መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ።

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22


ምዕራፍ 1

ንጉሡ ዳዊትም ሸመገለ ዕድሜውም በዛ፤ ልብስም ደረቡለት፥ ነገር ግን አይሞቀውም ነበር።
2 ፤ ባሪያዎቹም። ለጌታችን ለንጉሡ ድንግል ትፈለጋለች፤ በንጉሡም ፊት ቆማ ታገልግለው፥ በጌታችንም በንጉሡ ብብት ተኝታ ታሙቀው አሉት።
3 ፤ በእስራኤልም አገር ሁሉ የተዋበች ቈንጆ ፈለጉ፤ ሱነማይቱን አቢሳንም አገኙ፥ ወደ ንጉሡም ይዘዋት መጡ።
4 ፤ ቈንጆይቱም እጅግ ውብ ነበረች፤ ንጉሡንም ትረዳውና ታገለግለው ነበር፥ ንጉሡ ግን አያውቃትም ነበር።
5 ፤ የአጊትም ልጅ አዶንያስ። ንጉሥ እሆናለሁ ብሎ ተነሣ፤ ሰረገሎችንና ፈረሰኞችን በፊቱም የሚሮጡ አምሳ ሰዎች አዘጋጀ።
6 ፤ አባቱም ከቶ በሕይወቱ ሳለ። እንዲህ ለምን ታደርጋለህ? ብሎ አልተቈጣውም ነበር፤ እርሱ ደግሞ እጅግ ያማረ ሰው ነበረ፤ ከአቤሴሎምም በኋላ ተወልዶ ነበር።
7 ፤ ሴራውም ከጽሩያ ልጅ ከኢዮአብና ከካህኑ ከአብያታር ጋር ነበረ፥ እነርሱም አዶንያስን ተከትለው ይረዱት ነበር።
8 ፤ ነገር ግን ካህኑ ሳዶቅና የዮዳሄ ልጅ በናያስ ነቢዩም ናታን ሳሚም ሬሲም የዳዊትም ኃያላን ከአዶንያስ ጋር አልነበሩም።
9 ፤ አዶንያስም በጎችንና በሬዎችን ፍሪዳዎችንም በዓይንሮጌል አጠገብ ባለችው በዞሔሌት ድንጋይ ዘንድ ሠዋ፤ የንጉሡንም ልጆች ወንድሞቹን ሁሉ፥ የንጉሡንም ባሪያዎች፥ የይሁዳን ሰዎች ሁሉ ጠራ።
10 ፤ ነገር ግን ነቢዩን ናታንን፥ በናያስንም፥ ኃያላኑንም፥ ወንድሙንም ሰሎሞንን አልጠራም።
11 ፤ ናታንም የሰሎሞንን እናት ቤርሳቤህን እንዲህ ብሎ ተናገራት። ጌታችን ዳዊት ሳያውቅ የአጊት ልጅ አዶንያስ እንደ ነገሠ አልሰማሽምን?
12 ፤ አሁንም ነዪ፥ የልጅሽን የሰሎሞንን ነፍስና የአንቺን ነፍስ እንድታድኝ እመክርሻለሁ።
13 ፤ ሄደሽ ወደ ንጉሡ ወደ ዳዊት ግቢና። ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ ለእኔ ለባሪያህ። ልጅሽ ሰሎሞን ከእኔ በኋላ ይነግሣል፥ በዙፋኔም ይቀመጣል ብለህ አልማልህልኝምን? ስለ ምንስ አዶንያስ ይነግሣል? በዪው።
14 ፤ እነሆ፥ አንቺ በዚያ ለንጉሥ ስትነግሪ እኔ ከአንቺ በኋላ እገባለሁ፥ ቃልሽንም አጸናለሁ።
15 ፤ ቤርሳቤህም ወደ ንጉሡ ወደ እልፍኝ ገባች፤ ንጉሡም እጅግ ሸምግሎ ነበር፥ ሱነማይቱም አቢሳ ታገለግለው ነበር።
16 ፤ ቤርሳቤህም አጐንብሳ ለንጉሡ እጅ ነሣች፤ ንጉሡም። ምን ትፈልጊያለሽ? አለ።
17 ፤ እርስዋም አለችው። ጌታዬ ሆይ፥ አንተ ለባሪያህ። ልጅሽ ሰሎሞን ከእኔ በኋላ ይነግሣል፥ በዙፋኔም ይቀመጣል ብለህ በአምላክህ በእግዚአብሔር ምለህልኛል፤
18 ፤ አሁንም፥ እነሆ፥ አዶንያስ መንገሡ ነው፤ አንተም ጌታዬ ንጉሥ ይህን አታውቅም፤
19 ፤ እርሱም ብዙ በሬዎችንና ፍሪዳዎችን በጎችንም ሠውቶአል፥ የንጉሡንም ልጆች ሁሉ፥ ካህኑንም አብያታርን፥ የሠራዊቱንም አለቃ ኢዮአብን ጠርቶአል፤ ባሪያህን ሰሎሞንን ግን አልጠራውም።
20 ፤ አሁንም፥ ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ ከአንተ በኋላ በጌታዬ በንጉሥ ዙፋን ላይ የሚቀመጠውን ትነግራቸው ዘንድ የእስራኤል ሁሉ ዓይን ይመለከትሃል።
21 ፤ ይህ ባይሆን፥ ጌታዬ ከአባቶችህ ጋር ባንቀላፋህ ጊዜ እኔና ልጄ ሰሎሞን እንደ ኃጢአተኞች እንቈጠራለን።
22 ፤ እነሆም፥ ለንጉሡ ስትናገር ነቢዩ ናታን ገባ።
23 ፤ ለንጉሡም። እነሆ፥ ነቢዩ ናታን መጥቶአል ብለው ነገሩት፤ እርሱም ወደ ንጉሡ ፊት በገባ ጊዜ በግምባሩ በምድር ላይ ተደፍቶ ለንጉሡ እጅ ነሣ።
24 ፤ ናታንም አለ። ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ አንተ። ከእኔ በኋላ አዶንያስ ይነግሣል፥ በዙፋኔም ላይ ይቀመጣል ብለሃልን?
25 ፤ እርሱ ዛሬ ወርዶ ብዙ በሬዎችንና ፍሪዳዎችን በጎችንም ሠውቶአል፥ የንጉሡንም ልጆች ሁሉ፥ የሠራዊትንም አለቃ ኢዮአብን፥ ካህኑንም አብያታርን ጠርቶአል፤ እነሆም፥ በፊቱ እየበሉና እየጠጡ። አዶንያስ ሺህ ዓመት ይንገሥ ይላሉ።
26 ፤ ነገር ግን እኔን ባሪያህን፥ ካህኑንም ሳዶቅን፥ የዮዳሄንም ልጅ በናያስን፥ ባሪያህንም ሰሎሞንን አልጠራም።
27 ፤ በውኑ ይህ ነገር ከጌታዬ ከንጉሡ የተደረገ ነውን? ለባሪያህም ከአንተ በኋላ በጌታዬ በንጉሡ ዙፋን ላይ የሚቀመጠውን አልነገርህምን?
28 ፤ ንጉሡም ዳዊት። ቤርሳቤህን ጥሩልኝ ብሎ መለሰ። ወደ ንጉሡም ገባች፥ በንጉሡም ፊት ቆመች።
29 ፤ ንጉሡም። ነፍሴን ከመከራ ሁሉ ያዳነኝ ሕያው እግዚአብሔርን!
30 ፤ በእውነት። ልጅሽ ሰሎሞን ከእኔ በኋላ ይነግሣል፥ በእኔም ፋንታ በዙፋኔ ላይ ይቀመጣል ብዬ በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር እንደ ማልሁልሽ፥ እንዲሁ ዛሬ በእውነት አደርጋለሁ ብሎ ማለ።
31 ፤ ቤርሳቤህም በግምባርዋ በምድር ላይ ተደፍታ ለንጉሡ እጅ ነሣችና። ጌታዬ ንጉሥ ዳዊት ለዘላለም በሕይወት ይኑር አለች።
32 ፤ ንጉሡም ዳዊት። ካህኑን ሳዶቅንና ነቢዩን ናታንን የዮዳሄንም ልጅ በናያስን ጥሩልኝ አለ። ወደ ንጉሡም ፊት ገቡ።
33 ፤ ንጉሡም አላቸው። የጌታችሁን ባሪያዎች ይዛችሁ ሂዱ፥ ልጄንም ሰሎሞንን በበቅሎዬ ላይ አስቀምጡት፥ ወደ ግዮንም አውርዱት፤
34 ፤ በዚያም ካህኑ ሳዶቅና ነቢዩ ናታን በእስራኤል ላይ ንጉሥ አድርገው ይቅቡት፤ ቀንደ መለከትም ነፍታችሁ። ሰሎሞን ሺህ ዓመት ይንገሥ በሉ።
35 ፤ በኋላውም ተከትላችሁ ውጡ፤ እርሱም መጥቶ በዙፋኔ ላይ ይቀመጥ፥ በእኔም ፋንታ ይንገሥ፤ በእስራኤልና በይሁዳም ላይ አለቃ ይሆን ዘንድ አዝዣለሁ።
36 ፤ የዮዳሄም ልጅ በናያስ መልሶ ለንጉሡ አለ፥ ያበጅ ያድርግ፤ የጌታዬም የንጉሥ አምላክ ይህን ይናገር።
37 ፤ እግዚአብሔር ከጌታዬ ከንጉሥ ጋር እንደ ነበረ እንዲሁ ከሰሎሞን ጋር ይሁን፥ ዙፋኑንም ከጌታዬ ከንጉሡ ዳዊት ዙፋን የበለጠ ያድርግ።
38 ፤ ካህኑም ሳዶቅና ነቢዩ ናታን የዮዳሄም ልጅ በናያስ ከሊታውያንና ፈሊታውያንም ወረዱ፥ ሰሎሞንንም በንጉሡ በዳዊት በቅሎ ላይ አስቀምጠው ወደ ግዮን አመጡት።
39 ፤ ካህኑም ሳዶቅ ከድንኳኑ የቅብዓቱን ቀንድ ወስዶ ሰሎሞንን ቀባ፤ ቀንደ መለከትም ነፉ፤ ሕዝቡም ሁሉ። ሰሎሞን ሺህ ዓመት ይንገሥ አሉ።
40 ፤ ሕዝቡም ሁሉ እርሱን ተከትለው ወጡ፥ ሕዝቡም ዘፈን ይዘፍኑ ነበር፥ በታላቅም ደስታ ደስ አላቸው፤ ከጩኸታቸውም የተነሣ ምድር ተናወጠች።
41 ፤ አዶንያስና እርሱም የጠራቸው ሁሉ መብሉና መጠጡ ተፈጽሞ ሳለ ሰሙ፤ ኢዮአብም የቀንደ መለከት ጽምፅ በሰማ ጊዜ። ይህ በከተማ ውስጥ ያለ የሽብር ድምፅ ምንድር ነው? አለ።
42 ፤ እርሱም ይህን ሲናገር የካህኑ የአብያታር ልጅ ዮናታን መጣ፤ አዶንያስም። አንተ መልካም ሰው ነህና፥ መልካም ታወራልናለህና ግባ አለ።
43 ፤ ዮናታንም ለአዶንያስ እንዲህ ብሎ መለሰ። በእውነት ጌታችን ንጉሥ ዳዊት ሰሎሞንን አነገሠው።
44 ፤ ንጉሡም ከእርሱ ጋር ካሁኑን ሳዶቅንና ነቢዩን ናታንን የዮዳሄንም ልጅ በናያስን ከሊታውያንንና ፈሊታውያንንም ሰደደ፥ በንጉሡም በቅሎ ላይ አስቀመጡት።
45 ፤ ካህኑም ሳዶቅና ነቢዩ ናታን በግዮን ንጉሥ አድርገው ቀቡት፤ ከዚያም ደስ ብሎአቸው ወጡ፥ ከተማይቱም አስተጋባች፤ የሰማችሁትም ድምፅ ይህ ነው።
46 ፤ ደግሞም ሰሎሞን በመንግሥቱ ዙፋን ላይ ተቀምጦአል።
47 ፤ የንጉሡም ባሪያዎች ገብተው። እግዚአብሔር የሰሎሞንን ስም ከስምህ ዙፋኑንም ከዙፋንህ የበለጠ ያድርግ ብለው ጌታችንን ንጉሡን ዳዊትን ባረኩ፤ ንጉሡም በአልጋው ላይ ሆኖ ሰገደ።
48 ፤ ንጉሡም ደግሞ። ዓይኔ እያየ ዛሬ በዙፋኔ ላይ የሚቀመጠውን የሰጠኝ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን አለ።
49 ፤ አዶንያስም የጠራቸው ሁሉ ፈሩ፥ ተነሥተውም እያንዳንዳቸው በየመንገዳቸው ሄዱ።
50 ፤ አዶንያስም ሰሎሞንን ፈራ፥ ተነሥቶም ሄደ፥ የመሠዊያውንም ቀንድ ያዘ።
51 ፤ ለሰሎሞንም። እነሆ፥ አዶንያስ ንጉሡን ሰሎሞንን ፈርቶ። ንጉሡ ሰሎሞን ባሪያውን በሰይፍ እንዳይገድለኝ ዛሬ ይማልልኝ ብሎ የመሠዊያውን ቀንድ ይዞአል አሉት።
52 ፤ ሰሎሞንም። እርሱ አካሄዱን ያሳመረ እንደ ሆነ ከእርሱ አንዲት ጠጕር እንኳ በምድር ላይ አትወድቅም፤ ነገር ግን ክፋት የተገኘበት እንደ ሆነ ይሞታል አለ።
53 ፤ ንጉሡ ሰሎሞንም ላከ፥ ከመሠዊያውም አወረዱት፤ መጥቶም ለንጉሡ ለሰሎሞን እጅ ነሣ፥ ሰሎሞንም። ወደ ቤትህ ሂድ አለው።