ምዕራፍ 5

ከዚህም በኋላ ሙሴና አሮን መጥተው ፈርዖንን እንዲህ አሉት። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በምድረ በዳ በዓል ያደርግልኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ።
2 ፤ ፈርዖንም። ቃሉን እሰማ ዘንድ እስራኤልንስ እለቅቅ ዘንድ እግዚአብሔር ማን ነው? እግዚአብሔርን አላውቅም፥ እስራኤልንም ደግሞ አልለቅቅም አለ።
3 ፤ እነርሱም። የዕብራውያን አምላክ ተገናኘን፤ ቸነፈር ወይም ሰይፍ እንዳይጥልብን የሦስት ቀን መንገድ በምድረ በዳ እንድንሄድ፥ ለአምላካችን ለእግዚአብሔር እንድንሠዋ እንለምንሃለን አሉት።
4 ፤ የግብፅ ንጉሥም። አንተ ሙሴ አንተም አሮን፥ ሕዝቡን ለምን ሥራቸውን ታስተዋላችሁ? ወደ ተግባራችሁ ሂዱ አላቸው።
5 ፤ ፈርዖንም። እነሆ የምድሩ ሕዝብ አሁን በዝቶአል፥ እናንተም ሥራቸውን ታስፈቱአቸዋላችሁ አለ።
6 ፤ ፈርዖንም በዚያን ቀን የሕዝቡን አስገባሪዎች ሹማምቶቹንም እንዲህ ሲል አዘዘ።
7 ፤ እንደ ወትሮው ለጡብ ሥራ ደግሞ ገለባ ለሕዝቡ አትስጡ፤ ነገር ግን እነርሱ ሄደው ገለባ ይሰብስቡ።
8 ፤ ቀድሞ ያደርጉት የነበረውን የጡብ ቍጥር በእነርሱ ላይ አድርጉት፤ ምንም ከእርሱ አታጕድሉ፤ ሥራ ሰልችተዋልና ስለዚህ። ለአምላካችን እንድንሰዋ እንሂድ እያሉ ይጮኻሉ።
9 ፤ እርሱንም ያደርጉ ዘንድ በሰዎች ላይ ሥራው ይክበድባቸው፤ ከንቱ ቃልም አያስቡ።
10 ፤ የሕዝቡም አስገባሪዎች ሹማምቶቹም ወጡ፥ ሕዝቡንም። ፈርዖን እንዲህ ይላል። ገለባ አልሰጣችሁም።
11 ፤ እናንተ ሂዱ፥ ከምታገኙበትም ስፍራ ገለባ ሰብስቡ፤ ከሥራችሁ ግን ምንም አይጐድልም አሉአቸው።
12 ፤ ሕዝቡም ስለ ገለባ እብቅ ሊሰበስቡ በግብፅ ምድር ሁሉ ተበተኑ።
13 ፤ አስገባሪዎቹም። ገለባ ትቀበሉበት እንደ ነበረ ጊዜ የቀን ሥራችሁን ጨርሱ እያሉ አስቸኰሉአቸው።
14 ፤ የፈርዖንም አስገባሪዎች። ቀድሞ ታደርጉ እንደ ነበራችሁ ትናንትናና ዛሬ የተቈጠረውን ጡብ ስለ ምን አትጨርሱም? እያሉ በእስራኤል ልጆች ላይ የተሾሙትን አለቆቹን ገረፉ።
15 ፤ የእስራኤል ልጆች አለቆችም ወደ ፈርዖን መጡ። ለምን በባሪያዎችህ እንዲህ ታደርጋለህ?
16 ፤ ገለባ አይሰጡንም፥ የጡቡንም ሥራ እንድንሠራ ያዝዙናል፤ እነሆም ባሪያዎችህን ይገርፉናል፤ ግድፈቱ ግን በአንተ ሕዝብ ላይ ነው ብለው ጮኹ።
17 ፤ እርሱ ግን። ሰልችታችኋል፥ ሰልችታችኋል፤ ስለዚህም። እንሂድ ለእግዚአብሔርም እንሠዋ ትላላችሁ።
18 ፤ አሁንም ሂዱ፥ ሥሩ፤ ገለባ አይሰጡአችሁም፥ የጡቡን ቍጥር ግን ታመጣላችሁ አላቸው።
19 ፤ የእስራኤልም ልጆች አለቆች። ዕለት ዕለት ከምትሰሩት ከጡቡ ቍጥር ምንም አታጕድሉ ባሉአቸው ጊዜ ነገሩ እንደ ከፋባቸው አዩ።
20 ፤ ከፈርዖንም ዘንድ ሲወጡ ሙሴንና አሮንን በፊታቸው ቆመው ተገናኙአቸው።
21 ፤ እነርሱም። በፈርዖንና በባሪያዎቹ ፊት ሽታችንን አግምታችሁታልና፥ ይገድሉንም ዘንድ ሰይፍን በእጃቸው ሰጥታችኋቸዋልና እግዚአብሔር ይመልከታችሁ ይፍረድባችሁም አሉአቸው።
22 ፤ ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ተመለሰና። ጌታ ሆይ፥ ስለ ምን ይህን ሕዝብ አስከፋህ? ስለ ምንስ ላክኸኝ?
23 ፤ በስምህ እናገር ዘንድ ወደ ፈርዖን ከገባሁ ወዲህ፥ ይህን ሕዝብ አስከፍቶታልና፤ አንተም ሕዝብህን ከቶ አላዳንኸውም አለ።