ምዕራፍ 14

እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
2 ፤ ተመልሰው በሚግዶልና በባሕር መካከል፥ በበኣልዛፎንም ፊት ለፊት ባለው በፊሀሒሮት ፊት እንዲሰፍሩ ለእስራኤል ልጆች ተናገር፤ ከእርሱም አጠገብ በባሕር ዳር ትሰፍራላችሁ።
3 ፤ ፈርዖንም ስለ እስራኤል ልጆች። በምድር ይቅበዘበዛሉ፥ ምድረ በዳም ዘጋቻቸው ይላል።
4 ፤ እኔም የፈርዖንን ልብ አጸናለሁ፥ እርሱም ያባርራቸዋል፤ በፈርዖንና በሠራዊቱም ሁሉ ላይ ክብር አገኛለሁ፤ ግብፃውያንም እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። እነርሱም እንዲሁ አደረጉ።
5 ፤ ሕዝቡም እንደ ኰበለሉ ለግብፅ ንጉሥ ነገሩት፤ የፈርዖንና የባሪያዎቹም ልብ በሕዝቡ ላይ ተለወጠና። እንዳይገዛልን እስራኤልን የለቀቅነው ምን አድርገናል? አሉ።
6 ፤ ሰረገላውንም አሰናዳ፥ ሕዝቡንም ከእርሱ ጋር ወሰደ፤
7 ፤ ስድስት መቶ የተመረጡ ሰረገሎችንም፥ የግብፅንም ፈረሶች ሁሉ፥ በእያንዳንዱም ሰረገላ ሁሉ ላይ ሦስተኞችን ወሰደ።
8 ፤ እግዚአብሔርም የግብፅን ንጉሥ የፈርዖንን ልብ አጸና፥ እርሱም የእስራኤልን ልጆች አሳደደ፤ የእስራኤልም ልጆች ከፍ ባለች እጅ ወጡ።
9 ፤ ግብፃውያንም የፈርዖን ፈረሶች ሰረገሎቹም ፈረሰኞቹም ሠራዊቱም ሁሉ፥ አሳደዱአቸው፤ በባሕሩ ዳር በበኣልዛፎን ፊት ለፊት ባለው በፊሀሒሮት አጠገብ ሰፍረው አገኙአቸው።
10 ፤ ፈርዖንም በቀረበ ጊዜ የእስራኤል ልጆች ዓይናቸውን አነሡ፥ እነሆም ግብፃውያን በኋላቸው ገሥግስው ነበር፤ የእስራኤልም ልጆች እጅግ ፈሩ፥ ወደ እግዚአብሔርም ጮኹ።
11 ፤ ሙሴንም። በግብፅ መቃብር ስላልኖረ በምድረ በዳ እንሞት ዘንድ አወጣኸንን? ከግብፅ ታወጣን ዘንድ ይህ ያደረግህብን ምንድር ነው?
12 ፤ በምድረ በዳ ከምንሞት ብንገዛላቸው ይሻላልና። ተወን፥ ለግብፃውያን እንገዛ ብለን በግብፅ ሳለን ያልንህ ቃል ይህ አይደለምን? አሉት።
13 ፤ ሙሴም ለሕዝቡ። አትፍሩ፥ ዛሬ የምታዩአቸውን ግብፃውያንን ለዘላለም አታዩአቸውምና ቁሙ፥ ዛሬ ለእናንተ የሚያደርጋትን የእግዚአብሔርን ማዳን እዩ።
14 ፤ እግዚአብሔር ስለ እናንተ ይዋጋል፥ እናንተም ዝም ትላላችሁ አላቸው።
15 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። ለምን ትጮኽብኛለህ? እንዲጓዙ ለእስራኤል ልጆች ንገር።
16 ፤ አንተም በትርህን አንሣ፥ እጅህንም በባሕሩ ላይ ዘርጋ፥ ክፈለውም፤ የእስራኤልም ልጆች በባሕሩ ውስጥ በየብስ ያልፋሉ።
17 ፤ እነሆም እኔ የግብፃውያንን ልብ አጸናለሁ፥ በኋላቸውም ይገባሉ፤ በፈርዖንና በሠራዊቱም ሁሉ በሰረገሎቹም በፈረሰኞቹም ላይ ክብር አገኛለሁ።
18 ፤ ግብፃውያንም በፈርዖንና በሰረገሎቹ በፈረሰኞቹም ላይ ክብር ባገኘሁ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።
19 ፤ በእስራኤልም ሠራዊት ፊት ይሄድ የነበረው የእግዚአብሔር መልአክ ፈቀቅ ብሎ በኋላቸው ሄደ፤ የደመናውም ዓምድ ከፊታቸው ፈቀቅ ብሎ በኋላቸው ቆመ፥
20 ፤ በግብፃውያን ሰፈርና በእስራኤል ሰፈር መካከልም ገባ፤ በዚያም ደመናና ጨለማ ነበረ፥ በዚህ በኩል ግን ሌሊቱን አበራ፤ ሌሊቱንም ሁሉ እርስ በእርሳቸው አልተቃረቡም።
21 ፤ ሙሴም በባሕሩ ላይ እጁን ዘረጋ፤ እግዚአብሔርም ሌሊቱን ሁሉ ጽኑ የምሥራቅ ነፋስ አምጥቶ ባሕሩን አስወገደው፥ ባሕሩንም አደረቀው፥ ውኃውም ተከፈለ።
22 ፤ የእስራኤልም ልጆች በባሕሩ መካከል በየብስ ገቡ፤ ውኃውም በቀኛቸውና በግራቸው እንደ ግድግዳ ሆነላቸው።
23 ፤ ግብፃውያንም፥ የፈርዖን ፈረሶችና ሰረገሎች ፈረሰኞቹም ሁሉ፥ እያሳደዱ በኋላቸው ወደ ባሕር መካከል ገቡ።
24 ፤ ንጋትም በሆነ ጊዜ እግዚአብሔር በእሳትና በደመና ዓምድ ሆኖ የግብፃውያንን ሠራዊት ተመለከተ፥ የግብፃውያንንም ሠራዊት አወከ።
25 ፤ የሰረገሎቹንም መንኰራኵር አሰረ፥ ወደ ጭንቅም አገባቸው፤ ግብፃውያንም። እግዚአብሔር በግብፃውያን ላይ ይዋጋላቸዋልና ከእስራኤል ፊት እንሽሽ አሉ።
26 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን። እጅህን በባሕሩ ላይ ዘርጋ፥ ውኃውም በግብፃውያን በሰረገሎቻቸውም በፈረሰኞቻቸውም ላይ ይመለስ አለው።
27 ፤ ሙሴም እጁን በባሕሩ ላይ ዘረጋ፥ ባሕሩም ማለዳ ወደ መፍሰሱ ተመለሰ፤ ግብፃውያንም ከእርሱ ሸሹ፥ እግዚአብሔርም ግብፃውያንን በባሕሩ መካከል ጣላቸው።
28 ፤ ውኃውም ተመልሶ በኋላቸው ወደ ባሕር የገቡትን ሰረገሎችን ፈረሰኞችንም የፈርዖንንም ሠራዊት ሁሉ ከደነ፤ ከእነርሱም አንድ ስንኳ አልቀረም።
29 ፤ የእስራኤል ልጆች ግን በባሕሩ ውስጥ በየብስ ሄዱ፤ ውኆችም በቀኛቸውና በግራቸው እንደ ግድግዳ ሆኑላችው።
30 ፤ እግዚአብሔር በዚያን ቀን እስራኤልን እንደዚህ ከግብፃውያን እጅ አዳነ፤ እስራኤልም የግብፃውያንን ሬሳ በባሕር ዳር አዩ።
31 ፤ እስራኤልም እግዚአብሔር በግብፃውያን ላይ ያደረጋትን ታላቂቱን እጅ አዩ፥ ሕዝቡም እግዚአብሔርን ፈሩ፥ በእግዚአብሔርም በባሪያውም በሙሴ አመኑ።