ምዕራፍ 12

እግዚአብሔርም በግብፅ አገር ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው።
2 ፤ ይህ ወር የወሮች መጀመሪያ ይሁናችሁ፤ የዓመቱም መጀመሪያ ወር ይሁናችሁ።
3 ፤ ለእስራኤል ልጆች ሁሉ ተናገሩ፥ በሉአቸውም። በዚህ ወር በአሥረኛው ቀን ሰው ሁሉ ለአባቱ ቤት አንድ ጠቦት፥ ለአንድ ቤትም አንድ ጠቦት ይውሰድ።
4 ፤ የቤቱ ሰዎች ቍጥርም ለጠቦቱ የማይበቃ ቢሆን እርሱና ለቤቱ የቀረበው ጎረቤቱ እንደ ነፍሶቻቸው ቍጥር አንድ ጠቦት ይውሰድ፤ እያንዳንዱም እንደሚበላው መጠን ከጠቦቱ ይካፈሉ።
5 ፤ የእናንተ ጠቦት ነውር የሌለበት የአንድ ዓመት ተባት ይሁን፤ ከበጎች ወይም ከፍየሎች ውሰድ።
6 ፤ በዚህም ወር እስከ አሥራ አራተኛው ቀን ድረስ ጠብቁት፤ የእስራኤልም ማኅበር ጉባኤ ሁሉ ሲመሽ ይረዱት።
7 ፤ ከደሙም ወስደው በሚበሉበት ቤት ሁለቱን መቃንና ጉበኑን ይቅቡት።
8 ፤ በእሳት የተጠበሰውን ሥጋውንና ቂጣውን እንጀራ በዚያች ሌሊት ይብሉ፤ ከመራራ ቅጠል ጋር ይበሉታል።
9 ፤ ጥሬውን በውኃም የበሰለውን አትብሉ፥ ነገር ግን ከራሱ ከጭኑ ከሆድ ዕቃው ጋር በእሳት የተጠበሰውን ብሉት።
10 ፤ ከእርሱም እስከ ጥዋት አንዳች አታስቀሩ፤ እስከ ጥዋትም የቀረውን በእሳት አቃጥሉት።
11 ፤ ወገቦቻችሁን ታጥቃችሁ፥ ጫማችሁን በእግራችሁ፥ በትራችሁንም በእጃችሁ አድርጋችሁ እንዲህ ብሉት፥ ፈጥናችሁም ትበሉታላችህ፤ እርሱ የእግዚአብሔር ፋሲካ ነው።
12 ፤ እኔም በዚያች ሌሊት በግብፅ አገር አልፋለሁ፥ በግብፅም አገር ከሰው እስከ እንስሳ ድረስ በኵርን ሁሉ እገድላለሁ፤ በግብፅም አማልክት ሁሉ ላይ እፈርድባቸዋለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
13 ፤ ደሙም ባላችሁበት ቤቶች ምልክት ይሆንላችኋል፤ ደሙንም ባየሁ ጊዜ ከእናንተ አልፋለሁ፤ እኔም የግብፅን አገር በመታሁ ጊዜ መቅሰፍቱ ለጥፋት አይመጣባችሁም።
14 ፤ ይህም ቀን መታሰቢያ ይሁናችሁ፥ ለእግዚአብሔርም በዓል ታደርጉታላችሁ፤ ለልጅ ልጃችሁ ሥርዓት ሆኖ ለዘላለም ታደርጉታላችሁ።
15 ፤ ሰባት ቀን ቂጣ እንጀራ ትበላላችሁ፤ በመጀመሪያም ቀን እርሾውን ከቤታችሁ ታወጣላችሁ፤ ከመጀመሪያውም ቀን አንሥቶ እስከ ሰባተኛው ቀን እርሾ ያለበትን እንጀራ የሚበላ ነፍስ ከእስራኤል ተለይቶ ይጥፋ።
16 ፤ በመጀመሪያውም ቀን የተቀደሰ ጉባኤ እንዲሁም በሰባተኛውም ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይሆንላችኋል። ከሚበላው በቀር በእነርሱም ምንም አትሠሩም፥ ይህንም ብቻ ታደርጉታላችሁ።
17 ፤ በዚህም ቀን ሠራዊታችሁን ከግብፅ አገር አውጥቼአለሁና የቂጣውንም በዓል ጠብቁት፤ እንግዲህ ይህን ቀን ለልጅ ልጃችሁ ለዘላለም ሥርዓት ትጠብቃላችሁ።
18 ፤ በመጀመሪያውም ወር በአሥራ አራተኛው ቀን በመሸ ጊዜ ከወሩም እስከ ሀያ አንድ ቀን በመሸ ጊዜ የቂጣ እንጀራ ትበላላችሁ።
19 ፤ ሰባት ቀን በቤታችሁ እርሾ አይገኝ፤ እርሾ ያለበትንም እንጀራ የሚበላ ነፍስ፥ ከመጻተኛው ጀምሮ እስከ አገር ልጁ ድረስ፥ ከእስራኤል ማኅበር ተለይቶ ይጥፋ።
20 ፤ እርሾ ያለበትን ምንም አትብሉ፥ በቤቶቻችሁም ሁሉ ውስጥ ቂጣ እንጀራ ብሉ።
21 ፤ ሙሴም የእስራኤልን ሽማግሌዎች ጠርቶ አላቸው። በየቤታችሁ ጠቦት ምረጡ፥ ወስዳችሁም ለፋሲካ እረዱት።
22 ፤ ከሂሶጵ ቅጠልም ጭብጥ ውሰዱ፥ በዕቃ ውስጥ ባለውም ደም ንከሩት፥ በዕቃውም ውስጥ ካለው ደም ሁለቱን መቃኖችና ጉበኑን እርጩ፤ ከእናንተም አንድ ሰው ከቤቱ ደጅ እስኪነጋ ድረስ አይውጣ።
23 ፤ እግዚአብሔር ግብፃውያንን ይመታ ዘንድ ያልፋልና፤ ደሙንም በጉበኑና በሁለቱ መቃኖች ላይ ባየ ጊዜ እግዚአብሔር በደጁ ላይ ያልፋል፥ አጥፊውም ይመታችሁ ዘንድ ወደ ቤታችሁ እንዲገባ አይተውም።
24 ፤ ለእናንተ ለልጆቻችሁም ለዘላለም ሥርዓት አድርጋችሁ ይህችን ነገር ጠብቁ።
25 ፤ እንዲህም ይሆናል፤ እግዚአብሔር እንደ ተናገረ ወደ ሚሰጣችሁ አገር በገባችሁ ጊዜ ይህን አምልኮ ጠብቁት።
26 ፤ እንዲህም ይሆናል፤ ልጆቻችሁ። ይህ አምልኮ ለእናንተ ምንድር ነው?
27 ፤ ባሉአችሁ ጊዜ፥ እናንተ። በግብፅ አገር በእስራኤል ልጆች ቤቶች ላይ አልፎ ግብፃዊያንን በመታ ጊዜ፥ ቤቶቻችንን ያዳነ የእግዚአብሔር የማለፉ መሥዋዕት ይህች ናት ትሉአቸዋላችሁ።
28 ፤ ሕዝቡም ተጎነበሰ ሰገደም። የእስራኤልም ልጆች ሄዱ፥ እንዲሁም አደረጉ፤ እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንዳዘዘ እንዲሁ አደረጉ።
29 ፤ እንዲህም ሆነ፤ እኩል ሌሊት በሆነ ጊዜ እግዚአብሔር፥ በዙፋን ከተቀመጠው ከፈርዖን በኵር ጀምሮ በግዞት እስካሉት እስከ ምርኮኞቹ በኵር ድረስ፥ የግብፃውያንን በግብፅ ምድር የተገኘውን በኵር ሁሉ፥ የእንስሳውንም በኵሮች ሁሉ መታ።
30 ፤ ፈርዖንም ባሪያዎቹም ሁሉ ግብፃውያንም ሁሉ በሌሊት ተነሡ፤ የሞተ የሌለበት ቤት አልነበረምና በግብፅ ምድር ታላቅ ልቅሶ ሆነ።
31 ፤ ፈርዖንም ሙሴንና አሮንን በሌሊት ጠርቶ። እናንተ የእስራኤልም ልጆች ተነሡ፥ ከሕዝቤ መካከል ውጡ፤ ሂዱም፥ እንዳላችሁም እግዚአብሔርን አገልግሉ፤
32 ፤ እንዳላችሁም መንጎቻችሁንና ከብቶቻችሁን ውሰዱ፥ ሂዱም፥ እኔንም ደግሞ ባርኩኝ አለ።
33 ፤ ግብፃውያንም ፈጥነው ከምድሩ ይወጡ ዘንድ ሕዝቡን ያስቸኵሉአቸው ነበር። ሁላችን እንሞታለን ብለዋልና።
34 ፤ ሕዝቡም ሊጡን ሳይቦካ ተሸከሙ፥ ቡሃቃውንም በልብሳቸው ጠቅልለው በትከሻቸው ተሸከሙት።
35 ፤ የእስራኤልም ልጆች ሙሴ እንዳዘዘ አደረጉ፥ ከግብፃውያንም የብርንና የወርቅን ዕቃ ልብስንም ለመኑ።
36 ፤ እግዚአብሔርም ለሕዝቡ በግብፃውያን ፊት የፈለጉትን እንዲሰጡአቸው ሞገስን ሰጠ። እነርሱም ግብፃውያንን በዘበዙ።
37 ፤ የእስራኤልም ልጆች ከራምሴ ተነሥተው ወደ ሱኮት ሄዱ፤ ከሕፃናቱም ሌላ ስድስት መቶ ሺህ ሰው የሚያህል እግረኛ ነበረ።
38 ፤ ደግሞም ሌላ ብዙ ድብልቅ ሕዝብ መንጎችና ላሞችም እጅግ ብዙም ከብቶች ከእነርሱ ጋር ወጡ።
39 ፤ ከግብፅም ከእነርሱ ጋር ያወጡትን ሊጥ ጋገሩ፥ አልቦካም ነበርና ቂጣ እንጎቻ አደረጉት፤ ግብፃውያን በመውጣት ስላስቸኰሉአቸው ይቈዩ ዘንድ አልተቻላቸውም፥ ስንቅም አላሰናዱም ነበር።
40 ፤ የእስራኤልም ልጆች በግብፅ ምድር የተቀመጡት ዘመን አራት መቶ ሠላሳ ዓመት ነው።
41 ፤ እንዲህም ሆነ፤ አራት መቶ ሠላሳ ዓመት ከተፈጸመ በኋላ በዚያ ቀን የእግዚአብሔር ሠራዊት ሁሉ ከግብፅ ምድር ወጣ።
42 ፤ ይህች ሌሊት ከግብፅ ምድር ስላወጣቸው ለእግዚአብሔር የተጠበቀች ናት፤ ይህች ሌሊት በእስራኤል ልጆች ሁሉ ዘንድ እስከ ልጅ ልጃቸው ድረስ ለእግዚአብሔር የተጠበቀች ናት።
43 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን አለ። ይህ የፋሲካ ሕግ ነው፤ ከእርሱ እንግዳ ሰው አይብላ።
44 ፤ በብር የተገዛ ባሪያ ቢኖር ከተገረዘ በኋላ ከእርሱ ይብላ።
45 ፤ መጻተኛና ሞያተኛ ግን ከእርሱ አይብሉ።
46 ፤ በአንድ ቤትም ይበላ፤ ከሥጋውም አንዳች ከቤት ወደ ሜዳ አታውጡ፤ አጥንትም አትስበሩበት።
47 ፤ የእስራኤልም ጉባኤ ሁሉ ያድርጉት።
48 ፤ እንግዳ ሰውም በመካከላችሁ ቢቀመጥ ለእግዚአብሔርም ፋሲካን ሊያደርግ ቢወድድ፥ አስቀድሞ ወንድ ሁሉ ይገረዝ፥ ከዚያም ወዲያ ይቅረብ ያድርግም፤ እንደ አገር ልጅም ይሆናል፤ ያልተገረዘ ሁሉ ግን ከእርሱ አይብላ።
49 ፤ ለአገር ልጅ በእናንተ መካከልም ለሚቀመጡ እንግዶች አንድ ሥርዓት ይሆናል።
50 ፤ የእስራኤልም ልጆች ሁሉ እንዲህ አደረጉ፤ እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንዳዘዘ እንዲሁ አደረጉ።
51 ፤ በዚያም ቀን እግዚአብሔር የእስራኤልን ልጆች ከሠራዊታቸው ጋር ከግብፅ ምድር አወጣ።