ምዕራፍ 30

የዕጣን መሠዊያውን ሥራ፤ ከግራር እንጨት አድርገው።
2 ፤ ርዝመቱ አንድ ክንድ፥ ስፋቱም አንድ ክንድ፥ አራት ማዕዘን ይሁን፤ ከፍታውም ሁለት ክንድ ይሆናል፤ ቀንዶቹም ከእርሱ ጋር በአንድነት የተሠሩ ይሁኑ።
3 ፤ ላይኛውንና የግድግዳውንም ዙሪያ ቀንዶቹንም በጥሩ ወርቅ ትለብጠዋለህ፤ በዙሪያውም የወርቅ ክፈፍ ታደርግለታለህ።
4 ፤ ከክፈፉም በታች ሁለት የወርቅ ቀለበቶች አድርግለት። በዚህና በዚያ በሁለቱ ጎን ታደርጋቸዋለህ፤ ለመሸከምም የመሎጊያዎች ስፍራ ይሁኑ።
5 ፤ መሎጊያዎቹንም ከግራር እንጨት አድርግ፥ በወርቅም ለብጣቸው።
6 ፤ በምስክሩ ታቦት አጠገብም ካለው መጋረጃ በፊት ታኖረዋለህ ይህንም አንተን በምገናኝበት ከምስክሩ በላይ ባለው በስርየት መክደኛ ፊት ታኖረዋለህ።
7 ፤ አሮንም የጣፋጭ ሽቱ እጣን ይጠንበት፤ በማለዳ በማለዳ መብራቶቹን ሲያዘጋጅ ይጠነው።
8 ፤ ይህን በእግዚአብሔር ፊት ለልጅ ልጃችሁ የዘወትር ዕጣን ይሆን ዘንድ አሮን በማታ ጊዜ መብራቶቹን ሲያበራ ያጥነዋል።
9 ፤ ሌላም ዕጣን፥ የሚቃጠለውንም መስዋዕት፥ የእህሉንም ቍርባን አታቀርብበትም፤ የመጠጥም ቍርባን አታፈስስበትም።
10 ፤ አሮንም በአመት አንድ ጊዜ በቀንዶቹ ላይ ማስተስረያ ያደርጋል፤ በአመት አንድ ጊዜ ለልጅ ልጃችሁ ማስተስረያ በሚሆን በኃጢአት መሥዋዕት ደም ማስተስረያ ያደርግበታል። ለእግዚአብሔር ቅድስተ ቅዱሳን ናት።
11 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
12 ፤ አንተ የእስራኤልን ልጆች ቍጥር ተቀብለህ፥ በቈጠርሃቸው ጊዜ መቅሰፍት እንዳይሆንባቸው፥ በቈጠርሃቸው ጊዜ ከእነርሱ ሰው ሁሉ እንደ ቍጥራቸው መጠን የነፍሱን ቤዛ ለእግዚአብሔር ይስጥ።
13 ፤ አልፎ የሚቈጠር ሁሉ ግማሽ ሰቅል እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን ይሰጣል፤ የሰቅል ግማሽ ለእግዚአብሔር ያነሣል።
14 ፤ ሰቅሉ ሀያ ኦቦሊ ነው። አልፎ የተቈጠረ ሁሉ፥ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም ከፍ ያለ፥ የእግዚአብሔርን ስጦታ ይሰጣል።
15 ፤ ለነፍሳችሁ ማስተስረያ የእግዚአብሔርን ስጦታ ስትሰጡ ባለ ጠጋው ከሰቅል ግማሽ አይጨምር፥ ድሀውም አያጕድል።
16 ፤ የማስተስረያውንም ገንዘብ ከእስራኤል ልጆች ወስደህ ለመገናኛው ድንኳን ማገልገያ ታደርገዋለህ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ለነፍሳችሁ ቤዛ እንዲሆን ለእስራኤል ልጆች መታሰቢያ ይሁን።
17 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
18 ፤ የመታጠቢያ ሰንና መቀመጫውን ከናስ ሥራ፤ በመገናኛው ድንኳንና በመሠዊያው መካከል እርሱን አድርገህ ውኃን ትጨምርበታለህ።
19 ፤ አሮንና ልጆቹም እጆቻቸውንና እግሮቻቸውን ይታጠቡበታል።
20 ፤ ወደ መገናኛው ድንኳን በገቡ ጊዜ፥ ለእግዚአብሔርም የእሳት መስዋዕት ያቃጥሉ ዘንድ ወደ መሠዊያው ሊያገለግሉ በቀረቡ ጊዜ፥ እንዳይሞቱ ይታጠቡበታል።
21 ፤ እንዳይሞቱም እጆቻቸውንና እግሮቻቸውን ይታጠቡ፤ ይህም ለእርሱ ከእርሱም በኋላ ለዘሩ የዘላለም ሥርዓት ይሆንላቸዋል።
22 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
23 ፤ አንተም ክቡሩን ሽቱ ውሰድ፤ የተመረጠ ከርቤ አምስት መቶ ሰቅል፥ ግማሽም ጣፋጭ ቀረፋ ሁለት መቶ አምሳ ሰቅል፥ የጠጅ ሣርም እንዲሁ ሁለት መቶ አምሳ ሰቅል፥
24 ፤ ብርጕድም አምስት መቶ ሰቅል እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን፥ የወይራ ዘይትም አንድ የኢን መስፈሪያ ትወስዳለህ።
25 ፤ በቀማሚም ብልሃት እንደ ተሠራ ቅመም፥ የተቀደሰ የቅብዓት ዘይት ታደርገዋለህ፤ የተቀደሰ የቅብዓት ዘይት ይሆናል።
26 ፤ የመገናኛውንም ድንኳን፥ የምስክሩንም ታቦት፥
27 ፤ ገበታውንም ዕቃውንም ሁሉ፥ መቅረዙንም ዕቃውንም፥ የዕጣን መሠዊያውንም፥
28 ፤ ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነውን መሠዊያና ዕቃውንም ሁሉ፥ የመታጠቢያውን ሰንና መቀመጫውንም ትቀባበታለህ።
29 ፤ ሁሉንም ትቀድሳቸዋለህ፥ ቅድስተ ቅዱሳንም ይሆናሉ፤ የሚነካቸውም ሁሉ ቅዱስ ይሆናል።
30 ፤ በክህነትም ያገለግሉኝ ዘንድ አሮንንና ልጆቹን ቅባቸው፥ ቀድሳቸውም።
31 ፤ አንተም ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ተናገር። ይህ ለልጅ ልጃችሁ የተቀደሰ የቅብዓት ዘይት ይሁንልኝ።
32 ፤ በሰው ሥጋ ላይ አይፍሰስ፤ እንደ እርሱም የተሰራ ሌላ ቅብዓት አታድርጉ፤ ቅዱስ ነው፥ ለእናንተም ቅዱስ ይሁን።
33 ፤ እንደ እርሱ ያለውን የሚያደርግ ሰው፥ በሌላም ሰው ላይ የሚያፈስሰው ከሕዝቡ ተለይቶ ይጥፋ።
34 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። ጣፋጭ ሽቱ ውሰድ፤ የሚንጠባጠብ ሙጫ፥ በዛጎል ውስጥ የሚገኝ ሽቱ፥ የሚሸትትም ሙጫ፥ ጥሩም እጣን ውሰድ፤ የሁሉም መጠን ትክክል ይሁን።
35 ፤ በቀማሚ ብልሃት እንደ ተሠራ፥ በጨው የተቀመመ ንጹሕና ቅዱስ ዕጣን አድርገው።
36 ፤ ከእርሱም ጥቂት ትወቅጣለህ፥ ታልመውማለህ፤ ከዚያም ወስደህ አንተን በምገናኝበት በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በምስክሩ ፊት ታኖረዋለህ። እርሱም የቅዱሳን ቅዱስ ይሁንላችሁ።
37 ፤ እንደ እርሱ የተሠራ ዕጣን ለእናንተ አታድርጉ፤ በእናንተ ዘንድም ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ይሁን።
38 ፤ ሊያሸትተውም እንደ እርሱ የሚያደርግ ሰው ከሕዝቡ ተለይቶ ይጥፋ።