ኦሪት ዘጸአት
ምዕራፍ 39
እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው፥ በመቅደሱ ለማገልገል ከሰማያዊ ከሐምራዊም ከቀይ ግምጃም በብልሃት የተሠራ ልብስ፥ ለአሮንም የተቀደሰውን ልብስ አደረጉ።
2 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው፥ ኤፉዱን ከወርቅ ከሰማያዊም ከሐምራዊም ከቀይ ግምጃም ከተፈተለም ከጥሩ በፍታ አደረገ።
3 ፤ ወርቁንም ቀጥቅጠው እንደ ቅጠል ስስ አድርገው እንደ ፈትል ቈረጡ። ብልህ ሠራተኛም እንደሚሠራ ሰማያዊ ሐምራዊም ቀይም ግምጃ የተፈተለም ጥሩ በፍታ ከእርሱ ጠለፉ።
4 ፤ ሁለቱ ወገን እንዲጋጠም በሁለቱ ጫንቃዎች ላይ የሚጋጠም ልብስ አደረጉት።
5 ፤ በላዩም መታጠቂያ ሆኖ በብልሃት የተጠለፈው የኤፉዱ ቋድ እንደ እርሱ ከእርሱም ጋር አንድ ነበረ፤ ከወርቅና ከሰማያዊ ከሐምራዊ ከቀይ ግምጃም ከተፈተለም ከጥሩ በፍታ የተሠራ ነበረ።
6 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው፥ በወርቅ ፈርጥ የተያዙ የመረግድ ድንጋዮች ሠርተው እንደ ማኅተም ቅርጽ የእስራኤልን ልጆች ስም ቀረጹባቸው።
7 ፤ ለእስራኤል ልጆች የመታሰቢያ ድንጋዮች ይሆኑ ዘንድ በኤፉዱ ጫንቃዎች ላይ አደረጋቸው።
8 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው፥ የደረቱን ኪስ ብልህ ሠራተኛ እንደሚሠራ እንደ ኤፉዱ አሠራር ከወርቅና ከሰማያዊ ከሐምራዊም ከቀይም ግምጃ ከተፈተለም ከጥሩ በፍታ አደረገው።
9 ፤ አራት ማዕዘንም ነበረ፤ የደረቱን ኪስም ድርብ አደረጉ፤ ርዝመቱ ስንዝር፥ ወርዱም ስንዝር፥ ድርብም ነበረ።
10 ፤ ዕንቍዎቹንም በአራት ተራ አደረጉበት፤ በፊተኛውም ተራ ሰርድዮን፥ ቶጳዝዮን፥ የሚያብረቀርቅ ዕንቍ፤
11 ፤ በሁለተኛውም ተራ በሉር፥ ሰንፔር፥ አልማዝ፤
12 ፤ በሦስተኛውም ተራ ያክንት፥ ኬልቄዶን፥ አሜቴስጢኖስ፤
13 ፤ በአራተኛውም ተራ ቢረሌ፥ መረግድ፥ ኢያስጲድ በወርቅ ፈርጥ ተደረጉ።
14 ፤ የዕንቍዎችም ድንጋዮች እንደ አሥራ ሁለቱ እንደ እስራኤል ልጆች ስሞች ነበሩ፤ በየስማቸውም ማተሚያ እንደሚቀረጽ ተቀረጹ፥ ስለ አሥራ ሁለቱም ነገዶች ነበሩ።
15 ፤ ለደረቱ ኪስም የተጐነጐኑትን ድሪዎች እንደ ገመድ አድርገው ከጥሩ ወርቅ ሠሩ።
16 ፤ ሁለትም የወርቅ ፈርጦች፥ ሁለትም የወርቅ ቀለበቶች ሠሩ፤ ሁለቱንም ቀለበቶች በደረቱ ኪስ በሁለቱ ወገን አደረጉ።
17 ፤ ሁለቱንም የተጐነጐኑትን የወርቅ ድሪዎች በደረቱ ኪስ ወገኖች ወዳሉት ወደ ሁለቱ ቀለበቶች አገቡ።
18 ፤ የሁለቱንም ድሪዎች ጫፎች በሁለቱ ፈርጦች ውስጥ አግብተው በኤፉዱ ጫንቃዎች ላይ በፊታቸው አደረጉ።
19 ፤ ሁለቱንም የወርቅ ቀለበቶች ሠሩ፥ እነርሱንም በኤፉዱ ፊት ለፊት ባለው በደረቱ ኪስ በሁለት ጫፎቹ ላይ አደረጉአቸው።
20 ፤ ደግሞም ሁለት የወርቅ ቀለበቶች ሠሩ፥ በኤፉዱም ፊት፥ ከጫንቃዎች በታች፥ በብልሃት ከተጠለፈ ከኤፉዱ ቋድ በላይ፥ በመያዣው አጠገብ አደረጉአቸው።
21 ፤ የደረቱ ኪስ በብልሃት ከተጠለፈው ከኤፉዱ ቋድ በላይ እንዲሆን፥ ከኤፉዱም እንዳይለይ የደረቱን ኪስ ከቀለበቶቹ ጋር ወደ ኤፉዱ ቀለበቶች በሰማያዊ ፈትል አሰሩት።
22 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው፥ የኤፉዱን ቀሚስ ሞላውን በሸማኔ ሥራ ሰማያዊ አደረገው።
23 ፤ በቀሚሱም መካከል አንገትጌ ነበረ፤ እንዳይቀደድም እንደ ጥሩር የተሠራ ጥልፍ በአንገትጌው ዙሪያ ነበረ።
24 ፤ በቀሚሱም ታችኛ ዘርፍ ከሰማያዊ ከሐምራዊም ከቀይም ግምጃ፥ ከተፈተለ በፍታም ሮማኖች አደረጉ።
25 ፤ ከጥሩ ወርቅም ሻኵራዎችን ሠሩ፥ ሻኵራዎቹንም ከሮማኖች መካከል በቀሚሱ ዘርፍ ዙሪያ አደረጉ።
26 ፤ በቀሚሱ ዘርፍ ዙሪያ ሻኵራንና ሮማንን፥ ሻኵራንና ሮማንን ለማገልገል አደረጉ።
27 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው፥ እንደ ሸማኔ ሥራ ከጥሩ በፍታ ለአሮንና ለልጆቹ ሸሚዞችን፥
28 ፤ ከጥሩ በፍታም መጠምጠሚያውን፥ ከጥሩ በፍታም መልካሞቹን ቆቦች፥ ከተፈተለም ከጥሩ በፍታ የእግር ሱሪዎችን፥
29 ፤ ከተፈተለም ከጥሩ በፍታ፥ ከሰማያዊም ከሐምራዊም ከቀይም ግምጃ በጥልፍ አሠራር የተሠራ መታጠቂያውን አደረጉ።
30 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው፥ ከጥሩ ወርቅ የተቀደሰውን የአክሊል ምልክት ሠሩ፤ በእርሱም እንደ ማኅተም ቅርጽ አድርገው። ቅድስና ለእግዚአብሔር የሚል ጻፉበት።
31 ፤ በመጠምጠሚያውም ላይ ያንጠለጥሉት ዘንድ ሰማያዊውን ፈትል አሰሩበት።
32 ፤ እንዲሁም የመገናኛው ድንኳን የማደሪያው ሥራ ሁሉ ተጨረሰ። እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው ሁሉ የእስራኤል ልጆች አደረጉ፤ እንዲሁ አደረጉ።
33 ፤ ማደሪያውንም፥ ድንኳኑንም፥ ዕቃውንም ሁሉ ወደ ሙሴ አመጡ፤ መያዣዎቹን፥ ሳንቆቹን፥ መወርወሪያዎቹን፥ ምሰሶቹንም፥ እግሮቹንም፤
34 ፤ ከቀይ ከአውራ በግ ቁርበትም የተሠራ መደረቢያ፥ ከአቆስጣ ቁርበትም የተሠራ መደረቢያ፥ የሚሸፍነውንም መጋረጃ፤
35 ፤ የምስክሩንም ታቦት፥ መሎጊያዎቹንም፥ የስርየት መክደኛውንም፤
36 ፤ ገበታውንም፥ ዕቃውንም ሁሉ፥ የገጹንም ኅብስት፤
37 ፤ ጥሩውንም መቅረዝ፥ መብራቶቹንም፥ በተራ የሚሆኑትንም ቀንዲሎች፥ ዕቃውንም ሁሉ፥ የመብራቱንም ዘይት፤
38 ፤ የወርቁንም መሠዊያ፥ የቅብዓቱንም ዘይት፥ ጣፋጩንም ዕጣን፥ የድንኳኑንም ደጃፍ መጋረጃ፤
39 ፤ የናሱንም መሠዊያ፥ የናሱንም መከታ፥ መሎጊያዎቹንም፥ ዕቃውንም ሁሉ፥ የመታጠቢያውን ሰንም መቀመጫውንም፤
40 ፤ የአደባባዩንም መጋረጆች፥ ምሰሶቹንም፥ እግሮቹንም፥ የአደባባዩንም ደጃፍ መጋረጃ፥ አውታሮቹንም፥ ካስማዎቹንም፥ ለመገናኛው ድንኳን ለማደሪያው ማገልገያ የሚሆኑን ዕቃዎች ሁሉ፤
41 ፤ በመቅደስ ውስጥ ለማገልገል በብልሃት የተሠሩትን ልብሶች፥ በክህነትም ያገለግሉበት ዘንድ የተቀደሱትን የካህኑን የአሮንን ልብሶች፥ የልጆቹንም ልብሶች አመጡ።
42 ፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘ ሁሉ እንዲሁ የእስራኤል ልጆች ሥራውን ሁሉ ሠሩ።
43 ፤ ሙሴም ሥራውን ሁሉ አየ፥ እነሆም አድርገውት ነበር፤ እግዚአብሔር እንዳዘዘው እንዲሁ አድርገውት ነበር፤ ሙሴም ባረካቸው።