ምዕራፍ 21

በፊታቸው የምታደርገው ሥርዓት ይህ ነው።
2 ፤ ዕብራዊ ባሪያ የገዛህ እንደሆነ ስድስት ዓመት ያገልግልህ፥ በሰባተኛውም በከንቱ አርነት ይውጣ።
3 ፤ ብቻውን መጥቶ እንደሆነ ብቻውን ይውጣ፤ ከሚስቱ ጋር መጥቶ እንደሆነ ሚስቱ ከእርሱ ጋር ትውጣ።
4 ፤ ጌታው ሚስት አጋብቶት እንደ ሆነ ወንዶች ወይም ሴቶች ልጆች ብትወልድለት፥ ሚስቱና ልጆችዋ ለጌታው ይሁኑ፥ እርሱም ብቻውን ይውጣ።
5 ፤ ባሪያውም። ጌታዬን ሚስቴን ልጅቼንም እወድዳለሁ፥ አርነት አልወጣም ብሎ ቢናገር፥ ጌታው ወደ ፈራጆች ይውሰደው፥
6 ፤ ወደ ደጁም ወደ መቃኑ አቅርቦ ጆሮውን በወስፌ ይብሳው፤ ለዘላለምም ባሪያው ይሁን።
7 ፤ ሰውም ሴት ልጁን ለባርነት ቢሸጥ ባሪያዎች እንደሚወጡ እርስዋ አትውጣ።
8 ፤ ጌታዋን ደስ ባታሰኘው በዎጆ ይስደዳት፤ ስለ ናቃት ለሌላ ወገን ሰዎች ይሸጣት ዘንድ አይገባውም።
9 ፤ ለልጁም ብድራት፥ ለሴት ልጆች የሚገባውን ያድርግላት።
10 ፤ ከእርስዋ ሌላም ቢያጋባው፥ መኖዋን ልብስዋንም ለምንጣፍዋም ተገቢውን አያጕድልባት።
11 ፤ ይህንም ሦስት ነገር ባያደርግላት ያለ ገንዘብ በከንቱ ትውጣ።
12 ፤ ሰው ሰውን ቢመታ ቢሞትም፥ እርሱ ፈጽሞ ይገደል።
13 ፤ ባይሸምቅበትም፥ ነገር ግን እግዚአብሔር ድንገት በእጁ ቢጥለው፥ የሚሸሽበት ስፍራ እኔ አደርግልሃለሁ።
14 ፤ ሰው ግን ቢደፍር፥ ባልጀራውን በተንኰል ቢገድለው፥ እንዲሞት ከመሠዊያዬ አውጥተህ ውሰደው።
15 ፤ አባቱን ወይም እናቱን የሚመታ ፈጽሞ ይገደል።
16 ፤ ሰውን ሰርቆ ቢሸጥ፥ ወይም በእጁ ቢገኝ፥ እርሱ ፈጽሞ ይገደል።
17 ፤ አባቱን ወይም እናቱን የሚሰድብ ፈጽሞ ይገደል።
18 ፤ ሁለት ሰዎችም ቢጣሉ፥ አንዱም ሌላውን በድንጋይ ወይም በጡጫ ቢመታ፥ ያም ባይሞት ነገር ግን ታምሞ በአልጋው ላይ ቢተኛ፥
19 ፤ ተነሥቶም በምርኩዝ ወደ ሜዳ ቢወጣ፥ የመታው ንጹሕ ነው፤ ነገር ግን ተግባሩን ስላስፈታው ገንዘብ ይከፍለው ዘንድ፥ ያስፈውሰውም ዘንድ ግዴታ አለበት።
20 ፤ ሰውም ወንድ ባሪያውን ወይም ሴት ባሪያውን በበትር ቢመታ፥ ቢሞትበትም፥ ፈጽሞ ይቀጣ።
21 ፤ የተመታው ግን አንድ ወይም ሁለት ቀን ቢቈይ ገንዘቡ ነውና አይቀጣ።
22 ፤ ሁለት ሰዎች ቢጣሉ፥ ያረገዘችንም ሴት ልጁን እስክትጨነግፍ ቢገፉአት ባትጐዳ ግን፥ የሴቲቱ ባል የጫነበትን ያህል ካሳ ይስጥ፤ ፈራጆቹም እንደ ፈረዱበት ይክፈል።
23 ፤ ጕዳት ግን ቢያገኛት ሕይወት በሕይወት፥
24 ፤ ዓይን በዓይን፥ ጥርስ በጥርስ፥ እጅ በእጅ፥
25 ፤ እግር በእግር፥ መቃጠል በመቃጠል፥ ቍስል በቍስል፥ ግርፋት በግርፋት ይከፈል።
26 ፤ ሰውም የባሪያውን ወይም የባሪይይቱን ዓይን ቢመታ ቢያጠፋውም፥ ስለ ዓይኑ አርነት ያውጣው።
27 ፤ የባሪያውን ወይም የባሪያይቱን ጥርስ ቢሰብር፥ ስለ ጥርሱ አርነት ያውጣው።
28 ፤ በሬም ወንድን ወይም ሴትን እስኪሞቱ ድረስ ቢወጋ፥ በሬው ይወገር፥ ሥጋውም አይበላ፤ የበሬው ባለቤት ግን ንጹሕ ነው።
29 ፤ በሬው ግን አስቀድሞ ተዋጊ ቢሆን፥ ሰዎችም ለባለቤቱ ቢመሰክሩለት ባይጠብቀውም፥ ወንድንም ወይም ሴትን ቢገድል፥ በሬው ይወገር፥ ባለቤቱ ደግሞ ይገደል።
30 ፤ ከእርሱ ግን ካሳ ቢፈልጉ፥ የሕይወቱን ዎጆ የጫኑበትን ያህል ይስጥ።
31 ፤ ደግሞ ወንድን ልጅ ቢወጋ ሴትንም ልጅ ቢወጋ፥ ይህንኑ ፍርድ ያድርጉበት።
32 ፤ በሬው ወንድ ባሪያ ወይም ሴት ባሪያ ቢወጋ፥ የበሬው ባለቤት ሠላሳ የብር ሰቅል ለጌታቸው ይስጥ፥ በሬውም ይወገር።
33 ፤ ሰውም ጕድጓድ ቢከፍት፥ ወይም ጕድጓድ ቢቈፍር ባይከድነውም፥ በሬም ወይም አህያ ቢወድቅበት፥
34 ፤ የጕድጓዱ ባለቤት ዋጋቸውን ለባለቤታቸው ይክፈል፤ የሞተውም ለእርሱ ይሁን።
35 ፤ የሰው በሬ የሌላውን በሬ እስኪሞት ድረስ ቢወጋ፥ ደኅናውን በሬ ይሽጡ፥ ዋጋውንም በትክክል ይካፈሉ፤ የሞተውንም ደግሞ በትክክል ይካፈሉ።
36 ፤ በሬውም አስቀድሞ ተዋጊ መሆኑ ቢታወቅ፥ ባለቤቱም ባይጠብቀው፥ በሬውን በበሬው ፈንታ ይስጥ፥ የሞተውም ለእርሱ ይሁነው።