል እንዲለይ እንድታውቁ በእስራኤል ልጆች መካከል ከሰው ጀምሮ እስከ እንስሳ ድረስ ውሻ ምላሱን አያንቀሳቅስባቸውም።
8 ፤ እነዚህም ባሪያዎችህ ሁሉ። አንተ ውጣ የሚከተሉህም ሕዝብ ሁሉ ይውጡ እያሉ ወደ እኔ ይወርዳሉ፥ ለእኔም ይሰግዳሉ፤ ከዚያም በኋላ እወጣለሁ። ሙሴም በጽኑ ቁጣ ከፈርዖን ዘንድ ወጣ።
9 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን። ተአምራቴ በግብፅ አገር ብዙ እንዲሆን ፈርዖን አይሰማችሁም አለው።
10 ፤ ሙሴና አሮንም እነዚህን ተአምራቶች ሁሉ በፈርዖን ፊት አደረጉ፤ እግዚአብሔር የፈርዖንን ልብ አጸና፥ የእስራኤልንም ልጆች ከአገሩ አልለቀቀም።