መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ።

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22


ምዕራፍ 17

በገለዓድ ቴስቢ የነበረው ቴስብያዊው ኤልያስ አክዓብን። በፊቱ የቆምሁት የእስራኤል አምላክ ሕያው እግዚአብሔርን! ከአፌ ቃል በቀር በእነዚህ ዓመታት ጠልና ዝናብ አይሆንም አለው።
2 ፤ የእግዚአብሔርም ቃል እንዲህ ሲል ለእርሱ መጣለት።
3 ፤ ከዚህ ተነሥተህ ወደ ምሥራቅ ሂድ፥ በዮርዳኖስም ትይዩ ባለው በኮራት ፈፋ ውስጥ ተሸሸግ።
4 ፤ ከወንዙም ትጠጣለህ፥ ቍራዎችም በዚያ ይመግቡህ ዘንድ አዝዣለሁ።
5 ፤ ሄደም እንደ እግዚአብሔር ቃልም አደረገ። ሄዶም በዮርዳኖስ ትይዩ ባለው በኮራት ፈፋ ውስጥ ተቀመጠ።
6 ፤ ቍራዎቹም በየጥዋትና በየማታው እንጀራና ሥጋ ያመጡለት ነበር፤ ከወንዙም ይጠጣ ነበር።
7 ፤ ከብዙ ቀንም በኋላ በምድር ላይ ዝናብ አልነበረምና ወንዙ ደረቀ።
8 ፤ ተነሥተህም በሲዶና አጠገብ ወዳለችው ወደ ሰራፕታ ሂድ፥ በዚያም ተቀመጥ፤
9 ፤ እነሆም፥ ትመግብህ ዘንድ አንዲት ባልቴት አዝዣለሁ የሚል የእግዚአብሔር ቃል መጣለት።
10 ፤ ተነሥቶም ወደ ሰራፕታ ሄደ፤ ወደ ከተማይቱም በር በደረሰ ጊዜ አንዲት ባልቴት በዚያ እንጨት ትለቅም ነበር፤ እርሱም ጠርቶ። የምጠጣው ጥቂት ውኃ በጽዋ ታመጭልኝ ዘንድ እለምንሻለሁ አላት።
11 ፤ ውኃም ልታመጣለት በሄደች ጊዜ ወደ እርስዋ ጠርቶ፥ ቁራሽ እንጀራ በእጅሽ ይዘሽ ትመጭ ዘንድ እለምንሻለሁ አላት።
12 ፤ እርስዋም። አምላክህ ሕያው እግዚአብሔርን! በማድጋ ካለው ከእፍኝ ዱቄት፥ በማሰሮም ካለው ከጥቂት ዘይት በቀር እንጀራ የለኝም፤ እነሆም፥ ገብቼ ለእኔና ለልጄ እጋግረው ዘንድ በልተነውም እንሞት ዘንድ ጥቂት እንጨት እሰበስባለሁ አለች።
13 ፤ ኤልያስም አላት። አትፍሪ፤ ይልቅስ ሄደሽ እንዳልሺው አድርጊ፤ አስቀድመሽ ግን ከዱቄቱ ለእኔ ታናሽ እንጎቻ አድርገሽ አምጭልኝ፥ ከዚያም በኋላ ለአንቺና ለልጅሽ አድርጊ፤
14 ፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። በምድር ላይ እግዚአብሔር ዝናብ እስከሚሰጥበት ቀን ድረስ፥ ዱቄቱ ከማድጋ አይጨረስም፥ ዘይቱም ከማሰሮው አይጎድልም።
15 ፤ እርስዋም ሄዳ እንደ ኤልያሳ ቃል አደረገች፤ እርስዋና እርሱ ቤትዋም ብዙ ቀን በሉ።
16 ፤ በኤልያስም እጅ እንደ ተናገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል ዱቄቱ ከማድጋው አልተጨረሰም፥ ዘይቱም ከማሰሮው አልጎደለም።
17 ፤ ከዚያም በኋላ የባለቤቲቱ ልጅ ታመመ፤ ትንፋሹም እስኪታጣ ድረስ ደዌው እጅግ ከባድ ነበረ።
18 ፤ እርስዋም ኤልያስን። የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለኝ? ኃጢአቴንስ ታሳስብ ዘንድ፥ ልጄንስ ትገድል ዘንድ ወደ እኔ መጥተሃልን? አለችው።
19 ፤ ኤልያስም። ልጅሽን ስጪኝ አላት። ከብብትዋም ወስዶ ተቀምጦበት ወደ ነበረው ሰገነት አወጣው በአልጋውም ላይ አጋደመው።
20 ፤ ወደ እግዚአብሔርም። አቤቱ አምላኬ ሆይ፥ ልጅዋን በመግደልህ ይህችን ትቀልበኝ የነበረቺቱን ባልቴት እንዲህ ደግሞ አስጨነቅኻትን? ብሎ ጮኸ።
21 ፤ በብላቴናውም ላይ ሦስት ጊዜ ተዘረጋበት፥ ወደ እግዚአብሔርም። አቤቱ አምላኬ ሆይ፥ የዚህ ብላቴና ነፍስ ወደ እርሱ ትመለስ ዘንድ እለምንሃለሁ ብሎ ጮኸ።
22 ፤ እግዚአብሔርም የኤልያስን ቃል ሰማ፤ የብላቴናው ነፍስ ወደ እርሱ ተመለሰች፥ እርሱም ዳነ።
23 ፤ ኤልያስም ብላቴናውን ይዞ ከሰገነቱ ወደ ቤት አወረደው፥ ኤልያስም። እነሆ፥ ልጅሽ በሕይወት ይኖራል ብሎ ለእናቱ ሰጣት።
24 ፤ ሴቲቱም ኤልያስን። የእግዚአብሔር ሰው እንደ ሆንህ፥ የእግዚአብሔርም ቃል በአፍህ እውነት እንደ ሆነ አሁን አወቅሁ አለችው።