ምዕራፍ 29

እኔንም በክህነት እንዲያገለግሉኝ ትቀድሳቸው ዘንድ የምታደርግባቸው ነገር ይህ ነው፤ ነውር የሌለባቸውን አንድ ወይፈንና ሁለት አውራ በጎች ትወስዳለህ።
2 ፤ ቂጣ እንጀራ፥ በዘይትም የተለወሰ የቂጣ እንጐቻ፥ በዘይትም የተቀባ ስስ ቂጣ ከመልካም ስንዴ ታደርጋለህ።
3 ፤ በአንድ ሌማትም ታደርጋቸዋለህ፤ ከወይፈኑና ከሁለቱ አውራ በጎች ጋር በሌማቱ ታቀርባቸዋለህ።
4 ፤ አሮንና ልጆቹንም ወደ መገናኛው ድንኳን ታቀርባቸዋለህ፥ በውኃም ታጥባቸዋለህ።
5 ፤ ልብሶችን ወስደህ ለአሮን ሸሚዝና የኤፉድ ቀሚስ ኤፉድም የደረት ኪስም ታለብሰዋለህ፥ በብልሃትም በተጠለፈ ቋድ ታስታጥቀዋለህ፤
6 ፤ መጠምጠሚያውንም በራሱ ላይ ታደርጋለህ፥ የተቀደሰውንም አክሊል በመጠምጠሚያው ላይ ታኖራለህ።
7 ፤ የቅብዓትንም ዘይት ወስደህ በራሱ ላይ ታፈስሰዋለህ፥ ትቀባውማለህ።
8 ፤ ልጆቹንም ታቀርባቸዋለህ፥ ሸሚዞቹንም ታለብሳቸዋለህ።
9 ፤ አሮንንና ልጆቹንም በመታጠቂያ ታስታጥቃቸዋለህ፥ ቆብንም ታለብሳቸዋለህ፤ ለዘላለም ሥርዓትም ክህነት ይሆንላቸዋል፤ እንዲሁም አሮንንና ልጆቹን ትክናቸዋለህ።
10 ፤ ወይፈኑንም ወደ መገናኛው ድንኳን በር ፊት ታቀርበዋለህ፤ አሮንና ልጆቹም እጆቻቸውን በወይፈኑ ራስ ላይ ይጭናሉ።
11 ፤ ወይፈኑንም በመገናኛው ድንኳን በር አጠገብ በእግዚአብሔር ፊት ታርደዋለህ።
12 ፤ ከወይፈኑም ደም ወስደህ በመሠዊያው ቀንዶች ላይ በጣትህ ትረጨዋለህ፤ ደሙንም ሁሉ ከመሠዊያው በታች ታፈስሰዋለህ።
13 ፤ የሆድ ዕቃውንም የሚሸፍነውን ስብ ሁሉ በጉልበቱም ላይ ያለውን መረብ ሁለቱንም ኵላሊቶች በላያቸውም ያለውን ስብ ወስደህ በመሠዊያው ላይ ታቃጥላለህ።
14 ፤ የወይፈኑን ሥጋ ግን፥ ቁርበቱንም፥ ፈርሱንም ከሰፈር ውጭ በእሳት ታቃጥለዋለህ፤ የኃጢአት መሥዋዕት ነው።
15 ፤ አንደኛውንም አውራ በግ ትወስደዋለህ፤ አሮንና ልጆቹም በአውራው በግ ራስ ላይ እጆቻቸውን ይጭናሉ።
16 ፤ አውራውንም በግ ታርደዋለህ፥ ደሙንም ወስደህ በመሠዊያው ላይ በዙሪያው ትረጨዋለህ።
17 ፤ አውራውንም በግ በየብልቱ ትቈርጠዋለህ፥ የሆድ ዕቃውንና እግሮቹንም ታጥባለህ፥ ከብልቱና ከራሱም ጋር ታኖረዋለህ።
18 ፤ አውራውንም በግ በሞላው በመሠዊያው ላይ ታቃጥላለህ፤ ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት ነው፤ ጣፋጭ ሽቱ ነው። ለእግዚአብሔር የቀረበ የእሳት ቍርባን ነው።
19 ፤ ሁለተኛውንም አውራ በግ ትወስደዋለህ፤ አሮንና ልጆቹም እጆቻቸውን በአውራው በግ ራስ ላይ ይጭናሉ።
20 ፤ አውራውንም በግ ታርደዋለህ፥ ደሙንም ትወስዳለህ፥ የአሮንንም የቀኝ ጆሮ ጫፍ፥ የልጆቹንም የቀኝ ጆሮአቸውን ጫፍ፥ የቀኝ እጃቸውንና የቀኝ እግራቸውን አውራ ጣት ታስነካለህ፤ ደሙንም በመሠዊያው ላይ በዙሪያው ትረጨዋለህ።
21 ፤ በመሠዊያውም ላይ ካለው ደም ከቅብዓት ዘይትም ወስደህ በአሮንና በልብሱ ላይ፥ ከእርሱም ጋር ባሉት በልጆቹና በልብሶቻቸው ላይ ትረጨዋለህ፤ እርሱም ልብሶቹም፥ ከእርሱም ጋር ልጆቹ ልብሶቻቸውም ይቀደሳሉ።
22 ፤ ደግሞም የሚካኑበት አውራ በግ ነውና የበጉን ስብ፥ ላቱንም፥ የሆድ ዕቃውንም የሚሸፍነውን ስብ፥ በጉበቱም ላይ ያለውን መረብ፥ ሁለቱንም ኵላሊቶች በላያቸውም ያለውን ስብ፥ የቀኙንም ወርች ትወስዳለህ።
23 ፤ አንድ እንጀራ፥ አንድም የዘይት እንጀራ፥ አንድም ስስ ቂጣ በእግዚአብሔር ፊት በሌማት ካለው ቂጣ እንጀራ ትወስዳለህ፤
24 ፤ ሁሉንም በአሮን እጆችና በልጆቹ እጆች ታኖረዋለህ፤ ለሚወዘወዝ ቍርባን በእግዚአብሔር ፊት ትወዘውዘዋለህ።
25 ፤ ከእጃቸውም ትቀበለዋለህ፥ በመሠዊያውም ላይ ከሚቃጠል መሥዋዕት ጋር በእግዚአብሔር ፊት ጣፋጭ ሽቱ እንዲሆን ታቃጥለዋለህ፤ እርሱ ለእግዚአብሔር የእሳት ቍርባን ነው።
26 ፤ ለአሮንም ክህነት የታረደውን በግ ፍርምባ ወስደህ ለሚወዘወዝ ቍርባን በእግዚአብሔር ፊት ትወዘውዘዋለህ፤ እርሱም የአንተ ወግ ይሆናል።
27 ፤ ከሚካኑበትም አውራ በግ የተወሰደ ለአሮንና ለልጆቹ ወግ የሚሆን ለመሥዋዕት የተወዘወዘውን ፍርምባና የተነሣውን ወርች ትቀድሳለህ።
28 ፤ ያውም የማንሣት ቍርባን ነውና ከእስራኤል ልጆች ዘንድ ለዘላለም የአሮንና የልጆቹ ወግ ይሁን፤ የእስራኤል ልጆች የሚያቀርቡት የደኅንነት መሥዋዕታቸው የማንሣት ቍርባን ይሆናል፤ ለእግዚአብሔር የማንሣት ቍርባን ይሆናል።
29 ፤ የተቀደሰውም የአሮን ልብስ ይቀቡበትና ይካኑበት ዘንድ ከእርሱ በኋላ ለልጆቹ ይሁን።
30 ፤ ከልጆቹም በእርሱ ፋንታ ካህን የሚሆነው በመቅደስ ለማገልገል ወደ መገናኛው ድንኳን ሲገባ ሰባት ቀን ይልበሰው።
31 ፤ የሚካንበትንም አውራ በግ ወስደህ ሥጋውን በተቀደሰ ስፍራ ትቀቅለዋለህ።
32 ፤ አሮንና ልጆቹም የአውራውን በግ ሥጋ በሌማትም ያለውን እንጀራ በመገናኛው ድንኳን በር ይበሉታል።
33 ፤ የተካኑና የተቀደሱ ይሆኑ ዘንድ ማስተስረያ የሆነውን ነገር ይብሉት፤ ሌላ ሰው ግን አይብላው፤ የተቀደሰ ነውና።
34 ፤ የተካኑበትም ሥጋ ወይም እንጀራ ተርፎ ቢያድር፥ የቀረውን በእሳት ታቃጥለዋለህ፤ የተቀደሰ ነውና አይበላም።
35 ፤ እንዳዘዝሁህም ሁሉ በአሮንና በልጆቹ እንዲህ አድርግ፤ ሰባት ቀን ትክናቸዋለህ።
36 ፤ ዕለት ዕለትም ስለ ማስተስረይ ለኃጢአት መሥዋዕት ወይፈኑን ታቀርባለህ፤ ማስተስረያም ባደረግህ ጊዜ መሠዊያውን ታነጻዋለህ፤ ቅዱስም ይሆን ዘንድ ትቀባዋለህ።
37 ፤ ሰባት ቀን ለመሠዊያው ማስተስረያ ታደርጋለህ፥ ትቀድሰውማለህ፤ መሠዊያውም ቅድስተ ቅዱሳን ይሆናል፤ መሠዊያውንም የሚነካ ሁሉ ቅዱስ ይሆናል።
38 ፤ በመሠዊያውም ላይ የምታቀርበው ይህ ነው፤ በቀን በቀን ዘወትር ሁለት የዓመት ጠቦቶች ታቀርባለህ።
39 ፤ አንዱን ጠቦት በማለዳ ቍርባን አድርገህ ታቀርበዋለህ፤ ሁለተኛውንም ጠቦት በማታ ቍርባን አድርገህ ታቀርበዋለህ።
40 ፤ ከአንዱ ጠቦትም ጋር የኢን መስፈሪያ አራተኛ እጅ በሆነ ተወቅጦ በተጠለለ ዘይት የተለወሰ የኢፍ መስፈሪያ አሥረኛ እጅ መልካም ዱቄት፥ ደግሞ ለመጠጥ ቍርባን የኢን መስፈሪያ አራተኛ እጅ የወይን ጠጅ ታቀርባለህ።
41 ፤ ሁለተኛውንም ጠቦት በማታ ታቀርበዋለህ፥ እንደ ማለዳውም የእህልና የመጠጥ ቍርባን ታደርግበታለህ፤ ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽቱ እንዲሆን የእሳት ቍርባን ይሆናል።
42 ፤ ለአንተ እናገር ዘንድ ከእናንተ ጋር በምገናኝበት በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ፥ በእግዚአብሔር ፊት ይህ ዘወትር ለልጅ ልጃችሁ የሚቃጠል መሥዋዕት ይሆናል።
43 ፤ ከእስራኤልም ልጆች ጋር በዚያ እገናኛለሁ፤ ድንኳኑም በክብሬ ይቀደሳል።
44 ፤ የመገናኛውንም ድንኳን መሠዊያውንም እቀድሳለሁ፤ በክህነትም ያገለግሉኝ ዘንድ አሮንንና ልጆቹን እቀድሳለሁ።
45 ፤ በእስራኤልም ልጆች መካከል እኖራለሁ፥ አምላክም እሆናቸዋለሁ።
46 ፤ በመካከላቸውም እኖር ዘንድ ከግብፅ ምድር ያወጣኋቸው አምላካቸው እግዚአብሔር እኔ እንደ ሆንሁ ያውቃሉ፤ እኔ አምላካቸው እግዚአብሔር ነኝ።