መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ።
ምዕራፍ 22
ሶርያና እስራኤልም ሳይዋጉ ሦስት ዓመት ተቀመጡ።
2 ፤ በሦስተኛውም ዓመት የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ወደ እስራኤል ንጉሥ ወረደ።
3 ፤ የእስራኤልም ንጉሥ ባሪያዎቹን። ሬማት ዘገለዓድ የእኛ እንደ ሆነች፥ እኛም ከሶርያ ንጉሥ እጅ ሳንወስዳት ዝም እንዳልን ታውቃላችሁን? አላቸው።
4 ፤ ኢዮሣፍጥንም። በሬማት ዘገለዓድ እንዋጋ ዘንድ ከእኔ ጋር ትመጣለህን? አለው። ኢዮሣፍጥም የእስራኤልን ንጉሥ። እኔ እንደ አንተ፥ ሕዝቤም እንደ ሕዝብህ፥ ፈረሶቼም እንደ ፈረሶችህ ናቸው አለው።
5 ፤ ኢዮሣፍጥም የእስራኤልን ንጉሥ። የእግዚአብሔርን ቃል አስቀድመህ ትጠይቅ ዘንድ እለምንሃለሁ አለው።
6 ፤ የእስራኤልም ንጉሥ ነቢያቶቹን አራት መቶ የሚያህሉትን ሰዎች ሰብስቦ። ወደ ሬማት ዘገለዓድ ለሰልፍ ልሂድን? ወይስ ልቅር? አላቸው። እነርሱም። እግዚአብሔር በንጉሥ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና ውጣ አሉት።
7 ፤ ኢዮሣፍጥ ግን። እንጠይቀው ዘንድ ሌላ የእግዚአብሔር ነቢይ በዚህ አይገኝምን? አለ።
8 ፤ የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሣፍጥን። እግዚአብሔርን የምንጠይቅበት የይምላ ልጅ ሚክያስ የሚባል አንድ ሰው አለ፤ ነገር ግን ክፉ እንጂ መልካም ትንቢት አይናገርልኝምና እጠላዋለሁ አለው። ኢዮሣፍጥም። ንጉሥ እንዲህ አይበል አለ።
9 ፤ የእስራኤልም ንጉሥ አንዱን ጃንደረባ ጠርቶ። የይምላን ልጅ ሚክያስን ፈጥነህ አምጣ አለው።
10 ፤ የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ልብሰ መንግሥት ለብሰው በሰማርያ በር መግቢያ አጠገብ በአደባባይ በዙፋኖቻቸው ላይ ተቀምጠው ነበር፤ ነቢያቶቹም ሁሉ በፊታቸው ትንቢት ይናገሩ ነበር።
11 ፤ የክንዓና ልጅ ሴዴቅያስም የብረት ቀንዶች ሠርቶ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እስኪጠፉ ድረስ በእነዚህ ሶርያውያንን ትወጋለህ አለ።
12 ፤ ነቢያትም ሁሉ። እግዚአብሔር በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና ወደ ሬማት ዘገለዓድ ሂድና ተከናወን እያሉ እንዲህ ትንቢት ይናገሩ ነበር።
13 ፤ ሚክያስንም ሊጠራ የሄደ መልእክተኛ። እነሆ፥ ነቢያት ሁሉ በአንድ አፍ ሆነው ለንጉሡ መልካምን ይናገራሉ፤ ቃልህም እንደ ቃላቸው እንዲሆን መልካም እንድትናገር እለምንሃለሁ አለው።
14 ፤ ሚክያስም። ሕያው እግዚአብሔርን! እግዚአብሔር የሚነግረኝን እርሱን እናገራለሁ አለ።
15 ፤ ወደ ንጉሡም በመጣ ጊዜ ንጉሡ። ሚክያስ ሆይ፥ ወደ ሬማት ዘገለዓድ ለሰልፍ እንሂድን? ወይስ እንቅር? አለው፤ እርሱም። ውጣና ተከናወን፤ እግዚአብሔርም በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታል ብሎ መለሰለት።
16 ፤ ንጉሡም። ከእውነት በቀር በእግዚአብሔር ስም እንዳትነግረኝ ስንት ጊዜ አምልሃለሁ? አለው።
17 ፤ እርሱም። እስራኤል ሁሉ ጠባቂ እንደሌላቸው በጎች በተራሮች ላይ ተበትነው አየሁ፤ እግዚአብሔርም። ለእነዚህ ጌታ የላቸውም እያንዳንዱም በሰላም ወደ ቤቱ ይመለስ አለ ብሎ ተናገረ።
18 ፤ የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሣፍጥን። ክፉ እንጂ መልካም እንደማይናገርልኝ አላልሁህምን? አለው።
19 ፤ ሚክያስም አለ። እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቃል ስማ፤ እግዚአብሔር በዙፋኑ ተቀምጦ፥ የሰማይም ሠራዊት ሁሉ በቀኙና በግራው ቆመው አየሁ።
20 ፤ እግዚአብሔርም። ወጥቶ በሬማት ዘገለዓድ ይወድቅ ዘንድ አክዓብን የሚያሳስት ማን ነው? አለ። አንዱም እንዲህ ያለ ነገር፥ ሌላውም እንዲያ የለ ነገር ተናገረ።
21 ፤ መንፈስም ወጣ በእግዚአብሔርም ፊት ቆሞ። እኔ አሳስተዋለሁ አለ።
22 ፤ እግዚአብሔርም። በምን? አለው፤ እርሱም። ወጥቼ በነቢያቶቹ ሁሉ አፍ ሐሰተኛ መንፈስ እሆናለሁ አለ። እግዚአብሔርም። ማሳሳትስ ታሳስተዋለህ፥ ይሆንልሃልም፤ ውጣ፥ እንዲሁም አድርግ አለ።
23 ፤ አሁንም። እነሆ፥ እግዚአብሔር በእነዚህ በነቢያትህ ሁሉ አፍ ሐሰተኛ መንፈስ አድርጎአል፤ እግዚአብሔርም በላይህ ክፉ ተናግሮብሃል።
24 ፤ የክንዓናም ልጅ ሴዴቅያስ ቀረበ፥ ሚክያስንም ጕንጩን በጥፊ መታውና። አንተን ሊናገር የእግዚአብሔር መንፈስ በምን መንገድ ከእኔ አለፈ? አለ።
25 ፤ ሚክያስም። እነሆ፥ በዚያ ቀን ልትሸሸግ ወደ እልፍኝህ በሄድህ ጊዜ ታያለህ አለ።
26 ፤ የእስራኤልም ንጉሥ። ሚክያስን ውሰዱ፥ ወደ ከተማይቱም ሹም ወደ አሞን ወደ ንጉሡም ልጅ ወደ ኢዮአስ መልሳችሁ። ንጉሡ እንዲህ ይላል።
27 ፤ በደኅና እስክመለስ ድረስ ይህን ሰው በግዞት አኑሩት፥ የመከራም እንጀራ መግቡት፥ የመከራም ውኃ አጠጡት በሉ አለ።
28 ፤ ሚክያስም። በደኅና ብትመለስ እግዚአብሔር በእኔ የተናገረ አይደለም አለ። ደግሞም። አሕዛብ ሁሉ ሆይ፥ ስሙኝ አለ።
29 ፤ የእስራኤልም ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ወደ ሬማት ዘገለዓድ ወጡ።
30 ፤ የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሣፍጥን። ልብሴን ለውጬ ወደ ሰልፍ እገባለሁ፤ አንተ ግን ልብስህን ልበስ አለው። የእስራኤልም ንጉሥ ልብሱን ለውጦ ወደ ሰልፍ ገባ።
31 ፤ የሶርያም ንጉሥ ሠላሳ ሁለቱን የሰረገሎች አለቆች። ከእስራኤል ንጉሥ በቀር፥ ታናሽ ቢሆን ወይም ታላቅ ከማናቸውም ጋር አትግጠሙ ብሎ አዝዞ ነበር።
32 ፤ የሰረገሎች አለቆችም ኢዮሣፍጥን ባዩ ጊዜ። በእውነት የእስራኤል ንጉሥ ነው አሉ፤ ይገጥሙትም ዘንድ ከበቡት፤ ኢዮሣፍጥም ጮኸ።
33 ፤ የሰረገሎች አለቆችም የእስራኤል ንጉሥ እንዳልሆነ ባዩ ጊዜ እርሱን ከማሳደድ ተመለሱ።
34 ፤ አንድ ሰውም ቀስቱን ድንገት ገትሮ የእስራኤልን ንጉሥ በጥሩሩ ልብስ መጋጠሚያ በኩል ወጋው፤ ሰረገለኛውንም። መልሰህ ንዳ፥ ተወግቻለሁና ከሰልፍ ውስጥ አውጣኝ አለው።
35 ፤ በዚያም ቀን ሰልፍ በረታ፤ ንጉሡም በሶርያውያን ፊት በሰረገላው ላይ ተደግፎ ነበር፥ ማታም ሞተ፤ የቍስሉም ደም በሰረገላው ውስጥ ፈሰሰ።
36 ፤ በሠራዊቱም መካከል ፀሐይ ስትገባ። ንጉሡ ሞቶአልና እያንዳንዱ ወደ ከተማው፥ እያንዳንዱም ወደ አገሩ ይሂድ የሚል ጩኸት ሆነ።
37 ፤ ወደ ሰማርያም መጡ፥ ንጉሡንም በሰማርያ ቀበሩት።
38 ፤ አመንዝሮች በታጠቡባት በሰማርያ ኵሬ ሰረገላውን አጠቡት፥ እግዚአብሔርም እንደ ተናገረው ቃል ውሾች ደሙን ላሱት።
39 ፤ የቀረውም የአክዓብ ነገር፥ ያደረገውም ሁሉ፥ ከዝሆን ጥርስም የሠራው ቤት፥ የሠራቸውም ከተሞች ሁሉ፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?
40 ፤ አክዓብም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በእርሱም ፋንታ ልጁ አካዝያስ ነገሠ።
41 ፤ አክዓብም በነገሠ በአራተኛው ዓመት የአሳ ልጅ ኢዮሣፍጥ በይሁዳ ላይ ነገሠ።
42 ፤ ኢዮሣፍጥ መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሠላሳ አምስት ዓመት ጎበዝ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ሀያ አምስት ዓመት ነገሠ። እናቱም ዓዙባ የተባለች የሺልሒ ልጅ ነበረች።
43 ፤ በአባቱም በአሳ መንገድ ሁሉ ሄደ፥ ከእርሱም ፈቀቅ አላለም፥ በእግዚአብሔርም ፊት ቅን አደረገ፤ ነገር ግን በኮረብቶች ላይ ያሉትን መስገጃዎች አላራቀም፤ ሕዝቡ ገና በኮረብቶቹ ላይ ባሉት መስገጃዎች ይሠዋና ያጥን ነበር።
44 ፤ ኢዮሣፍጥም ከእስራኤል ንጉሥ ጋር ታረቀ። vፕ
45 ፤ የቀረውም የኢዮሣፍጥ ነገር፥ የሠራውም ጭከና፥ እንዴትም እንደ ተወጋ፥ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?
46 ፤ ከአባቱ ከአሳ ዘመን የተረፉትን ሰዶማውያን ከምድር አጠፋ።
47 ፤ በኤዶምያስም ንጉሥ አልነበረም፤ ሹሙም እንደ ንጉሥ ነበረ።
48 ፤ ኢዮሣፍጥም ወደ ኦፊር ሄደው ወርቅ ያመጡ ዘንድ የተርሴስን መርከቦች ሠራ፤ ነገር ግን መርከቦቹ በዔጽዮንጋብር ተሰበሩ እንጂ አልሄዱም።
49 ፤ የአክዓብም ልጅ አካዝያስ ኢዮሣፍጥን። ባሪያዎቼ ከባሪያዎችህ ጋር በመርከብ ይሂዱ አለው፤ ኢዮሣፍጥ ግን አልወደደም።
50 ፤ ኢዮሣፍጥም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በአባቱም በዳዊት ከተማ ከአባቶቹ ጋር ተቀበረ፤ በእርሱም ፋንታ ልጁ ኢዮራም ነገሠ።
51 ፤ በይሁዳም ንጉሥ በኢዮሣፍጥ በአሥራ ሰባተኛው ዓመት የአክዓብ ልጅ አካዝያስ በእስራኤል ላይ በሰማርያ መንገሥ ጀመረ፤ በእስራኤልም ላይ ሁለት ዓመት ነገሠ።
52 ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ አደረገ፥ በአባቱና በእናቱም መንገድ፥ እስራኤልንም ባሳተው በናባጥ ልጅ በኢዮርብዓም መንገድ ሄደ።
53 ፤ በኣልንም አመለከ ሰገደለትም፤ አባቱም እንዳደረገ ሁሉ የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን አስቈጣ።