ምዕራፍ 19

በሦስተኛውም ወር የእስራኤል ልጆች ከግብፅ ምድር ከወጡ በኋላ በዚያ ቀን ወደ ሲና ምድረ በዳ መጡ።
2 ፤ ከራፊድም ተነሥተው ወደ ሲና ምድረ በዳ መጡ፥ በምድረ በዳም ሰፈሩ፤ በዚያም እስራኤል በተራራው ፊት ሰፈረ።
3 ፤ ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ወጣ፤ እግዚአብሔርም በተራራው ጠርቶ አለው። ለያዕቆብ ቤት እንዲህ በል፥ ለእስራኤልም ልጆች እንዲህ ንገር።
4 ፤ በግብፃውያን ያደረግሁትን፥ በንስርም ክንፍ እንደተሸከምኋችሁ፥ ወደ እኔም እንዳመጣኋችሁ አይታችኋል።
5 ፤ አሁንም ቃሌን በእውነት ብትሰሙ ኪዳኔንም ብትጠብቁ፥ ምድር ሁሉ የእኔ ናትና ከአሕዛብ ሁሉ የተመረጠ ርስት ትሆኑልኛላችሁ፤
6 ፤ እናንተም የካህናት መንግሥት የተቀደሰም ሕዝብ ትሆኑልኛላችሁ። ለእስራኤል ልጆች የምትነግራቸው ቃል ይህ ነው።
7 ፤ ሙሴም መጣ፥ የሕዝቡንም ሽማግሌዎች ጠርቶ እግዚአብሔር ያዘዘውን ይህን ቃል ሁሉ በፊታቸው ተናገረ።
8 ፤ ሕዝቡ ሁሉ አንድ አፍ ሆነው። እግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እናደርጋለን ብለው መለሱ፤ ሙሴም የሕዝቡን ቃል ወደ እግዚአብሔር አደረሰ።
9 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን። ከአንተ ጋር ስነጋገር ሕዝቡ እንዲሰሙ፥ ደግሞም ለዘላለም እንዲያምኑብህ፥ እነሆ በከባድ ደመና እመጣልሃለሁ አለው። ሙሴም የሕዝቡን ቃል ለእግዚአብሔር ነገረ።
10 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። ወደ ሕዝቡ ሂድ፥ ዛሬና ነገም ቀድሳቸው፥ ልብሳቸውንም ይጠቡ፤
11 ፤ በሦስተኛው ቀን ሕዝቡ ሁሉ ሲያዩ እግዚአብሔር በሲና ተራራ ላይ ይወርዳልና ለሦስተኛው ቀን ይዘጋጁ።
12 ፤ ወሰንም ለሕዝቡ በዙሪያው አድርግላቸው። ወደ ተራራው እንዳትወጡ ጫፉንም እንዳትነኩ ተጠንቀቁ፤ ተራራውንም የነካ ፈጽሞ ይሞታል፤
13 ፤ የማንም እጅ አይንካ፤ ነገር ግን የሚነካው ሁሉ ይወገራል፥ ወይም በፍላጻ ይወጋል፤ እንስሳ ወይም ሰው ቢሆን አይድንም በላቸው። ሳያቋርጥ የመለከት ድምፅ ሲነፋ በዚያን ጊዜ ወደ ተራራው ይውጡ።
14 ፤ ሙሴም ከተራራው ወደ ሕዝቡ ወረደ፥ ሕዝቡንም ቀደሰ፤ ልብሳቸውንም አጠቡ።
15 ፤ ሕዝቡንም። ለሦስተኛው ቀን ተዘጋጁ፥ ወደ ሴቶቻችሁ አትቅረቡ አለ።
16 ፤ እንዲህም ሆነ፤ በሦስተኛው ቀን በማለዳ ጊዜ ነጐድጓድና መብረቅ ከባድም ደመና እጅግም የበረታ የቀንደ መለከት ድምጽ በተራራው ላይ ሆነ፤ በሰፈሩም የነበሩት ሕዝብ ሁሉ ተንቀጠቀጡ።
17 ፤ ሙሴም ሕዝቡን ከእግዚአብሔር ጋር ለማገናኘት ከሰፈር አወጣቸው፤ ከተራራውም እግርጌ ቆሙ።
18 ፤ እግዚአብሔርም በእሳት ስለ ወረደበት የሲና ተራራ ሁሉ ይጤስ ነበር፤ ከእርሱም እንደ እቶን ጢስ ያለ ጢስ ይወጣ ነበር፥ ተራራውም ሁሉ እጅግ ይናወጥ ነበር።
19 ፤ የቀንደ መለከቱም ድምፅ እጅግ በበረታና በጸና ጊዜ ሙሴ ተናገረ እግዚአብሔርም በድምፅ መለሰለት።
20 ፤ እግዚአብሔርም በሲና ተራራ ላይ ወደ ተራራው ራስ ወረደ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን ወደ ተራራው ራስ ጠራው፤ ሙሴም ወጣ።
21 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን። ውረድ፥ እግዚአብሔርን ለማየት ዳርቻውን እንዳያልፉ ከእነርሱም ብዙ እንዳይጠፉ ለሕዝቡ አስጠንቅቃቸው፤
22 ፤ ወደ እግዚአብሔርም የሚቀርቡት ካህናት ደግሞ እግዚአብሔር እንዳያጠፋቸው ራሳቸውን ይቀድሱ አለው።
23 ፤ ሙሴም እግዚአብሔርን። አንተ። በተራራው ዙሪያ ወሰን አድርግ ቀድሰውም ብለህ አስጠንቅቀኸናልና ሕዝቡ ወደ ተራራ ይወጡ ዘንድ አይችሉም አለው።
24 ፤ እግዚአብሔርም። ሂድ፥ ውረድ፤ አንተ አሮንም ከአንተ ጋር ትወጣላችሁ፤ ካህናቱና ሕዝቡ ግን እግዚአብሔር እንዳያጠፋቸው ወደ እግዚአብሔር ይወጡ ዘንድ አይተላለፉ አለው።
25 ፤ ሙሴም ወደ ሕዝቡ ወረደ፥ ይህንንም ነገራቸው።