ምዕራፍ 4

ሙሴም መለሰ። እነሆ አያምኑኝም ቃሌንም አይሰሙም። እግዚአብሔር ከቶ አልተገለጠልህም ይሉኛል አለ።
2 ፤ እግዚአብሔርም። ይህች በእጅህ ያለችው ምንድር ናት? አለው። እርሱም። በትር ናት አለ።
3 ፤ ወደ መሬት ጣላት አለው፤ እርሱም በመሬት ጣላት፥ እባብም ሆነች፤ ሙሴም ከእርሷ ሸሸ።
4
5 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን። የአባቶቻቸው አምላክ፥ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ፥ እግዚአብሔር እንደ ተገለጠልህ እንዲያምኑ እጅህን ዘርግተህ ጅራትዋን ያዝ አለው። እጁንም ዘርግቶ ያዛት በእጁም ውስጥ በትር ሆነች።
6 ፤ እግዚአብሔርም ደግሞ። እጅህን ወደ ብብትህ አግባ አለው። እጁንም ወደ ብብቱ አገባት፤ ባወጣትም ጊዜ እነሆ፥ እጁ እንደ በረዶ ለምጽ ሆነች።
7 ፤ እርሱም። እጅህን ወደ ብብትህ መልስ አለው። እጁንም ወደ ብብቱ መለሳት፥ ከብብቱም ባወጣት ጊዜ እነሆ ተመልሳ ገላውን መሰለች።
8 ፤ ደግሞም አለው። እንዲህም ይሆናል፤ ባያምኑህ የፊተኛይቱንም ምልክት ነገር ባይሰሙ፥ የሁለተኛይቱን ምልክት ነገር ያምናሉ።
9 ፤ እንዲህም ይሆናል፤ እነዚህን ሁለት ምልክቶች ባያምኑ ቃልህንም ባይሰሙ፥ ከወንዙ ውኃን ውሰድ፥ በደረቁም መሬት ላይ አፍስሰው፤ ከወንዙም የወሰድኸው ውኃ በደረቁ መሬት ላይ ደም ይሆናል።
10 ፤ ሙሴም እግዚአብሔርን። ጌታ ሆይ፥ እኔ አፌ ኰልታፋ ምላሴም ጸያፍ የሆነ ሰው ነኝ፤ ትናንት ከትናንት ወዲያ ባሪያህንም ከተናገርኸኝ ጀምሮ አፈ ትብ ሰው አይደለሁም።
11 ፤ እግዚአብሔርም። የሰውን አፍ የፈጠረ ማን ነው? ዲዳስ ደንቆሮስ የሚያይስ ዕውርስ ያደረገ ማን ነው? እኔ እግዚአብሔር አይደለሁምን?
12 ፤ እንግዲህ አሁን ሂድ፥ እኔም ከአፍህ ጋር እሆናለሁ፥ የምትናገረውንም አስተምርሃለሁ አለው።
13 ፤ እርሱም። ጌታ ሆይ፥ በምትልከው ሰው እጅ ትልክ ዘንድ እለምንሃለሁ አለ።
14 ፤ የእግዚአብሔርም ቍጣ በሙሴ ላይ ነደደ እንዲህም አለ። ሌዋዊው ወንድምህ አሮን አለ አይደለምን? እርሱ ደህና እንዲናገር አውቃለሁ፤ እነሆም ደግሞ ሊገናኝህ ይመጣል፤ ባየህም ጊዜ በልቡ ደስ ይለዋል።
15 ፤ አንተም ትናገረዋለህ ቃሉንም በአፉ ታደርገዋለህ፤ እኔ ከአፍህና ከአፉ ጋር እሆናለሁ፥ የምታደርጉትንም አስተምራችኋለሁ።
16 ፤ እርሱ ስለ አንተ ከሕዝቡ ጋር ይናገራል፤ እንዲህም ይሆናል፤ እርሱ አፍ ይሆንልሃል አንተም በእግዚአብሔር ፋንታ ትሆንለታለህ።
17 ፤ ይህችንም ተአምራት የምታደርግባትን በትር በእጅህ ይዘሃት ሂድ።
18 ፤ ሙሴም ሄደ፥ ወደ አማቱ ወደ ዮቶር ተመለሰ። እስከ ዛሬ በሕይወት እንዳሉ አይ ዘንድ ተመልሼ ወደ ግብፅ ወደ ወንድሞቼ ልሂድ አለው። ዮቶርም ሙሴን። በሰላም ሂድ አለው።
19 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን በምድያም። ነፍስህን የሚሹአት ሰዎች ሁሉ ሞተዋልና ተመልሰህ ወደ ግብፅ ሂድ አለው።
20 ፤ ሙሴም ሚስቱንና ልጆቹን ወሰደ፥ በአህያ ላይም አስቀመጣቸው፥ ወደ ግብፅም አገር ተመለሰ፤ ሙሴም የእግዚአብሔርን በትር ይዞ ሄደ።
21 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። ወደ ግብፅ ስትመለስ በእጅህ ያደረግሁትን ተአምራት ሁሉ በፈርዖን ፊት ታደርገው ዘንድ ተመልከት፤ እኔ ግን ልቡን አጸናዋለሁ፥ ሕዝቡንም አይለቅቅም።
22 ፤ ፈርዖንንም። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል።
23 ፤ እስራኤል የበኵር ልጄ ነው፤ ይገዛልኝ ዘንድ ልጄን ልቀቅ አልሁህ፤ አንተም ትለቅቀው ዘንድ እንቢ አልህ፤ እነሆ እኔ የበኵር ልጅህን እገድላለሁ ትለዋለህ።
24 ፤ እንዲህም ሆነ፤ በመንገድ ላይ ባደረበት ስፍራ እግዚአብሔር ተገናኘው፥ ሊገድለውም ፈለገ።
25 ፤ ሲፓራም ሚስቱ ባልጩት ወሰደች፥ የልጅዋንም ሸለፈት ገረዘች፥ ወደ እግሩም ጣለችው። አንተ ለእኔ የደም ሙሽራ ነህ አለች።
26 ፤ ከእርሱም ፈቀቅ አለ። የዚያን ጊዜ። ስለ ግርዛቱ አንተ የደም ሙሽራ ነህ አለች።
27 ፤ እግዚአብሔርም አሮንን። ሄደህ በምድረ በዳ ሙሴን ተገናኘው አለው፤ ሄዶም በእግዚአብሔር ተራራ ተገናኘው፥ ሳመውም።
28 ፤ ሙሴም እግዚአብሔር በእርሱ ዘንድ የላከውን ቃል ሁሉ ያዘዘውንም ተአምራት ሁሉ ለአሮን ተናገረው።
29 ፤ ሙሴና አሮንም ሄዱ የእስራኤልንም ልጆች ሽማግሌዎች ሁሉ ሰበሰቡ።
30 ፤ አሮንም እግዚአብሔር ለሙሴ የነገረውን ቃል ሁሉ ተናገረ፥ ተአምራቱንም በሕዝቡ ፊት አደረገ።
31 ፤ ሕዝቡም አመኑ፤ እግዚአብሔርም የእስራኤልን ልጆች እንደ ጐበኘ ጭንቀታቸውንም እንዳየ በሰሙ ጊዜ፥ አጐነበሱ ሰገዱም።